Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, June 4, 2018

በሀዋሳ እና ወልቂጤ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ


 በደቡብ ክልል ሀዋሳ እና ወልቂጤ ከተሞች በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ።
በሃዋሳ እና ወልቂጤ ከተሞች  ግጭቶች ተከስተዉ በርካታ ሰዎች ተጎድተዋል።
በሁለቱም ከተሞች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎም ሰዎች መገደላቸው እየተነገረ ነው።
በሃዋሳ የሚከበረው የሲዳማ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨንበላላ በአል ሲከበር በከተማዋ ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሰው ተገኝቶ ነበር።
ይሕንኑ የዘመን መለወጫ በአልን ምክንያት በማድረግ የተሰበሰበው ሕዝብ የሲዳማ  ዞን በክልልነት እንዲዋቀር የሚጠይቅ መፈክር ሲያሰማ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
የሲዳማ ዞን ዋና ከተማው ሀዋሳ ሆኖ በክልልነት ካልተዋቀረ ሰላም አይኖርም ሲሉ የሚዝቱ እና በሌሎች ብሄረሰቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ እንደነበርም ነው የተገለጸው።
ለግጭቱ መባባስ ምክንያት የሆነውም ሐዋሳ ከተማን በመለየት ቀሪው የሲዳማ ዞን ክልል ሊሆን ነው መባሉን ተክትሎ እንደሆነም ተነግሯል።
የደቡብ ክልል ፖሊስ እንደገለጸውም በበአሉ ምክንያት ቁጥሩ ከፍያለውን ሕዝብ ታሳቢ በማድረግ ሁከት ለመቀስቀስ ያለሙ አካላት ግጭት ፈጥረው በርካታ ሰዎች እና ንብረት ተጎድቷል።
ቁጥሩ በውል ባይታወቅም ሰዎች መገደላቸውንም የአይን እማኞች ይናገራሉ።
በበርካታ የሕክምና ተቋማትም  በርካታ ቁስለኞች መኖራቸው ታውቋል።
በሀዋሳ ከተማ ስርአት አልበኝነት ነግሶ ሱቆችና የንግድ መደብሮችን ለመዝረፍ ሙከራ ሲደረግ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
ይሕም ሆኖ ግን በተፈጠረዉ ግጭት የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ከማጋጠሙ ባለፈ በሰዉ ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የደቡብ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መናገራቸውን ፋና ብሮድካስቲግ ዘግቧል።
በሌላ በኩል በወልቂጤ ከተማ የቀቤና ብሔረሰብ አባላት ጉራጌዎች ይውጡ በሚል በተፈጠረ ግጭት ሰዎች መገደላቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ወደ ወልቂጤ ከተማ መከላከያ ሰራዊት እየገባ መሆኑ ነው የተነገረው።
ታዛቢዎች እንደሚሉት በሀገሪቱ እየተከሰተ ባለው ለውጥ ያልተደሰቱ ሕወሃቶች በደኢህዴን ካድሬዎች በኩል የጉራጌን ሕዝብ በመከፋፈል እና የብሔር ግጭት እንዲነሳ በማድረግ በሀገሪቱ ሰላም እንዳይኖር እየሰሩ ይገኛሉ።

No comments:

Post a Comment

wanted officials