Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, November 10, 2017

አቶ በቀለ ገርባ የውሸት ፍርድ ለመከታተል ችሎት እንደማይቀርቡ ተናገሩ





(ቢቢኤን) የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ በከፍተኛው ፍርድ ቤት እየተካሔደ ያለውን የውሸት ፍርድ ለመከታተል ችሎት እንደማይቀርቡ ተናገሩ፡፡ አቶ በቀለ ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት ጥቅምት 28 ቀን 2010 በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት በቀረቡበት ሰዓት ነው፡፡ በኦፌኮ አመራሮች በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ፣ ከትላንት ጥቅምት 27 ቀን 2010 ጀምሮ የመከላከያ ምስክሮችን የማሰማት ቀጠሮ የነበረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ለጠሯቸው መከላከያ ምስክሮች መጥሪያ ባለመጻፉ፣ ችሎቱ ያለ ምንም ፋይዳ ተበትኖ ነበር፡፡



በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ የተዘረዘሩ ተከሳሾች ለመከላከያ ምስክርነት የጠሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እና ምክትላቸው ዶ/ር አብይ አህመድ፣ አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ እና የለገዳዲ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ናቸው፡፡ ተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አስመዝግበው የነበረ ሲሆን፣ በተያዘው ቀጠሮ መሰረትም ምስክሮቹ ትላንት ችሎት መቅረብ ነበረባቸው፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ ለመከላከያ ምስከሮቹ መጥሪያ አልጻፍኩም የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ አክሎም ‹‹ባለስልጣናቱ የመከላከያ ምስክር ሆነው የመቅረባቸው አስፈላጊነት ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለህዳር 6 ቀን 2010 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሰጠው ተጨማሪ ቀጠሮ አግባብ እንዳልሆነ የገለጹት ተከሳሾች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ የመከላከያ ምስክሮች ይቅረቡ አይቅረቡ በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የግድ ህዳር ስድስትን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፣ የተከሳሾችን አቤቱታ አጣጥሏል፡፡ የኦፌኮ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ እንዲህ ያለ ህገ ወጥ እና የውሸት ፍርድ ለመከታተል ፍርድ ቤት አልመጣም፡፡›› ሲሉ ችሎቱን ላስቻሉት ዳኞች ተናግረዋል፡፡ አክለውም ፍርድ ቤቱ ማንኛውንም ፍርድ ቢፈርድባቸው እንደሚቀበሉ ገልጸዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ይሔን ሲናገሩ ችሎቱ በተከሳሾች ህብረ ዜማ ድብልቅልቅ ብሎ እንደነበር በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለቢቢኤን ተናግረዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ30 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ውሳኔ አስተላልፎላቸው የነበረ ሲሆን፣ ሆኖም ውሳኔው በ24 ሰዓት ውስጥ ተለውጦ ከእስር እንዳይወጡ መደረጋቸው አይዘነጋም፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials