Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, June 30, 2018

አርበኛ ታጋይ ሽባባው ጌታሁን ለሀገሩ ማድረግ ያለበትን ሁሉ አድርጎ በመጨረሻ በክብር አረፈ


የአገራችን ፖለቲካ እንዲስተካከል እድሜውን ሙሉ የለፋና የደከመ ፣የኢትዮጵያን ህዝቦች ከጭንቀት ለመገለገል የወጣና የወረደ የያኔው የኢህአፖ የአሁኑ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አርበኛ ታጋይ ሽባባው ጌታሁን ። እራሱን እንደ ሻማ አቅልጦ ለሌሎች ብርሃን ለመሆን በክብርና በኩራት ታሪክ ሰርቶ ያለፈ ጀግና። አርበኛ ታጋይ ሽባባው ሞትን ከአንዴ ሁለት ሶስቴ በተለያዩ ጦር ሜዳዎች ተጋፍጦ አሸንፏል። ይህ ሞትን በተደጋጋሚ የተጋፈጠውና እጅ ላለመስጠት አልያም ከመቃብር በላይ የሚያስጠራ ስራ ሰርቶ ለማለፍ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይለው ሃያል ሰው በመጨረሻ ስዓት የድል ሻማውን ከፍ አድርጎ ሳይጨርስ ከትግል ጓዶቹ በሞት ተለይቶናል። አባታችን ፣ወንድማችን፣ መካሪያችን፣ አስተማሪያችን፣ አለኝታችን ጓድ ሽባባው ጌታሁን ።

አርበኛ ታጋይ ሽባባው ጌታሁን ከአባቱ ከወታደር ጌታሁን ዋዩ እና ከእናቱ ወ/ሮ የሻለም ፈንታ በ1952 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ ልዩ ስሙ መሆና ጊዮርጊስ በሚባል አካባቢ ተወለደ ። በተወለደበት በአካባቢ ከእኩዮቹ ጋር የልጅነት ጊዜውን አጣጥሞ ሳይጨርስ የ5 ዓመት ልጅ እያለ አባቱ አቶ ጌታሁን ዋዩ ወታደር ቤት በመቀጠራቸው ምክንያት ወደ አዘዞ ከተማ ከአባቱ ጋር መጣ ።እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በዛው በአዘዞ ከተማ ትምህርቱን አንድ ብሎ በመጀመር ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማረ ከ9-12ኛ ክፍል ትምህርቱን ደግሞ በጎንደር ከተማ በአጼ ፋሲለደስ ትምህርት ቤት ተምሯል ።ይሁን እንጅ የ12ተኛ ክፍል አገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና አልወሰደም በጊዜው የግራው ፖለቲካው ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ስለነበር በህቡዕ በወጣቶች ማህበር ሲንቀሳቀስ ቆይቶ በ1969 ዓ/ም ከኢህአፖ የከተማ መዋቅር ወደ ገጠሩ የኢህአፖ መዋቅር ጎልማሳነቱና ህይወቱ፣ቤተሰቡና ትምህርቱ ሳያሳስቡት በቆራኝነት ጠለምት ወደ ሚገኘው የኢህአፖ ሰራዊት በማምራት ትግሉን ተቀላቀለ ። ከህጻንነት ጊዜው ጀምሮ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ስላደገ የወታደራዊ ህይዎት ብዙም አልከበደው በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በወታደራዊ መዋቅሩ በምክትል ጋንታ መሪነትና ፣በብሬን ተኳሽነት ተመድቦ ያገለገለ ሲሆን በተጨማሪም በሀይል መሪነት አገልግሏል። በሶስትና አራት ሀይሎች ውስጥም የወታደራዊና የፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን መርቷል። አርበኛ ታጋይ ሽባባው ብዙ ጦር ሜዳዎች ላይ በተዋጊነትና በአዋጊነት ተፋልሟል አፋልሟል፣ አካሉን አጥቷል፣ ጓዶቹን ሰውቷል። አስቸጋሪውን የጣረሞትና የሲቃ በአይኑ አይቷል ኑዛዜአቸውንና አደራቸውን በጀሮው ሰምቶ ተቀብሏል።በ1974 ዓ/ም የኢህአፖ በገጠመው ችግር የመበተን አደጋ ሲያጋጥመው ከፊሉ ወደ ሱዳን ሲሰደድ የተወሰኑት ደግሞ ወደ ኤርትራ በማቅናት ሁለት ወር ግምገማ አድርገው ድርጅቱን ለመታደግ በሞከሩበትና ወደ ቋራ ለዳግም ትግል ሲመለሱ በወቅቱ አርበኛ ታጋይ ሽባባው ቀኝ እጁ ላይ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ አጋጥሞት ስለነበር በጀበሃ አጋዥነት ከሰላ ህክም ላይ ቆይቶ ነበር። ህክምናው ብዙም ለውጥ ስላልታየበት ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ ካርቱም ለከፍተኛ ህክምና እንዲሄድ ተደርጎ ለስምንት ወራት ህክምናውን ሲከታተል ከቆየ በኋላ በ1974 ዓ/ም መጨረሻ ወደ አሜሪካን ሀገር ችጋጎ የመሄድ እድል አግኝቶ ካርቱምን ተሰናብቶ ሄደ።
ጓድ ሽባባው አሜሪካን ሀገር በኖረባቸው 36 ዓመታት በነበረውም ሀገራዊ ስሜትና ተቆርቋሪነት በአሜሪካን ሀገር የኢትዮጵያ ኮሚነቲ ማህበርን በሊቀመንበረነት ለሰባት ተከታታይ አመታት በመመረጥ መርቷል። የማህበሩ አባላትም በሀገራቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦና አሻራቸውን እንዲያስቀምጡ በፖለቲካው መድረክ ሲሰራ ቆይቷል ።ኢህአፖን ወደ ነበረበት የትግል ጎዳና ለመመለስ በተደጋጋሚ ሲጥር የነበረው ጓድ ሽባባው እንዳሰበው ስላልሆነለት በመጨረሻ ድርጅቱን ለቅቆ የጓዶችን አላማ ለማሳካት የተሻለ ነው፣ ከግብም ያደርስልኛል ብሎ ያሰበውን አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄን የውጭው ዘርፍን ተቀላቅሎ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በወታደራዊ ዘርፍ ልምዱን ለመካፈል በማሰብ የድርጅቱን የትጥቅ ትግል ተቀላቀለ ።
አርበኛ ታጋይ ሽባባው ጌታሁን የሶስት ልጆች አባትና የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነበር ነገር ግን የልጆቹና የቤተሰቡ ሁኔታ ሳያስጨንቀው የተደላደለ የአሜሪካን ሀገር ኑሮውን ጥሎ ኤርትራ በርሃ ገባ ።ለአርበኛ ታጋዩ የትጥቅ ትግልን ለመቀላቀል ምክንያት የሆነው በኢህአፖና በተለያዩ ድርጅቶች ስም ለነጻነትና ዴሞክራሲ ሲሉ አብረውት ተሰልፈው ደማቸውና አጥንታቸው እንዲሁም ምትክ የለላት ህይወታቸውን የሰጡለትን ትግል ፍሬ እንዲያፈራ ለማድረግ በጠመንጃ ሃይል የተገኘን የመንግሥት ሥልጣን የሙጥኝ ብለው የአገራችንና የህዝባችንን ስቃይ ለማራዘም የወሰኑትን ለመፋለም ተገዶ በማረፊያ ዕድሜው መሳሪያ ለማንሳት ከተገደዱት ቅን ዜጎች አንዱ ነው።
ጓድ ሽባባው የብዙ ኢትዮጵያውያን ህይዎት ተገብሮበት ከዚህ ግባ የሚባል ውጤት ያልታየበትን የሀገራችን ፖለቲካ ለማስተካከልና መንገድ ላይ ተሰውተው የቀሩት ጉዶቹ የከንቱ ሞት እንዳልሞቱ የተነሱለትን አላማ ከግብ በማድረስ በሽምግልና እድሜው ፣በጥይት የተጎዳ አካሉ ሳይበግረው፣ በውሃ ጥምና በርሃብ እየደከመና እየዛለ፣በተራራና በቁልቁለት እየወጣና እየወረደ ፣በቀንና በሌሊት ጉዞዎች እየወደቀና እየተነሳ በብዙ ስቃዮች በመፈተን የድርሻውን ሃላፊነት ለመወጣት ወስኖ በ2008ዓ/ም ኤርትራ በርሃ ከሚገኘው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሰራዊት ጋር ለዳግም የትጥቅ ትግል ሲቀላቀል አረአያነቱ ከርሱ ጋር ለነበሩት ጓዶቹ ቀላል አልነበረም።
ጓድ ሽባባው ለወጣቶች የትግል ተሞክሮውን፣ልምዱንና ያለፈባቸውን እልህ እስጨራሽ የፖለቲካና የወታደራዊ ፈተናዎችና መሰናክሎችን ለወጣቶች በማስተማር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ትግሉን አንድ ደረጃ ወደ ፊት ለመግፋት የነበረው ቁርጠኝነት እጅግ የሚደነቅ ነው። በአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የተጋትሮ መምሪያ ውስጥ የትምህርትና ስልጠና መምሪያ ሀላፊ በመሆን አዲስ አርበኛ ታጋዮችን በፖለቲካውና በወታደራዊው መስክ ብቁ እንዲሆኑ ሲሰራ ቆይቷል። ለኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲን ፣ነጻነትን፣ፍትህን ፣ እኩልነትን ፣አንድነትን ለማጎናጸፍ የአንድ ሰው እድሜ የሚያክል ጊዜ በትግል ላይ ሲቆይ አንድ ቀን ሳይሰለችና ተስፋ ሳይቆርጥ ከጠለምት እስከ በለሳ ፣ከቋራ እስከ ሱዳን ፣ ከኤሜሪካ እስከ ኤርትራ ቦታዎች በፖለቲካው አለም ታላቅ ስራ ሰርቷል ። በኢህአፖና በአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ውስጥ በሰላማዊና በትጥቅ ትግል ውስጥ ለሀገሩና ለወገኑ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል ። አርበኛ ታጋይ ሽባባው ለወጣት አርበኛ ታጋዮች ትልቅ እክብሮት የነበረውና እነሱንም ድርጅቱ በሚፈልጋቸው መንገድ በመቅረጽና በማብቃት ለኢትዮጵያ ህዝብ ጩኽትና መከራ የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ እንዲሁም የያዙት ታሪካዊና ወገናዊ ሀላፊነት እጅግ የሚከብድ እንደሆነና እሱንም በመወጣት ታሪክ የምትመሰክርላችሁ ጀግኖች እንጅ የምትወቅሳችሁ እንዳትሆኑ እያለ እንደ ጉንዳን ሁሌም የሚሰራና የሚያሰራ ፣የሀገር መሰረት ፈር ቀዳጅና የነጻነት ትግሉ ቀንዲል ቆራጥና ጽኑ ጀግና ነው ። አንድን ሰው ይበልጥ ጀግና የሚያስብለው ብቻውን በመታገል ሳይሆን ከጎኑ ብዙ የሱን አይነት ጀግኖችን በማሰለፍ ነውና ጓድ ሽባባውም በእሳት የተፈተኑ እንደ ተሞረደ አልማዝ የሚያብለጨልጩ በርካታ ቁጥር ያላቸው አርበኛ ታጋዮችን ከጎኑ አስልፏል ምንም ቢመጣ ከአላማቸው ንቅንቅ የማይሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው።
አርበኛ ታጋይ ሽባባው ጌታሁን ለሰው ልጅ የሚሰጠውን የመጨረሻ የህይወት ዋጋ በበርሃ እየሳቀና እየተደሰተ በተወለደ በ58 ዓመቱ በደረሰበት ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከዚህ አለም በሞት ተለይቶአል ። የጓዳችን ሞት መሪርና ከባድ ያደረገው እድሜ ልኩን የተነሳለት የኢትዮጵያን ህዝብ የስልጣን ባለቤት የማደረግ ፣ዜጎች በሃገራቸው እንደ ዜጋ መቆጠር እንዲችሉ ፣ኢትዮጵያ ከውርደትና ከውድቀት ወጥታ ወደ ነበረችበት የክብር ማማ ተመልሳ ማየትና የመሳሰሉት ሲሆኑ አሁን ትግሉ ጫፍ ደርሶ ነገሮች በተሳካ መልኩ በሚጓዙበት ወቅትና በድል በሚጠናቀቅበት ስዓት ለትንሽ በሞት መቀደሙ ነው ያበሳጨንና ሀዘናችንን መሪር ያደረገው።ይቺ ቀን ለመላው የነጻነት ታጋይና ለአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት የከፋች ናት። ምክንያቱም የወጣት ታጋዮች መምህር፣የዲያስፖራው ኩራትና መሪ የሆነው አርበኛ ታጋይ ሽባባው ጌታሁንን አሳጥታናለች። ጓዳችን ዛሬ ከጎናችን ብትለይም የተነሳህበትን አላማ ከግብ እንደምናደርስ ግን በእርግጠኝነት እንናገራለን ። ነብስህ ፈጣሪ አጸደ በገነት ያኑርልን እያልን የአርበኞች ግንቦት 7 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለጓድ ሽባባው ጌታሁን ለቤተሰቦቹና ለትግል ጓዶቹ ፣በሀገር ውስጥና በውጭ ላላችሁ ወገኖቻችን መጽናናትን እንመኛለን።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ !
አንድነት ሀይል ነው !
የአርበኞች ግንቦት 7 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

No comments:

Post a Comment

wanted officials