ኢትዮጵያዊነት ምንነት መግለጫ እና ለምን በኢትዮጵያዊነታችን መኩራት እንደሚገባን
ክፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ የጽፈት ጠረጴዛ
ኢትዮጵያዊ መሆን እጅግ የሚያኮራ ነገር መሆኑን ባለመገንዘባችን እና “አትዮጵያ” የሚለውን ቃል ትክክለኛ ፍቺ ባለማወቃችን፣ አንዳንዶቻችን በኢትዮጵያዊነታችን አናፍራለን።
“ኢትዮጵያዊነት” ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት የቃሉን ትርጉም ምንጭ ማወቅ ግድ ይላል፡፡
“ኢትዮጵያ” ማለት ቢጫ ወርቅ ስጦታ (ለእግዚአብሄር ማለት) ነው፡፡ ይህ ስም የተሰጠው ለኢትዮጵያ መስራችና የኢትዮጵያውያን አባት ለሆነው ለ ኢትዮጵ ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ወርዶ፣ ወርዶ ወደ እኛ የደረሰው ከሱ ስም ነው ማለት ነው፡፡ “ኢትዮጵያዊ” ማለት በግሪክ ቋንቋ የተቃጠለ ፊት ነው የተባለው ነጭ ውሸት ነው። በግሪክ መዝገበ ቃላት ውስጥ እንደዚህ የሚል ቃል የለም።
ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸው፣ ከፍ ሲል ኢትዮጵያን በስሙ ካስጠራው ከካህኑና ከንጉሠነገሥቱ ከኢትዮጵ፣ ዝቅ ሲል የሱ ዘር ከሆነው ከነቢዩና ከፈላስፋው ከደሸት መውረዳቸ ነው፡፡ ኢትዮጵ የዛሬ 4000 ሺ ዐመት አካባቢ ዐስር ወንዶች ልጆች ወልዶ ነበር፡፡ ስማቸውም እንደሚከተለው ነው፡፡--
አቲባ፣ ቢኦር፣ ተምና፣ አቴር፣ አሻን፣ አክሲብ፣ በሪሳ፣ ቴስቢ፣ ቶላ እና አዜብ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ስሞች ውስጥ አሻን፣ በሪሳ፣ ቶላ እና አዜብ አሁንም ድረስኢትዮጵያ ውስጥ አሉ።
የኢትዮጵ ዘር፣ የነቢዩ ደሸት ልጆች ደግሞ መደባይ፣ መንዲ፣ ጂማ እና ማጂ ይባሉ ነበር፡፡ ማጂ ማራ (አማራ) ን እና ጀማን ወለደ፡፡ ሰዎቹ የተሰየሙት የዛሬ 3600 ዐመት ቢሆንም፣ እነዚህ ስሞች አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡
የኢትዮጵ 10 እና የደሸት 4 ልጆች ተባዝተው ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የአሉት ሰዎች በሞላ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያና በመላው ዐለም ባሉት ትውልደ ኢትዮጵያውያን የደም ስሮች ውስጥ የኢትዮጵ እና የደሸት ደም ይዘዋወራል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በሞላ ምንጫቸው አንድ እና አንድ ነው፡፡ ስለዚህም ቋንቋቸው ቢለያይም ደምና ዘራቸው አንድ ነው፡፡ ቋንቋ ደግሞ የመግባቢያ መሳሪያ እንጂ ዘርን አመላካች ወይም የዘር ክፍል አይደለም፡፡ ቋንቋ ማለት ጎሳ ማለት ነው፡፡
ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ጎስአ(ጎሳ) ልብየ ሰናይ ይላል፡፡ ልቤ መልካም ተናገረ፣ ማለት ነው፡፡ አገሳ ወይም ከውስጥ አወጣ፣ የተሰኘውም ቃል ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ጎሳ ማለት አንድ ዐይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ነው፡፡ ዘር ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ አባትና እናት ወደ ፈረንሳይ ሃገር ሄደው ልጅ ቢወልዱና ፈረንሳይኛ ቢናገር፣ ከዛም ወደ አሜሪካን አገር ተጉዘው ሌላ ልጅ ወልደው እንግሊዝኛ ቢናገር፣ ልጆቻቸው ሁለት የተለያዩ ቋንቋዎች ስለተናገሩ ወንድማማችነታቸው አይፋቅም፡፡ ወላጆቹም አማርኛ፣ ኦሮምኛ ወይም አፋርኛ በመናገራቸው ወላጅነታቸው አይደመሰስም፡፡ ደምና ዘራቸው አንድ ናውና፡፡ ስለዚሀ ወሳኙ ቋንቋ ሳይሆን ደምና ዘር ነው፡፡ ስለዚህ ቋንቋ ወይም ጎሳ ወሳኝ አይደለም፡፡ መግባቢያ ነው እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ከ 80 በላይ ቋንቋዎች የሚናገሩ ጎሳዎች አሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ ጎሳዎች በቋንቋ ቢለያዩም በደማቸው አንድ የኢትዮጵ ልጆች ናቸው፡፡ የሚያገናኛቸውም ኢተዮጵያን በስሙ ያስጠራው ኢትዮጵ አባታቸው ነው፡፡
ክ 200 ዐመታት በፊት መላው አፍሪካ ኢትዮጵያ ይባል ነበር። የእዚህ ምክንያቱ የኢትዮጵ ተወላጆች በመላው አፍሪካ ተሰራጭተው፣ አፍሪካን አሰልጥነው ስለኖሩበት ነው። የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን በቅኝ መግዛት ከጀመሩ ወዲህ ግን ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ቀርቶ አህጉሩ አፍሪስካውያን በተባሉት አፋሮች አፍሪካ መባል ጀመረ። አሁንም ድረስ ስሙ ክእኛው ስለ አልወጣ ቅር አንሰኝም።
እንድ ኢትዮጵያዊ ውስጥ የተወለደ ወይም ትውልደ-ኢትዮጵየዊ ሰው በሁለት ምክንያቶች ኢትዮጵያዊ ይሆናል። አንደኛ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለዱ። ሁለተኛ፣ ትውልደ-ኢትዮጵያዊ በመሆኑ። ሁለቱንም የሚያገናኛቸው በደምና በዘራችው ክኢትዮጵ መውረዳቸው ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት በዐለም ልዩ የሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ዮጵ የተባለ ቢጫና ብርቅዬ ወርቅነት ማለት ነው። ክዚህም በላይ፣ ለዐለሙ ፈጣሪ ለእግዚአብሄር ብቻ የሚቀርብ ልዩ ገጰበረከት ማለት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የህይወት ምንጭነት፣ የሰብእና መገኛ ስፍራ ማለት ነው።
ኢትየጰያዊነት ማለት የስነመለኮት ክፍታ፣ የስልጣኔ መጀመሪያ፣ የሰው ዘር አርአያ፣ የስነምግባር ልእልና ማለት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የህርነት፣ የጀግንነት እና የፍትሀዊነት ተምሳሌነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የእኩልነትና የሰው ልጅ ክቡርነት አርማ ነው።
እትዮጵያዊነት ማለት የታማኝነት እና የተአማኒነት እንዲሁም የመለኮት ማህደርነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የፅናትና የብርታት እና የትእግስትና የዘላቂነት ምልክት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የሀቀኝነትና የእውነተኛነት ምሳሌ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የርህራሄና የችርነት ናሙናነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት ሰው አክባሪነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ይሉኝተኝነት እና አዙሮ ተመልካቸነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት የጥበበኝነት ቁንጮ፣ የብልህነት እራስ ማለት ነው።
ኢትዮጵያዊነትማለት የቅድስና እና የብጱእነት ጫፍ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት የወንድማማችነትና የእህትማማችነት፣ የመትዛዘን ማማነት ነው።
ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሞላ በሚክተሉት ምክንያቶች በኢትዮጵያዊነታቸው ሊኮሩ ይገባል። የኩራቶቹን ሁሉ ምክንያቶች ለመዘርዘር ጊዜ ስለሚፈጅ ጥቂቶቹ ብቻ ይቀርባሉ።
1 ኢትዮጵያ በሳይንስም ሆነ በመፅሃፍ ቅዱስ የሰው ዘር መገኛ በመሆኗ፣
2 ክ 4500 ዐመታት በፊት በንጉሥ ስብታህ አማካኝነት የጋዜጣን እና የፖሊስን ሥራ ከዐለም ቀድማ ኢትዮጵያ በማቋቋሟ፣
3 በዐለም ላይ የሌለ ከኖህ ጀምሮ ስሞቻቸውና የነገሡበት አዝማናት የተመዘገበ ነገሥታት በመኖራቸው፣
4 አባችን ኢዮጵ እና ሚስቱ እናታችን ሲና እንቁዮጵግዮን መሲሁ እየሱስ ሲወለድ ልጆቻችው ወደ እስራኤል ተጉዘው ገዳ እንዲያበረክቱለት በእግዚአቤሄር ትአዛዝ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ መምጣታችው እና ጣና ጎጃም ላይ በተልእኮ በመስፈራቸው፣
5 የኢትዮጵና የእንቁዮጳግዮን ልጆች ታላላቅ ነገሥታት ሆነው በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅና እስያ በመንሰራፋታቸው፣ ስልጣኔአቸውን በማሰራጨታቸው እና መላውን አፍሪካ ኢትዮጵያ በማሰኘታቸው፣
6 አጼ እስያኤል እስያን አሰልጥኖ በስሙ አህጉሩን እስያ በ ማስኝቱ፣ እጽዋትን እና እንስሳትን አዳቅሎ አዲስ ውጤት ያስገኘው በዐለም የመጀመሪያው ጄኔቲክ ኢንጂኔር በመሆኑ፣ ክ3000 ዐመታት በፊት ይኽው ትልቅ ስው ምናልባት በዕለም የመጀመሪያ የሆነውን ሰንደቅአላማችንን በመፈልሰፉ፣
7 በንግሥተ ሳባ ተልቅነት--- ኢትያኤል የተባለች የሳባ ንግሥት በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰች፣ የዐለሙ ፈጣሪ እየሱስ ክርስቶስ ስሟን ጠርቶ፣ የንጉሥ ሰለሞንን ጥበበኝነት ለመፈተን ኢየሩሳሌምን መጎብኝቷን የመሰከረላት ትልቅ ሰው በመሆኗ፣
8 በአፋሮች ትልቅነት---አፍሪካ በአፋሮች አፍሪካ ስለተባለች። ከ 3000 ዘመናት በፊት አፋሮች ታላቅ መርከብ ገንቢዎችና መርክቦኞች እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅና በእስራኤል ስመጥር የኦፊር ወርቅ ነጋዴዎች ከመሆናቸውም በላይ ተጽእኖ አሳዳሪዎች በመሆናቸው፣
9 የኢትዮጵ ዝርያዎች 12 ጠበብት ነገሥታት ሆነው እሴራኤሎች ሳያውቁ የመሲሁን መወለድ ተረድተው፣ ፣ ከኢትዮጵያ ተነስተው በኮከብ እየተመሩ ቤተልሄም ደርሰው ለመሲሁ ለእየሱስ ክርስቶስ ገዳ በማቅረባቸው፣
10 በዐለም ላይ ከአሉት ነገሮች ሁሉ በጣም ውድ እና ብርቅ የሆነው የታቦቱ ማረፊያ እና መኖርያ አድርጎ እግዚአብሄር ከእስራኤል ይልቅ ኢትዮጵያን በመምረጡ፣
11 ኢትዮጵያ በዳዊት መዝሙርና በሌሎችም መጽሃፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ በእግዚአብሄር በመጠራትዋ፣
