ኤርትራ ወደ አዲስ አበባ የልኡካን ቡድን እንደምትልክ አስታወቀች።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ በተከበረው የሰማዕታት ቀን ላይ ወደ አዲስ አበባ ስለሚልኩት የልኡካን ቡድናቸው በይፋ መናገራቸውም ታውቋል።
በኢትዮጵያ የተከሰተው የፖለቲካ ለውጥ ቀልብ የሚስብ ነው በማለት የገለጹት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ ሃገራት መካከል ለሚደረገው ገንቢ ውይይት የልኡካን ቡድናቸው ወደአዲስ አበባ ያመራል ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምላሽ የመጣው የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበል መወሰኑን ተከትሎ ነው።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምላሽ ምስጋና ማቅረባቸውንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት ላይ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበለውና ለተግባራዊነቱም እንደሚሰራ ውሳኔ ላይ ከደረሰ በኋላ በኤርትራ በኩል ይፋዊ ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል።
በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ የኤርትራ አምባሳደሮችና የኤርትራ መንግስት ቃለ-አቀባይ ወዲያውኑ በሰጡት አጭር ምላሽም ቢሆን ስለ ኢሕአዴጉ መግለጫ የኤርትራን አቋም ከመግለጽ ተቆጥበው ነበር።
ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካኝነት ኤርትራ ምላሿን አስታውቃለች።
በሀገሪቱ ቴሌቪዥን በቀጥታ በተላለፈና የሰማዕታትን ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የፖለቲካ ለውጥ ትኩረት የሚስብ እንደሆነም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሽግግር ወቅት ላይ መሆኗን ተገንዝበናል ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ኢትዮጵያ አንድ የልዑካን ቡድን እንደሚልኩ ነው በይፋ ያስታወቁት።
አቶ ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩት ቡድን ገንቢ ውይይት እንደሚያደርግ ከመግለጽ ባለፈ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።
መቼና እንዴት የልዑካን ቡድኑ ወደኢትዮጵያ እንደሚያመራ የገለጹት ነገር ግን የለም።
በኢትዮጵያ የሚታየው ለውጥ ወዴት ያመራል የሚለው በጥያቄ የሚተው ነው ያሉት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጊዜ ቢወስድም የህወሀት አገዛዝ እያበቃለት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ በትኩረት የሚሰራ ተግባር እንደሆነም አስታውቀዋል።
የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምላሽን በደስታ እንደተቀበሉትም የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል።
ወልቂጤ ላይ ህዝባዊ መድረክ እየመሩ የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂን ምላሽ የሰሙት ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ የኤርትራን የልዑካን ቡድን በታላቅ አክብሮት ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
የፕሬዝዳንት ኢሳያስን የዛሬ ምላሽ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በትኩረት የዘገቡት ሲሆን ከ20 ዓመታት በላይ ለዘለቀው የሁለቱ ሃገራት ፍጥጫ መፍትሄ በመስጠት አንጻር የመጀመሪያ ስኬታማ ድርድር ሊሆን እንደሚችል በመገለጽ ላይ ነው።
ሁለቱ ሀገራት እዚህ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በሸምጋይነት መሀል የገቡ ወገኖች ስለመኖራቸው የተገለጸ ነገር የለም።
በቀጣይም ያለአደራዳሪ ሁለቱ ሀገራት ለመወያየት መፍቀዳቸው ነው የተገለጸው።
No comments:
Post a Comment