በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጉዳይ በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ የተወሰነ ምንም አዲስ ጉዳይ የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።
ሕዝብ ሳይወያይበት ለምን በአደባባይ ተገለጸ በሚል ሕወሃት ያቀረበውን ጥያቄ በተመለከተም ከእንግዲህ የመደበቅ ፖለቲካ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
አሰብን ስንሰጥስ ሕዝብን አወያይተናል ወይ በማለት ጥያቄውን በጥያቄ የመለሱት ጠቅላይ ሚኒስት አብይ አህመድ ውጥረቱ ሊረግብ በድንበር ላይ ያለውም ሕዝብ እፎይ ሊል ይገባል ብለዋል።
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊው ጦርነት እንደሆነ ዛሬ በፓርላማ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ላለፉት 20 አመታትም ሃገራቱ በውጥረት ውስጥ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባድመን በተመለከተ ያሳለፈው ውሳኔም ቢሆን በፓርላማ የተወሰነውን ወደ ተግባር የመቀየር ርምጃ እንጂ አዲስ የተለወጠ ነገር የለም ብለዋል።
አዲስ የተወሰነ ውሳኔ እንደሌለ አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፓርላማው ሊጠይቅ የሚገባው የፓርላማው ውሳኔ እስካሁን ተግባራዊ ለምን አልሆነም በሚል መሆን እንደነበረበት አስገንዝበዋል።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚም ባድመን ነጥሎ እንዳልተወያየ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተወያየነው ሁለቱን ሃገራት ስለሚያዋስነው አንድ ሺ ኪሎ ሜትር ነው ብለዋል።
ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ/ሕወሃት/ሕዝብ ሳይወያይበት ለምን በይፋ ተገለጸ ማለቱን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከሕዝብ የሚደበቅ ነገር መኖር የለበትም የስራ አስፈጻሚው ስብሰባም ቢሆን በየደቂቃው ለሕዝብ መገለጽ አለበት የድብቅ ፖለቲካ ማብቃት አለበት ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል።
ሕዝብን በቅድሚያ ማወያየት አለብን የሚሉት ወገኖች አሰብን ሲሰጡ ሕዝብ አወያይተዋል ወይ የሚል ጥያቄንም ለፓርላማው አቅርበዋል።
መገናኛ ብዙሃንም ለሕዝብ ተደራሽ የሆኑና ነጻ መሆን አለባቸው ብለዋል።
No comments:
Post a Comment