12 ከእግዚአብሄር በታች ኢትዮጵያ አይሁዳውያንን በእግራችው ስለማቆሟቸው፣ ከነብዩ ከሙሴ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ አይሁዳውያንን ወደ ግዛትዋ እያስገባች ጥገኝነት፣ መሬት እና ንግሥና ሳይቀር እየሰጠቸ አስተናግዳለች። በሌላ ሃገራት ግን እስራኤላውያንን ያሳድድዋቸው፣ እንዲሁም ይገድሏቸው ነበር። በእኛ በጎ አድራጊነት እንኮራለን። ክዚህ በተጨማሪ፣ እሴራኤላውያን በባርነት በባቢሎን 70 ዐመት ሲሰቃዩ ቆይተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተመቅደሳቸውን ካደሱ በሁዋላ መጻህፍት አጡ። መጽሃፍ ቅዱስን እና ሌሎች ብርቅዬ መጻህፍትን ኢትዮጵያ ስለላከችላቸው እንታበያልን።
13 ትልቅ ለሚባለው ለሙሴ ጥገኝነት እና ሚስት ኢትዮጵያ ሰጥታ የፍትህን እና የሕግ አስተዳደርን እንዲሁም ነገረመለኮትን ስለአስተማረችው፣
14 ኢትዮጵያ በርካታ የሴት ነገሥታትን በኢትዮጵያ እና በግዛቶቿ ላይ ሾማ የሴቶችን መብት በማስከበር በዐለም ግንባር ቀደም በመሆኗ፣
15 ኢትዮጵያ ክጣና ሃይቅ ተነስታ ወደ ኑብያ እና ገብጽ ወርዳ የግብጽን እና ኑብያን ስልጣኔ በመፍጠርዋ፣ ሕልቆመሳፍርት ፈርኦኖችን እና ህንድኬ በሚል ማእረግ 17 የሴት ነገሥታትን ብግብጽ፣ ብሊብያ እና ኑብያ ላይ በመሾሟ፣
16 አጼ አክሱማይ የዐለም አባት፣ የነገሥታት አራስ ተብሎ ከባቢሎን ሳይቀር በንጉሦች የተበደሉ ዜጎቹ ለአቤቱታ ወደ እሱ ሲመጡ እምባቸውን ስለአበሰላቸው፣
17 እየሱስ ክርስቶስ፣ ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ዮሴፍ በኢትዮጵያ ግዛት በግብጽ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ጥገኝነት አግኝተው በመኖራቸው፣
18 እየሱስ ራሱን ለዐይሁዳውያን ሳይገልጽ በ22 ዕድሜው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለኛ ቅድሚያ ሰጥቶ ራሱን ለኛ ገልጾ እስከ 25 ዕድሜው ድረስ ሲያስተምርና ሲፈውስ ሃገራችን ውስጥ በመኖሩ፣
19 እየሱስ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ ሲል ግብጽ ሳለ ጥገኝነት የሰጠውን ንጉሥ አማናቱ ተትናይን እግረመንገዱን ጎብኝቶ ለአንድ ሳምንት እሱ እልፍኝ ውስጥ ሰንብቶ ነበር። እየሱስ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንደተሻገረ አልፍኙን ንጉሥ አማናቱ ተትናይ ቤተክርስትያን አደረገው:። እየሱስ ክርስቶስ በህይወቱ እየአለ እኛ በዐለም የመጀመሪየውን ቤተክርስቲያን በመመስረታችን፣
20 የንግሥት ሕንደኬ ዣን በጅሮንድ በቅዱስ ፊሊፖስ መጠመቁና እሱ ክርስትያን ከአውሮፓውያን ቀድሞ ክርስትናን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባቱ፣
21 አውሮፓውያን ወደ ክርስትና የተሽጋገሩት ክ አረማዊነት ሲሆን ኢትዮጵያውያን ግን ክኦሪት ሃይማኖት ነው። ይህ በመሆኑም የክርስትና እውቀታችንን ከአውሮፓውያን ለማጥለቅና ለማበልጸግ አስችሎናል። በእዚህም እንኮራለን።
22 እየሱስ ክርስቶስ፣ ኢትዮጵያውያን ውስጣቸው የኖርኩ ዘመዶቼ ናችው፣ በእኔ ያምናሉ፣ እናንተ እነሱን ለማሳመን ሳትደክሙ አጥምቃችሁ አቁርቡአቸው፣ ብሎ ደቀመዛሙርቱን በርጠለሚዎስን፣ ማቴዎስን፣ ቶማስን ናትናኤልን፣ እንድርያስን እና ማርቆስን ወደ ኢትዮጵያ ልኳቸው፣ ክሃዋርያቱ ግማሾቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስለአስተማሩ በእግዚአብሄር እንደተከበርን ስለሚሰማን፣
23 ኢትዮጵያውያን ክርስትያናት እና አይሁዳውያን ያለደም መፋሰስ ተስማምተው የኦሪትን እና የክርስትናን አምልኮ ስርዐቶች የሚተዉትን ትተው የተረፉትን ወደ ክርስትና በማሸጋገራቸው፣
24 ክኢትዮጵ እስክ አጼ እስያኤል ድረስ የኢትዮጵያ ነገሥታት ክእግዚአብሄር ጋራ በቀጥታ የሚነጋገሩ ሊቀካህናት መሆናቸውና በፈሪሃ እግዚአብሄር ህዝባቸውን በፍትህ እና ርትህ በማስተዳደራቸው እና ይህ ክስተት በዐለም ላይ የሌለ በመሆኑ፣
25 ነብዩ መሃመድ በችግር ላይ ሳለ ዘመዶቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ኢትዮጵያ ጥገኝነት ስለሰጠቻቸው፣ መሃመድ ራሱ ሙስሊም ከመሆኑ በፊት ኢትዮጵያ በመካና በመዲና ውስጥ የራስዋ ቤተክርስትያን ስለነበራት እና እሱ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ተጠቃሚና የሊቀካህናቱ ወዳጅ በመሆኑ፣ እንዲሁም በመጀመሪያ አላሁ አክበር ብሎ የጮኸው ድምጸ-መረዋው ኢትዮጵያዊው ቢላል ሃበሽ በመሆኑ፣ ነብዩም ኢትዮጵያውያን ላይ ጂሃድ አታኪያሂዱ በማለቱ፣
26 በ ኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ክርስትያኖቼ በሃይማኖት ልዩነቶች ካለመጋጨታቸውም በላይ ተፋቅረውና ተባብረው ቤተክርስትያኖች እና መስጊዶች አንዱ ለሌላው በመገንባታቸው፣ አብረው በመጸለያቸው እና ከተዋደዱ ያለብዙ ችግር መጋባት በመቻላቸው፣
27 በዐለም ላይ የሌሉ ብርቅዬ የሱባ እና የሳባ ፊደላትን ፈጥረው ስለአቆዩልን፣
28 እንደ አክሱም እና ላሊበላ ዐይነት ያልተለመዱ ቤተክርስትያናት መኖራቸው፣ ክነሱ የተገኘው ቅዱስ ያሬድ ልዩ ማህሌትን በመድረሱ እና ክአውሮፓውያን 700 ዐመታት አስቀድሞ የዜማ ምልክቶችን በመፈልፈሰፉ፣ እንዲሁም የማንንም ይማይመስል ቅዳሴ እና ስርዐተ ዐምልኮ ስለአለን፣
29 በቀለማችን እና በተክለሰውነታችን የተቅለመለምን አበቦች ከመሆናችንም በላይ የተለያዩ አልባሳት፣ ዳንኪራዎች እና ባህላዊ እሴቶች ስለአሉን፣
30 ከተለያዩ የምግብ አሠራር ሙያዎች በተጨማሪ ለዐለም ምግቦች የእበርክትናቸው እንደ ቡና አና ጤፍ የመሳስሉ አዝእርት ስለአሉን፣
31 ኢትዮጵያ፣ ባለፉት 4000 ዐመታት ጠላቶችዋን ሮማውያንን፣ ገብጾችን፣ አረቦችን እና ሌሎችንም በጦርነቶች ድባቅ እየመታች ነጻነታችንን እና ክብራችንን በማስጠበቋ እና ለዐለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነጻነት እና የድል አድራጊነት ዐርማ በመሆንዋ እንኮራለን።
32 በመጨረሻም እጅግ የሚያኮራን በእየሱስ ክርስቶስ የደም ስር ውስጥ የእኛ የኢትዮጵያውያን ደም መፍሰሱ ነው። እንዴት ቢሉ፣ እየሱስ ክርስቶስ የቅዱስ ዳዊት ዘር በመሆኑ እና የእሱም እናት አይሁዳውያን አዶልያ ወይም አዴል የሚሏት፣ እኛ ደግሞ ሀብሌ የምንላት ኢትዮጵያዊት በመሆኗ።
የሚያኮሩንን ሁሉ ነገሮች በእርግጥ ዘርዝረን አንጨርሳቸውም። ክብዙ በጥቂቱ አላይ የሰፈሩት ናቸው። አነሱን መስፈንጠሪያ ኢድርገን፣ ደረታችንን ነፍተን በኢትዮጵያዊነታችን ታብየን፣ እርስ በርሳችን ተከባብረን፣ ተፋቅረን እና ተቃቅፈን በእኩልነት ወደፊት እመር! እንላለን። የጥንት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ትልቅ ከነበሩ እኛም እነሱን አርአያ አድርገን ወደፊት ይበጥል ትልቅ የማንሆንበት ምክንያት የለም።
No comments:
Post a Comment