የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ምደባ አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር እየተጠቀመበት ያለውን አሰራር እንደማይቀበሉት አስታወቁ።
የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያ የአንድ ሀገር ህዝቦችን የሚነጣጥልና የፌደራሊዝም ስርአቱን የሚያበላሽ ነው ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳ ግጭት በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
አሁን ላይ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታትና ከቀያቸው የተፈናቀሉትን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው አዲስ መመሪያ ሌላ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።
መመሪያው የኦሮሞ ክልል ተወላጆች በሶማሌ ክልል፣የሶማሌ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች እንዳይመደቡ የሚያዝ ነው።
ይህንን መመሪያ ደግሞ የሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሀመድ ኡመር በፍጹም እንደማይቀበሉትና መመሪያውንም እንደማያምኑበት ነው ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት።
እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ የኦሮሞ ተማሪ ጅግጅጋ የራሱ ነው።የሶማሌው ተማሪም ኦሮሚያ ውስጥ ያለው መሬት የራሱ ነው።ይህንን ነው ልንነግራቸው የሚገባው።
የኦሮሚያ ክልል መንግስትም ቢሆን እንዲህ አይነቱን መለያየት የሚያምንበት አይመስለኝም ብለዋል።
የኦሮሚያ ተማሪዎች ከጅግጅጋ የሶማሌ ክልል ተማሪዎች ከኦሮሚያ ውጭ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች እንዲመደቡ የሚያዘውን መመሪያም አላምንበትም ሲሉ አስምረውበታል።
የሁለቱ ክልል ህዝቦችን በጠላትነት እንዲፈራረጁ ማድረግ የለብንም።–ስለ አንድነት ነው ልንነግራቸው የሚገባው።የአንድ ሀገር ህዝቦች መሆናችንን መዘንጋት የለብንም እንደ አቶ አብዲ አባባል።
መመሪያው የፌደራሊዝም ስርአቱንም ቢሆን የሚያበላሽ ነው ብለዋል።
አሁን በክልሉ መሻሻሎች አሉ ያሉት አቶ አብዲ ቀድሞውንም ቢሆን እንደዚህ አይነቱ ችግር መፈጠር አልነበረበትም ሲሉ ያክላሉ።
ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት መመለስ አለበት የሚሉት አቶ አብዲ ይህን ለማድረግ ደግሞ የተጀመሩ ጥረቶች አሉ።
የሶማሌ ክልልም የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው።
በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከአለም አቀፍ መመዘኛ በታች መሆናቸው እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ወቅት እንዲህ አይነቱን መመሪያ ማውጣትና የተማሪዎች ክፍፍልን መፍጠር ሌላ ጥያቄን ያጫረ ጉዳይ ሆኗል።
በሰው ሃይል፣በትምህርት አሰጣጥ፣በመሰረተ ልማት፣በተማሪዎቹ ብቃት በአጠቃላይ በሀገሪቱ በተደረገ ጥናት 30 ሺ 605 ትምህርት ቤቶች ከአለም አቀፍ መመዘኛ በታች ሆነዋል መባሉን ኢሳት በትላንት የዜና እወጃ ሰአቱ ማቅረቡ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment