Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, March 18, 2017

Ethiopian church donates 200 Thausend Birr for the cictms of pits Landslide





ቋሚ ሲኖዶስ: በቆሻሻ ክምር ናዳ ለሞቱት ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ አዘዘ፤ የብር 200ሺሕ ድጋፍ አደረገ

በመላ አድባራትና ገዳማት፣ የሰባት ቀናት ጸሎተ ፍትሐት ይካሔዳል፤
ለተጎጂ ቤተ ሰዎች፣ የብር 200 ሺሕ ጊዜአዊ የገንዘብ ድጋፍ ይደረጋል፤
ተጎጅዎችን በዘላቂ ለማቋቋም፣ ለምእመናንና ገባሬ ሠናያት ጥሪ ቀረበ፤


*                *               *

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት፣ በአዲስ አበባ፣ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፣ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ የቆሻሻ ክምር ተንዶ በደረሰው አደጋ ሕይወታቸውን ላጡና ለተጎዱ ወገኖች ሐዘኗን ገለጸች፤ ላለፉት ምሕረትን፣ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጣቸው ተመኘች፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ ባካሔደው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ “በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ቤተ ክርስቲያናችን ሐዘኗን ትገልጻለች፤ የሞቱትን ነፍስ ይማርልን፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይስጥልን፤”  በማለት፣ ጸሎተ ፍትሐትና የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግትእዛዝና ውሳኔ ማሳለፉን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ከቀትር በፊት ለብዙኃን መገናኛ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በመኾኑም፣ በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖችን በማሰብ፣ ከነገ መጋቢት 7 እስከ 14 ቀን፣ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት፣ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ ቋሚ ሲኖዶሱ ማዘዙን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም፣ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተጎዱ ወገኖች መጽናናትን በመመኘት፣ ለጊዜው የብር 200 ሺሕ የማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲደረግ መወሰኑን ቅዱስነታቸው በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
የገንዘብ ድጋፉ፣ አብነት ለመኾን ያኽል የተለገሰ እንደኾነ፣ ለኢ.ኦ.ተ.ቤን – ቴቪ የተናገሩት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ምእመናንና ገባሬ ሠናይ አካላት፣ ተጎጅዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በሚያስፈልገው ኹሉ እንዲያግዙ ጥሪአቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የነፍስ አድን ጥረቱ እስከ ዛሬ የቀጠለ ሲኾን፣ በአብዛኛው ሴቶችና ሕፃናት
 የሚገኙበት የሟች ወገኖች ቁጥር 72 መድረሱ ተዘግቧል፤ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤትም፣ ከዛሬ መጋቢት 6 ቀን ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን መታወጁ ይታወቃል፡
በሌላ በኩል፣ በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዙሪያ፣ መጋቢት 1 ቀን ተቀስቅሶ የነበረውን እሳት ለማጥፋትና ለመከላከል እስከ ሕይወት መሥዋዕት የተረባረቡ ምእመናንንና በጎ ፈቃደኞችን ቤተ ክርስቲያን እንደምታመሰግናቸው ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ጽ/ቤቱና ሀገረ ስብከቱ፣ በየጊዜው በገዳሙ ዙሪያ የሚነሣውን ቃጠሎ መንሥኤ በትብብር በማጥናት ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት በጋራ እየሠሩ እንዳለም፣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል – ከቋሚ ሲኖዶሱ ጋዜጣዊ መግለጫ በኋላ ከኢ.ኦ.ተ.ቤን – ቴቪ ለተጠየቁት በሰጡት ምላሽ፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials