Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, March 22, 2017

House demolition vs Churches destroying in Addisababa



አዲሱ የቤተክርስቲያንና የምዕመናን መፈተኛ መድረክ ይሄ በልማት ስም የሚከናወን የቤት ማፍረስ ሒደት ነው፡፡
በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ምዕመናን ከተወለዱበት አጥቢያ አፈናቅሎ ለሁለትና ለሦስት ባለሀብት ያንን ቦታ እየሰጡ አጥቢያዊውን ያለ ምዕመን ማስቀረት የቤተክርስቲያናችን አዲሱ ፈተና ነው፡፡
ቤተክርስቲያንን ያለ ምዕመናን … ምዕመናንም ያለ ቤተክርስቲያን ማሰብ ሊሆን የማይችል ነው፡፡
አንዱን ከአንዱ ነጥሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡የቤተክርስቲያን መኖር ለምዕመናን እንዲቆርቡ ፣ እንዲጠመቁ (ዳግም ከውሃና ከመንፈስ እንዲወለዱ)፣ አበ ነፍስ አግኝተው እንዲፅናኑ ፣ ስለ ነፍሳቸው መዳን እንዲያስቡ ፣ በምክረ አበው ኑሯቸውን የተቃና እንዲያደርጉ ፣ በየሰንበቴው በየማኅበሩ እየተገናኙ ስለ ክርስቲያናዊ ሕይወታቸው መበልፀግ እንዲወያዩ ነው፡፡
መልሶ ማልማቱ ብዙዎችን ከሚወዱት ከተወለዱበት ክርስትና ከተነሱበት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ትተው እንዲሄዱ ግድ የሚል ነው፡፡
በመናፍቃን የተሰነዘረውን የፈተና ቀስት ደገኛ በሆነ ትምህርቷ ቤተክርስቲያናችን መለሰችው፡፡
በአላዊያን ነገሥታት የተሰነዘረውን የሃይማኖታችሁን ለውጡ ፈተና ሰማዕትነትን ለመቀበል በቆረጡ ልጆቿ፣ ሰማዕትነት አያምልጣችሁ በሚሉ ልጆቿና እነርሱን ባፀናቸው መንፈስ ቅዱስ ተሻገረችው፡፡
ይሄን የመልሶ ማልማት ፈተናን መሻገሯም አይቀርም ፡፡
አብያተ ክርስቲያናት የዚህን ችግር ገፈት መቅመስ ከጀመሩ ቀላል የማይባሉ ዓመታት ተቆጥረዋል ፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ
ቅዱስ ራጉኤል ቤ/ክ
አፍሪካ ሕብረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ
ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤ/ክ
ታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም
መካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ
መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ፈተናው ፈትኗቸዋል፡፡
አዲስ አበባ ደሃ አይኑርብሽ የተባለች ይመስል ነገ ከነገ ወዲያ ፎቅ ለመስራት በሚተጉ ግለሰቦች አማካኝነት አዲሱን የቤተክርስቲያኒቱን ፈተና የሚቋደሱ አብያተ ክርስቲያናት በቁጥር መላቃቸው አይቀርም፡፡
የዛ ሁሉ እናቶች ዕንባ ግን ወዴት ይሆን መሰወሪያው?
በልማት ሰም ከከተማ መሐል አውጥተው ካሰፈሯቸው በኋላ ምዕመኑ ቤተከርስቲያንን ሲያቋቁም ግብረ ኃይል ልከው ያስፈርሱታል ፡፡
የተወለዱበትን ቤተክርስቲያንን ነጥቆ ቤተክርስቲያንን አትገነቡም ማለት እውን መልሶ ማልማት ይሆን ? ለምዕመናን ትልቁ ፈተና ባሉበት ቦታ ሆነው ስንዱዋን ፣ ምስጢር አከናዋኟን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ያለማግኘት ነው፡፡
የአንድ ወዳጄ አባት ሰሞኑን ቤታቸው በልማት ስም ይፈርሳል፡፡ እኚህ አባት ቅዱስ ቂርቆስን በጣም ነው የሚወዱት ለሰማዕቱ ፍቅራቸው በቃል ከሚገለፀው በላይ ነው፡፡ቡልጋሪያ ከሚገኘው ቤታቸው አጠገብ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ እያለ እሳቸው ግን በሌሊትም ይሁን በቀን ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ ነው የሚመጡት፡፡ ሰሞኑን ቤታቸው እንደሚፈርስ እውን ሲሆን እንዲህ አሉ፡-
"አይቻለኝም እንጂ ቂርቆስዬ ይዤው ብሔድ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የማይሆን ነገር ሆነብኝ፡፡"
የእኛ ሀገር ልማት ይሄ ነው ከሚወዱት ቤተክርስቲያን ከሚወዱት ሰማዕት የሚለይ ነው፡፡በዚህ መልሶ ማልማት/ምን መልሶ ማልማት ነው አፍርሶ ማጠር ነው እንጂ/ የተነሣ ከቀላል እስከ ከባድ ችግሮች አብያተ ክርስቲያናት ላይ ይደርሳል፡፡
 የሰርክ ጉባዔ ይቀዘቅዛል
 በሰንበትም ሆነ በአዘቦት ቅዳሴ የሚያስቀድሰው ምዕመን ቁጥር ይቀንሳል
 ማህሌቱም ይቀዘቅዛል
 ባለ ራዕይ ምዕመናን ባለመኖራቸው የተነሳ ቤተከርስቲያን በልማት ትጎዳለች
 ካህናት አባቶችን እንደወትሮው የሚጎበኛቸው ይጠፋል
 ሰንብት ት/ቤትች ይፈታሉ
ይሄ ፕሮግራም ከብዙ ፈተና የተረፈችውን ቤ/ክ በአዲስ የፈተና መድረክ የሚገልጣት ነው፡፡
ቤተክርስቲያን ሆይ እግዚአብሔር ያፅናናሽ፡፡
ዲያቆን ጸገየ ኃይለሚካኤል
19/07/09 ዓ.ም
አዲስ አበባ
Image may contain: text and outdoor

No comments:

Post a Comment

wanted officials