Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, November 3, 2017

የኢትዮጵያውያን ዳግም አንድነት (Re-Unification of Ethiopians)Nuti tokko addaan hinbaanu

የኢትዮጵያውያን ዳግም አንድነት (Re-Unification of Ethiopians)
#AMHARA+#OROMO+___+___
(Nuti tokko addaan hinbaanu-አንድ ነን አንለያይም!)
==================================
አባ ገዳዎች አባይን ተሻግረዋል፡፡ አንድነት ለአማራና ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም ለዓለም ህዝብ ፈዋሽ መድሃኒት ነው፡፡ አንዱ የአንዱን ቁስል ሲጠረፍት፣ አንዱ የአንዱን አጥንት ሲቆፍር፣ እንደ አለት የከበዱ ሃገራዊ ችግሮችን ተሸክመን አብዛኛው ጊዜያችን የሚያልፈው በመናከስ ነው፡፡ ምዕራባውያን ወደ ውህደተ ዓለም (ግሎባላይዜሽን) እየተንደረደሩ እኛ በየቀኑ ድንበር ስንምስ፣ ድልድይ ስናፈርስ፣ አጥር ስንቀልስ እንውላለን፡፡ ልዩነት ይኖራል፡፡ አንድ ቤተሰብ ውስጥም ልዩነት ይኖራል፡፡ በልዩነት ተከባብሮ፣ አንድ የሚሆኑበት ነገር ላይ አብሮ መስራት ግን ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ልዕልናዋ ለመመለስ፤ ካልሆነም ቢያንስ በረሃብና በችግር የሚሰቃዩ ንፁሃን ዜጎችን ለመታደግ አይነተኛ መፍትሄ ነው፡፡
‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ›› እንዲሉ ከችግራችንና ከድህነታችን በላይ በተፈጠረው የዘረኝነት መንፈስ ንፁሃን ዜጎች ሁሌም በስጋት እንዲኖሩ ማድረግ እንደ ሰው ለሚያስብ ሰው ልብ ይሰብራል፡፡ እንግሊዞች ይጠቀሙበት የነበረውን ያረጀውና ያፈጀው የከፋፍለህ ግዛ (Divide and Rule) ስርዓት ለኢትዮጵያ እስካሁን ብዙ ዋጋ ቢያስከፍልም የመጭውን ዘመን ጨለማ ቀድሞ በማጤን ሻማ መለኮስ መቻል ትልቅ ብቃት እና መስዋትነት ይጠይቃል፡፡
በፌደራል ስርዓት ውስጥ የታቀፉ የግዛት አስተዳዳሪዎች (state Governors) በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እኩል የሆነ የመደራደር አቅም (equal political negotiation capacity) ከሌላቸው አቻ የሆነ የፖለቲካ ስነምህዳር (Balanced political environment) በፍፁም ሊፈጠር አይችልም፡፡ እንዲህ ባለው የፖለቲካ ስርዓት ደግሞ፣ አንዱ የቤት ልጅ አንዱ የእንጀራ ልጅ ሁኖ ይቀጥላል፡፡ አንዱ አስገዳጅ-ሌላው አጎብዳጂ፣ አንዱ ማማ-ሌላው ጫማ ሁኖ ይቀጥላል፡፡ ከጅምሩ የፌደራል ስርዓቱ መሰረት ቋንቋ በሆነባት ሃገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ችግሩ በጣም የጎላ ይሆናል፡፡
ሄዶ ሄዶ ግን ፍፃሜው አያምርም፡፡ የተገፋ፣ የተረገጠ፣ ሰብዓዊ እኩልነቱንና ነፃነቱን የተነፈገ ትውልድ ለአንድ ቀንም ቢሆን ነፃነቱን አውጆ ነፍሱን ይሰጣል፡፡ ሮናልድ ሬገን እንደሚለው ከሆነ ይህ ደግሞ ከ አንድ ትውልድ እድሜ በላይ አይሄድም፡ <<Freedom is never more than one generation away from extinction>>
ሰው እንደ ሰው እኩል ተከባብሮና ተቻችሎ የሚኖርባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው እንቅስቃሴ በግሌ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል መራሄ መንግስታት እያሳዩት ያለው ከፍ ያለ የመደራደር አቅምና የህዝብን ጥያቄ የመመለስ ሂደት ትልቅ ተምሳሌት ነው፡፡ በአማራ እና ሌሎችም ክልሎች መሰል ዘመኑን የዋጁና ከህዝብ ጎን የቆሙ መሪዎች እንደሚያስፈለጉ የተገለጠ ሃቅ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ አባ ገዳዎች እየተደረገ ያለው ጉብኝት አበረታችና አንድነትን ለማጠናር ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ወጣቶቹ መሪዎች ፍቅርና አንድነትን ብቻ ሳይሆን ድፍረትንም አስተምረው ይመጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ነገርግን ከዚህ ሁሉ ጀርባ አልፎ አልፎ የሚሸተኝ ተንኮል ያለ ይመስለኛል፡፡ ይህን የምለው የውሻ አፍንጫ ስላለኝ ወይም ሟርተኛ ስለሆንኩ አይደለም፡፡ ሰው ዛሬና ነገን ለመተንበይ ትናንትን ማጤን በቂ ባይሆንም መነሻ ይሆነዋል፡፡ ‹‹ አንዳንዴ የጣፈጠንን ነገር እንዳገኙ መብላት፣ ፍፃሜው በሽታ ሊሆን ይችላል››፡፡ ያም ሆነ ይህ ጉብኝቱ በብዙ ጥንቃቄ የሚደረግ መሆኑን ብረዳም፣ በጎጃም እና በጎንደር ህዝብ በኩል ጨዋነት የተሞላበት ተጨማሪ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ጠቁሜ ልመርሽ፡፡
ፍቅርና አንድነት ለኢትዮጵያ ህዝቦች!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
(Zelalem Tilahun)
Image may contain: bus, sky and outdoor
Image may contain: 8 people, people smiling, people standing and wedding

No comments:

Post a Comment

wanted officials