በአማራ ክልል ቻግኒ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች በፖሊስና በአካባቢው የሚሊሻ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት ሰነዘሩ
በደቡብ ጎንደር ደጎማም ዛሬ ክፍተኛ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል።
በሀዋሳና በአዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች የትግል ጥሪ ወረቀቶች መበተናቸው ታውቋል።
በአዊ ዞን ቻግኒ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በፖሊስና በአካባቢው ሚሊሻ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ነው የታወቀው።
ትናንት ልዩ ስሙ ፎረንቅ በተባለው ስፍራ ከምሽቱ 3 ፡20 ሲሆን በአካባቢው ሲዘዋወሩ በነበሩ የፖሊስና የሚሊሻ አባላት ላይ ጥቃት ተከፍቶ ሁለት ታጣቂዎች በቀስት የተመቱ ሲሆን አንደኛው በቻግኒ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት ሌላኛው ታጣቂ ጉዳቱ ከባድ በመሆኑ ወደ ባህርዳር ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዱ ታውቋል።
ከጥቃቱ በኋላ በአካባቢው ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ እንደተሰማ የጠቀሱት የአይን እማኞች ተጨማሪ ሃይል በመግባት ጥቃት አድራሾቹን እያሰሰ እንደሆነም ገልጸዋል።
በሌላ በኩልም በደቡብ ጎንደር ደጎማ ዛሬ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበረ መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በከተማዋ የተበተነውን የትግል ቅስቀሳ ጥሪ ወረቀት ለመሰብሰብ የተሰማራው የመንግስት ታጣቂ ቡድን ህዝቡን ለማስፈራራት የተኩስ ሩምታ የከፈተ ሲሆን በዕለቱ በሚከበረው የንግስ በዓል ታዳሚዎች ላይ ከፍተኛ መረበሽ መፍጠሩን ምንጮች ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የትግል ጥሪ ወረቀቶች ሰሞኑን ሲበተኑ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።
በአዲስ አበባና በሀዋሳ ከተሞች በተመረጡ አደባባዮች በተበተኑት በዚሁ ወረቀቶች በዘርና በሃይማኖት አንከፋፋልም፣ነጻነት የሚፈልግ ዜጋ ህዝባዊውን ትግል በአስቸኳይ ይቀላቀል፣የወያኔን ስርዓት ለመገርሰስ ተነስተናል የሚሉ መልዕክቶች መሰራጨታቸው ተገልጿል።
No comments:
Post a Comment