Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, June 12, 2018

የወልቂጤ ነዋሪ ህወሃትን በማውገዝ ተቃውሞ አሰማ


ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቀባበል የወጣው የወልቂጤ ነዋሪ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ህወሃትን በማውገዝ ተቃውሞ ማሰማቱ ተገለጸ።
በቅርቡ በወልቂጤ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ህዝቡን ለማነጋገር ወደ አካባቢው ያመሩት ዶክተር አብይ አህመድም በሀዋሳ፣ በወላይታና ወልቂጤ በደረሱት ግጭቶች እጃቸው ያለበት የመንግስት ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸው እንደሚነሱና በህግ እንደሚጠየቁም አስታውቀዋል።
የወልቂጤ ነዋሪ በቅርቡ የተከሰተው ግጭት የህወሃት እጅ እንዳለበት በመግለጽ ተቃውሞውን ማቅረቡ ተሰምቷል።
በተያያዘ ዜና ከልደታ ፍርድ ቤት ችሎት የወጡ በርካታ እስረኞች ህወሃትን በማውገዝ መፈክር ማሰማታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወልቂጤ እንደሚገቡ ከተገለጸበት ዛሬ ጠዋት አንስቶ የወልቂጤ ጎዳናዎች በነዋሪው መሞላት መጀመራቸውን ነው መረጃዎች ያመለከቱት።
በእርስ በእርስ ግጭት ለሰነበተችው ወልቂጤ ዛሬ የተለየ ትዕይንት ይስተናገድባታል ተብሎ አልተጠበቀም።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል የወጣው ህዝብ ግን ምሬት ብሶቱን ለማሰማት መልካም አጋጣሚን ፈጥሮለታል።
ባለፈው ሳምንት በተከሰተውና ለሶስት ሰዎች መገደል ምክንያት የሆነው ግጭት ከህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የዘር ፖለቲካ የመነጨ ነው በሚል ተቃውሞውን በህወሃት ላይ ያደረገው የወልቂጤ ነዋሪ፣ ውግዘቱን ሲያሰማ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ የወልቂጤ ነዋሪ ከኢትዮጵያ ከጫፍ እስከጫፍ እየተዘዋወረ በነጻነት ሲኖር የነበረው የጉራጌ ህዝብ በዘመነ ህወሃት በገዛ ቤቱ እንኳን መኖር አልቻለም ሲሉ በምሬት ተናግሯል።
የቅርብ ጊዜው ግጭትም የህወሃት ሴራ ውጤት ነው ብለዋል ነዋሪው።
ለዶክተር አብይ አቀባበል የወጣው የወልቂጤ ነዋሪዎች በአስቸኳይ የህወሃት አገዛዝ እንዲወርድ የጠየቁ ሲሆን ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወልቂጤው መድረክ የተገኙት በቀጥታ የሀውሳና የወላይታ ህዝባዊ ውይይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሲሆን በሶስቱም አካባቢዎች ለተፈጠረው ግጭት ተጠያቂ የሆኑ አመራሮች ራሳቸውን ከስልጣናን እንዲያገሉ ጠይቀዋል።
ምርመራ ተካሂዶ ጥፋተኞችም ለፍርድ እንደሚቀርቡ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የገለጹት።
በስም የትኞቹ አመራሮች ለፍርድ እንደሚቀርቡ ባይገለጽም በነዋሪው በኩል ግን አንዳንድ ባለስልጣናት ተጠቅሰው ለፍርድ እንዲቀርቡ ተጠይቋል።
በሲዳማ፣ በወላይታና በወልቂጤ ነዋሪዎች ዘንድ ስማቸው ተነስቶ ለፍርድ እንዲቀርቡ ከተጠየቁት መካከል የደኢህዴን አመራሮች አቶ ሽፈራው ሽጉጤና አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ይገኙበታል።
በተያያዘ ዜና በአርባምንጭ ከተማም ህወሃትን የሚያወግዝ የተቃውሞ ትዕይንት የተደረገ ሲሆን በጅማ ለተፈቱ እስረኞች አቀባበል እያደረጉ ባሉ ነዋሪዎች ላይ የአገዛዙ ታጣቂዎች ርምጃ በመውሰድ በርካታ ሰዎችን ማቁሰላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በአዲስ አበባ ልደታ ፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበራቸው እስረኞችም ትላንት ከችሎት ሲወጡ የህወሃትን አገዛዝ በማውገዝ መፈክር ሲያሰሙ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
እስረኞቹ በእልህና ቁጣ የህወሀት አገዛዝ ዘረኛ ነው፣ ህወሃት ወንጀለኛ ነው የሚሉና ሌሎች መልዕክቶችን በማሰማት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials