Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, November 11, 2017

የአገራችንን ስም ከኢትዮጵያ ወደ ኩሽ የመለወጥ ዘመቻ – ተፈራ ድንበሩ



ይህ ጽሑፍ አቶ ሉሉ ከበደ ስለኦሮሞ ኅብረተሰብ በእግዚአብሔር እንጂ በጣኦት አለማምለክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኢትዮጵያ በኩሽ ተተክቶ እንዲጻፍ ከጀርመኖች ጋር በመተባበር ዋናውን ሥራ ከሠሩት ከዶክተር በንቲ ኦጁሉ ጋር የተደረገውን ቃለምልልስ በኢትዮመዲያ ድረገጽ ላይ እንዲወጣ ከተነበበው በመነሣት ነው።

ከቃለምልልሱ እንደሚታየው የኦሮሞ ኅብረተሰብ በጣኦት ሳይሆን በእግዚአብሔር (ዋቃ) ያመልክ ነበር ብሎ ባጭሩ የተቀመጠው የተሟላ ሆኖ አይታይም፤ ኦሮሞዎች አቴቴንና ማርያምን እየጠሩ ስለሚያመልኩት አምልኮ፣ በነአብርሃም ዘመን ዱር በመሄድ በዛፍ ሥር መስዋዕት የማቅረብ ባህል፣ እንዲሁም ረቢ የሚለውን ቃል የእግዚአብሔር መጠሪያ አድርገው ስለመጠቀማቸው እነዚህን የመሳሰሉት ከክርስትና ሃይማኖት ጋር ተዛምደው እንዲገለጹ ይጠበቃል። በእርግጥ ማንም ሰው እግዚአብሔርን በኅሊነው ሲያስብ ወደላይ ወደሰማይ እንደሚያይ የታወቀ ስለሆነ ይህ የኦሮሞ እምነት ብቻ እይደለም። ለአባብ(ዘንዶ) የሚደግን ግብር፣ ዛፍ ላይ ቅቤ የመቀባትን ባህል፣ በአንዳንድ ቦታዎዎች ቦረንቲቻ እየተባለ የሚጣል ሥጋና ደምን፣ያልተቀጠቀጠ በሬ (ኮርማ) አርዶ የመጣል ባህልን በተመለተ በጥናታቸው ውስጥ ተካቶ እንዲገለጽ ይጠበቃል። በተለይም ዶክተር በንቲ ተጨባጭ ጥናቶች አድርገው ከሆነ ብዙዎቻችን በአገራችን ብቻ ሳይሆን በብዙ ወደኋላ በቀሩ የዓለም ማህበረሰቦችም ውስጥ የማምለክ ሥነሥርዓቱ ተመሣሣይ ሆኖ የምናየውን ዛር ወይም ቃሉ(ቃልቻ) በተመለከተ በባለሙያዎች የተደገፈ ጥናት ስለማድረጋቸውተገልጾ አልታየም። ይህን መሰል ጥናቶችን ቢያካትቱ ስለኦሮሞ እምነት ያደረጉትን ጥናታዊ ሥነጽሑርፍ ተገቢነት ያሳይ ነበር።



ሆኖም፣ እነዶክተር በንቲ የሥነመለኮት ጥናት ሲያደርጉ በሥነመለኮት ላይ እንጂ ለብዙ ሺዎች ዓመታት በዓለም ዘንድ ሲታወቅ የነበረን የአገር ስም የሚያስቀይር የፖሊቲካ አባዜ ውስጥ ምን አገባቸው? ይህች ጠባብነት በሃይማኖት ሥር እየተሽለኮሎከች መግባቷ ካልሆነ። ይህማ ባይሆን እነዶክተር በንቲ የአገርንና የሕዝብን ክብር የሚነካ ነገር ውስጥ ገብተው የሕዝብን ሞራል የሚነካ ወይም እርስ በርሱ የሚያቃቅርና የሚያነታርክ መሣሪያ ለመሆን ማሰብ አልነበረባቸውም፤ ነገር ግን በጽንፈኛ ወይም የዘር ፖሊቲካ የተጨማለቀ ሰው ይሉኝታም ሆነ የሕዝብ ክብር ደንታ አይሰጠውም፤ ፖሊቲከኛ የሃይማኖት ካባ ለብሶ የሕዝብን አስተሳሰብ ለመበረዝ ምን ይሉኝታ ይኖረዋል? ለጀርመን ድርጅት የኅሊና ቅጥረኛ ሆነው አገርዎንና ሃይማኖትዎን መበደልዎ ይታወቅዎታል?

የጀርመን ምሁራን ጥንታዊት ኢትዮጵያ የክርስትና እምነት በሚከተሉ ነገሥታት አገር ስታስተዳድር አውሮፓ በሙሉ ጀርመንን ጨምሮ በባርባሮች (ወሮበሎች) ይታመሱ ስለነበር ይህን መሰል ጥናት አድርገው እንደት እንደበለጸጉ ቢገልጹ መብታቸው ነው፣ ስለማርቲን ሉተር እና ሉተራን ወይም ኢቫንጀሊካን እምነት ያጥኑ እንጂ የኢትዮጵያን ስም ለመቀየር ምን መብት አላቸው? በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሊቃውንት እና ከዘር ፖሊቲካ ነፃ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የታሪክ ምሁራን ጥናታዊ መረጃ ወስደዋል? ኢትዮጵያ የምትወክለው ለብዙ ሽህ ዓመታት ስሟን ሲጠቀም ኖሮ ስሟን እንደያዘ የሞተውን እልፍ አዕላፍ ትውልድ፣ አሁን ያለውን በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠረውን ሕዝቧንና ወደፊትም ታሪኳን ጠብቆ በማንነቱ ኮርቶ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ትውልድ ይመለከታል እንጂ በኢትዮጵያዊነታቸው ክብር ለማይሰማቸው ለሆዳቸው ለሚያድሩ ምሁር ነን ለሚሉ እፍኝ በማይሞሉ ግለሰቦች የአገር ስም ቀርቶ የአንድ ግለሰብ ስም እንኳ አይለወጥም።



ዶክተር በንቲ ስምዎ ትክክል አይደለም ብሎ አንድ ሰው ሌላ ስም ሊቀይርልዎት ይችላል? የሚያስገርመው እነ ዶክተር በንቲ ተመሣሣይ ጥናት ቢያደርጉ ኖሮ ከ250 ዓመታት ወዲህ የሚታወቀውን የበርቱማንና የቦረናን ትውልድ ያስገኘውን ሕዝብ የድሮ አጠራር “ጋላ”፣ ወይም “ኦሮሞ” መባል የተለያዩ ተጨባጭ፣ ነባርና ቁሳዊ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ትክክለኛውን ስያሜ ይነግሩን ነበር። “ኦሮም”፣ “ኦርማ”፣ “ነመ ኦርማ”፣ “ቢየ ኦርማ”፣ እና ስለ”ጋላ” አሰያየም ሲሰጡ የቆዩትን “ገላ” ወደቤት ግቡ፣ “ጋለ” ግመል፣ “ገላ” ስንቅ፣ “ገሎ” ጎርፍ…በመሳሰሉት አገላለጾች ፊደሎችን በመነጣጥልና በማገጣጠም በየአካባቢው የተሠሩ መላምቶችን እልባት ለማስገኘት አጥንተው ዕንቆቅልሹን ለመፍታት ጥረት ቢያደርጉ በታሪካዊ አመጣጡ ላይ ሰዎች የተቸገሩበት ነገር ስለሆነ መፍትሔ በመፈለግዎ ያስመሰግንዎት ነበር። ፖሊቲካው ውስጥ መግባትዎ ካልቀረ ለምን ከዚያ በመጀመር የራስዎን እውነተኛ የታሪክ ጀርባ ሊነግሩን አልፈለጉም? አላጤኑትም እንጂ “በንቲ” የሚለውን ስያሜ ሊያገኙ የቻሉበት ታሪክ በዘር ሐረጋቸው ኦሮሞ ሳይሆኑ በሞጋሳ፣ ሚደቻና በመሳሰሉት የመቀያየጥ ሥርዓቶች (assimilation processes) የቅድም አያቶችዎ በወቅቱ በሌሎች ዜጎች ላይ ሲደረግ አንደነበረው ከሌላ ነገድ ወደኦሮሞነት የተለወጡ ሆነውስ እንደሆነ ማን ያውቃል? ሐሰት ተደጋግሞ ሲነገር የዋሆች እውነት ሊመስላቸው ይችላል፤ነገር ግን በጽንፈኛነት ወይም በዘረኛነትና በአድርባይነት ላይ በተመሠረቱ ሰዎች በሚደረስ ልበወለድ ጽሑፍ ሳይሆን እውነትን በእውነት ለማግኘት ሙያቸውን ለመጠቀም ለሚሹ ተከታይ ትውልዶች ይህ ተጥንቶ ሲረጋገጥ የነዶክተር በንቲ ጥናት ተጋልጦ አንደሕፃን ጨዋታ መታየቱ የማይቀር ነው። ታዲያ ያን ጊዜ የነዶክተር በንቲ ኢትዮጵያዊ መሆን እንደፀሐይ ድምቀት ጎልቶ ይታያል።



ስም በተለያዩ ምክንታቶች ሊሰየም ይችላል፤ አንድን ልጅ እንኳ ቤተሰቡ ባንድ ስያሜ ሲጠራው ጎደኞቹ ደግሞ የቅጽል ስም አውጥተውለት በዚያ ሊጠሩት ይችላሉ፤ አገርና ሕዝብም እንዲሁ፤ ለምሳሌ ኦሮሞዎች በብዙ አካባቢዎች አማርኛ ተናጋሪዎችን ሲዳማ ብለው ሲጠሩ አማርኛ ተናጋሪዎች ደግሞ ኦሮሞዎችን ጋላ ብለው ይጠሩ ነበር (ስያሜው እንደምን እንዳመጣ ባይታወቅም)። እርስዎን መሰል ፖሊቲከኞች ግራርዋን ቢሾፍቱ፣ አዲስ ዓለምን ኤጄሬ ፣ አዲስ አበባን ድሮ ሸገር፣ አሁን ደግሞ ፊንፊኒ ብለው ሲጠሩ ሌላው ሕዝብ በትዝብት እየተከታተለ ነው፤ ጀርመኖች በውጭ ሰዎች ጀርመን ሲባሉ ራሳቸውን ዶች፣ አገራቸውን ዶችላንድ ይላሉ፤ አሜሪካኖች ራሳችውን አሜሪካ ሲሉ ሌሎች ያንኪ ይልዋቸዋል፤ በያንኪ ስም ስታዲየም፤ የአትሌቲክ ቡድን እና ሌሎችም ስያሜዎች ሰይመዋል፤ እንዲሁም ኢራን ፐርሺያ፣ ጋና ጎልድ ኮስት፣ ግብጽ ምሥር፣ ኢራቅ ሜሶፖታሚያ፣ ደቡብ አፍሪካ አዛኒያ፣ ታይላንድ ሲያም፣ አርሜኒያ ሔያስታን በሚል ሊሎችም አያሌ ሕዝቦችና አገሮች ከአንድ በላይ መጠሪያ አላቸው። ባለቤቱ የመረጠውን ስያሜ ግን ማንም በምንም መልኩ ለመለወጥ መብት የለውም፤ ማንነቱ የባለቤቱ ስለሆነ ማለት ነው፤ ኢትዮጵያ ኩሽ ተብላ አትታወቅም፤ ባይሆን የኩሽ የበላይ አገር ተብላ ትታወቃለች እንጂ፤ ኢትዮጵያዊ ሆነው ኩሽ የሚለውን ስያሜ ለኢትዮጵያ ለመስጠት የሚቃጣዎት ከሆነ አረቦች ኢትዮጵያን ሐበሻ፣ ሕዝባችንን ሐበሽ (ድብልቅ ወይም ዲቃላ) ብለው መጥራታቸውን ሊቀበሉ ነው? አዎን ካሉ ኢትዮጵያዊ መሆንዎ ያጠራጥራል፤ ወላጁን በባዕድ እንዲናቅ አሳልፎ የሚሰጥ አዕምሮ ያለው ሰው አይኖርምና።



እነዶክተር በንቲ ያልተገነዘቡት ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜ ግሪኮች የሰጧት ስም ነው ብለው በመቀበል ለጥናታዊ ጽሑፋቸው ማረጋገጫ አድርገውታል። ፈረንጅ አምላኩ ማለት ይኸ ነው! ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ሳያውቁ ግሪክ ስም እንዳወጣችላቸው ሲገልጹ አገራችን ሰው የሌለበት ባዶ አድርገዋታል ማለት ነው። ለመሆኑ የዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳን ጥናት አይተዋል? ከግሪክ አፈታሪክ በመውሰድ እና ቃላትን በይመስላል በማገጣጠም (wild guess based on phonetic combination) የተሰነዘሩ መላምቶችን መነሻ አድርገው ጥናት አድርጌያለሁ ማለትዎ ምን ያህል ዕውቀትዎ ሚዛን ሊደፋ የማይችል (shallow) እና ተቀባይነት የሌለው guesswork) መሆኑን ያሳያል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘው አገላለጽዎ ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ በአፄ ምንሊክ ዘመን የተሰጠ ስያሜ ነው ሲሉ ትንሽም አላፈሩም፤ እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስም የተጻፈው በአፄ ምንሊክ ዘመን ነው ሊሉን ይሆን? መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈባቸው በጣት ከሚቆጠሩ ቋንቋዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ቋንቋ (ግዕዝ) መሆኑን የውቃሉ? ይህን የማይገነዘብ/የማይቀበል ውሱንና ጥራዝ-ነጠቅ ዕውቀት ጭልጥ አድርጎ ኢትዮጵያን ከሚክዱት ጠባብ ፖሊቲከኞች ጎራ ውስጥ በቀጥታ ያስገባዎታል። ወደታሪክ ጠቀሳ ከመሄዳችን በፊት ዓላማዎ የሃይማኖት ጥናት ነው? ወይስ የፖሊቲካ? የሚለው ተንከባሎ ይመላለሳል።



ኢትዮጵያን በመቶ ዓመት ለመገደብ የሚፈልጉ ጠባብ ፖሊቲከኞች ከሚጠቀሙባቸው የጠባብነት መግለጫዎች ውስጥ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ስሞችን በመተው በተወሰኑ ዘመኖች ውስጥ በሰፋሪዎች የተሰጡና የሚመቻቸውን ስሞች በመቀበል ታሪክን ይክዳሉ። ለምሳሌ ከሰሜን አረቢያ እስከኤደን የነበሩትን አያሌ አብያተክርስትያን ቀርቶ እስከዛሬ ቆመው ከሚታዩት ውስጥ ባሌ ጎባ ውስጥ ከድንጋይ ተጠርቦ የተሠራው ቤተክርስትያን ከአፄ ምንሊክ ዘመን ወዲህ የተሠራ ነው ሊሉን ነው ማለት ነው፤ ከእንጦጦ እስከ የካ አካባቢ የሚገኘው ዋሻ ሚካኤል ድረስ ተቀብሮ እንደነበረ የታወቀውን ከተማ ሊክዱ ነው ማለት ነው፤ በባሌ፣በሸዋ፣ በወሎ፣ በወለጋ፣ በቦንጋ፣ በዛሬው ጋሞጎፋ፣ በምሥራቅና ደቡብ ኢትዮጵያ በይፋ የሚታዩትን እንዲሁም በዋሻ ውስጥ የተገኙ ንዋየ-የቅዱሳትን፣ የአዳዲ ማርያምንና የዝቋላ አቦን ጥንታዊ አብያተክርስትያን ሊክዱ ነው ማለት ነው፤አምባሰል፣ ባንቻሮ፣ ኩታበር፣ ላኮመልዛ፣ ሐይቅ፣ የጎፍ፣ አርዲቦ፣ ዞብል፣ ወልደያ፣ደሴ፣ ላስታ፣ቀብሪ ደሐር፣ ደጋሃቡር፣ እንጦጦ፣ እንደገብጣን፣ ዝቋላ፣ ግንደበረት፣ ምንጃር፣ ቡልጋ፣ ደዋሮ፣ ዳሞት፣ ፋጢጋር፣ ግራርዋ፣ አሰቦት፣ ጀጎል፣ ጋንዝ፣ ባሌ፣ ሸዋ፣ ጋፋት…ወዘተ ጥንት የነበሩ ስሞች መሆናቸው ቀርቶ በእነ አፄ ምንሊክ ዘመን የተፈጠሩ ስያሜዎች ናቸው ሊሉን ይፈልጋሉ ማለት ነው። ዶክተር በንቲ ቅን የሃይማኖት ጥናት የሚያደርጉ ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ የተገኘውን መጽሐፈ ሒኖክ ነባራዊ ኢትዮጵያዊ መንፈሳዊ ሥነጽሑፍ እንዲሁም እነሚካኤል አንጀሎ፣ ሊዎናርዶ ዳቨንሲ፣ ዊሊያም ሼክስፒር ከመወለዳቸው ከ1000 ዘመናት በፊት በኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ ስለተሠሩ መንፈሳዊ ዜማዎችዎና ከ4000 ዓመታት በፊት በመንፈሳዊ ሥነጽሑፍ ላይ ስለነበረው የግዕዝ ፊደልና ቋንቋ አጥንተውና የሀገርዎን ጥንታዊነት አውቀው ለማያውቁት ባሳወቁ ነበር።



እነዶክተር በንቲ ማወቅ የነበረባቸው ወይም ማወቅ ሲችሉ የዘነጉት ነገር ቢኖር ጥቁር ፈርኦን በሚባሉ መሪዎች በኢትዮጵያ ሥር ግብፅን ጭምር ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ720 እስከ 610 ዓመተ ዓለም ገደማ ደረስ ሲገዙ በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን በአረቢያ የነበረው የአብርሃ መንግሥት በአክሱማዊው አፄ ካሌብ ሥር እንደነበረ ሁሉ፤ የኩሽ መንግሥትም ርዕሰ ከተሞቹን ከርማ፣ ናፓታ እና ሚሮ በማድረግ ለብዙ ዘመናት በኢትዮጵያ ሥር የነበረ መንግሥት ስለነበርና በኢትዮጵያ ሥር ሆኖ ግብፅን የወጋ ስለሆነ ግብፆች ኢትዮጵያን ኩሽ ብለው መጥራታቸውን ነው ከታሪክ የምንረዳው። ግብፅ ኢትዮጵያን ኩሽ ብላ ብትጠራም ኩሽም በኋላ ኑብያ ተብሎ ይጠራ ነበር። ከሮማውያን መነሣት በፊት ፈኒቃውያን፣ ሒክሶስ የሚባሉ ነገዶችና አሦራውያን በግብፅ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀናቃኝ ኃይሎች ነበሩ፤ ስለሆነም በተለይ አሦራውያን እያየሉ ሲመጡና ኢትዮጵያ በግብፅ ላይ የነበራት የበላይነት ሲቀር፤ የኢትዮጵያ ግዛት ከግብፅ ወጥቶ ሳባዊ፣ አክሱማዊ እና ሰሎሞናዊ ጭምር እየተባለ እንደተጠራ፤ በኋላ እንደሆነው እንደ አብርሃ መንግሥት ኩሽ እየከሰመ (phase out) መሄድና በዚሁ መሠረት ሰሎሞናዊው መንግሥት ግዛቶቹ እየቀነሱ የመጡ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን በበላይነት እየመራ አስከ 20ኛው መቶ ክፍለዘመን ማገባደጃ ድረስ የቆየ መሆኑን መረዳት ነበረባቸው።



በጥንታዊት ኢትዮጵያ ሰሎሞናዊውን ሥርወመንግሥት ከውስጥ ይቀናቀኑ የነበሩት የኩሽ፣ የቤጃ፣ የዳሞት፣ ከግራኝ መሐመድ አነሳስ በፊት የሚታወቀው የወላስማ፣ ማዕከሉ ላስታ የሆነው የዛጉዌ ሥርዓቶችም እንደነበሩ በታሪክ ይታወቃል። የውጭ አገር ፀሐፊዎች ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሕንደኬ ተብሎ የሚጠራውን ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ ከሮማውያን መንግሥት ጋር ተፎካካሪ መሆኑ የሚታወቀውንና መግባቢያው ግዕዝ የነበረውን ጥንታዊ በአብዛኛው የሴት ነገሥታትን ያካተተ ሥርወመንግሥት “Candace – Queens of Ethiopa” አንዳንዴ “ Kushitic Queens” ፣ ዝቅ ማድረግ ሲፈልጉ ደግሞ “Merotic Queens” ይሏቸዋል። ልዕለ ኃያል የሆኑ አገሮች የከሰሙ የመንግሥት ሥርዓቶች ታሪክ ስለማይጎዳቸው ዝናቸውን ከገለጹ በኋላ ኢትዮጵያ ግን አሁንም አልጠፋ እያለች ስለተቸገሩ የነበራትን ታላቅነት ማንኳሰስን መርጠዋል። ዶክተር በንቲ በደንብ አላጤኑትም እንጂ ፈረንጆች እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያን ኩሽም ሳይሆን አቢሲኒያ ብለው መጥራትን ይመርጣሉ፤ የበለጠ ማሳነስ ሲፈልጉ አማራ ብለውም ይጠሩ ነበር፤ ምክንያቱም አውሮፓውያንም ሆኑ ኦቶማኖች በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ የበላይነት የነበረውን የነአፄ ካሌብን፣ ፕሬስተር ጆን ወይም ኢትዮጵያዊ ቆስጠንጢኖስ ተብሎ የሚታወቀውን የነአፄ ዘራያቆብን፣ የእነአምደጽዮንን ግዛት ዝና ከመስማት አረቦች ሐበሽ በማለት በሚያንኳስስ ስያሜ መጥራታቸው ኢትዮጵያን ዝቅ አድርገው እነሱ ባሪያ እየገዙ ኢትዮጵያ ባሪያ ትሸጣለች በማለት ራስዋንም ማስተዳደር እንደማትችል ማረጋገጫ በመፈለግ በነሱ ቅኝ ሥር ለማድረግ የጋራ ጥረት እንዳደረጉ፤ ኢጣሊያ በወረረችን ጊዜ ትልልቆቹ የአውሮፓና ዛሬ በጣት የምንቆጥራቸው ጥቂት ኃያላን መንግሥታት አገሮች በሙሉ የባህር በሮቿን በሙሉ በመቆጣጠርና ማዕቀቦችን በማድረግና ለኢጣሊያ የጦር መሣሪያ በማቅረብ ጭምር በአገራችን ላይ ምን ያህል ተባብረውባት እንደነበረ፤ በአገራችን እንደአቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ያሉ የሃይማኖት መሪዎቻችን ጠላትን እያወገዙ ሲታረዱ በአውሮፓ በተለይም በሮም ያሉ ታላላቅ የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች በፋሽስታዊ ወረራው ላይ ምንአቋምእንደወሰዱ፤ እንዲሁም ኢጣሊያ ተሸንፋ ስትወጣና የኢትዮጵያ አርበኞች ከንጉሠነገሥታቸው ጋር በኦሜድላ በኩል ሲገቡ በጀነራል ካኒንግሃም የሚመራው የእንግሊዝ ሠራዊት ኢትዮጵያን እንደገና በቅኝ ለመያዝ በደቡብ በኩል ወዳገራችን እንደዘመተ፤ በቀላሉ ከታሪክ አንብበው መረዳት ይገባዎታል። የደቡብ አፍሪቃ አገሮችን መንፈሳዊ ትምህርት እያስተማሩ በቅኝ ገዥዎች ሥር እንዲወድቁ ያደረጉት እንደርስዎ ያሉ አድርባይ ወንጌላውያን ነን ባዮች እንደነበሩ ከታሪክ አይተነዋል። እነዚህ ኃያላን መንግሥታት እንደ ኢትዮጵያ ያሉትን አገሮች በራሳቸው አድርባዮች ተጠቅመው የጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ውስጥ ለማስገባት ዛሬም እንደሚፈልጉ ካላወቁ ዛሬም ለወራሪዎች የሚያገለግሉ የባንዳነት ሚና ውስጥ ተንሸራተው መግባትዎን መረዳት አለብዎት። መጽሐፍ ቅዱስን ተቀብሎ እግዚአብሔርን የሚያምን ሰው በሥነመለኮት ጥናቱ ላይ በማተኮርና ዕውቀቱን በማዳበር ሃይማኖቱን ያጸናል እንጂ ብሉይን ከሐዲስ አወራርሳ የኖረችውን ጥንታዊ አገር ስም በሃይማኖት ካባ ለመቀየር ሰበብ ፈልጎ መጽሐፍ ቅዱስን ለማሻሻል መሞከር ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ አለማመኑን እና እምነቱን የሚሸረሽር፤ በሌላ በኩል ሃይማኖት ዋና ዓላማው እንዳልሆነ ያሳያል፤ እንደባለቤትም የአገሩን ክብር ይጠብቃል እንጂ ኢትዮጵያን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ጥረት ለሚያደርግ ሥርዓት አያገለግልም፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ክብር ለማንኳሰስ መሞከር ጠላቶቻችን ሊያደርጉብን የሚፈልጉትን የባህል ወረራ መከተል ስለሆነ ከባንዳነት ተግባር ተለይቶ ሊታይ አይችልም።



የአገርን ስም በልበወለድ መጽሐፍ ለመለወጥ የሚያደርጉት ሙከራ ከቅዠት የማያልፍ ነገር ቢሆንም፤ በማወቅም ሆነ ተዘናግተው ባለማስተዋል የኢትዮጵያን ክብር ለማጉደፍ ከሚሯሯጥ የባእድ አገር ሴራ ጎን ተባባሪና አገልጋይ ሆነው በመቆምዎ በተለይም ዛሬ አገራችን ኅብረትና አንድነት እየጠማት ባለችበት ወቅት በተፈጠረው ችግር ላይ በሃይማኖት ስም ሌላ በሽታ ለመጨመር በመሞከር የሀገር ክህደት ተግባር በመፈጸምዎ ከአገርዎ ሕዝብ ራስዎን የተገለሉ ያደርግዎታል። ሥነጽሑፍዎ አግባብነት ካላቸው ተጨባጭ መረጃዎች ጋር ተገናዝቦ አግባብነት ባላቸው ባለሙያዎች ከተገመገመ በኋላ ድርሰት መሆኑ ሲረጋገጥ የሚያገኙትን/ያገኙትን የትምህርት ማዕረግ ተአማኒነት ወይም ትክክለኛነት (validity) ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባው እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብዎታል። ኢትዮጵያ የግል ስም ነው፤ ኢትዮጵያ ኅብረብሔራዊት መሆንዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚታወቅላት ጥንታዊትና ወደውስጥ ከገቡት ይልቅ ወደውጭ የፈለሱ ማኅበረሰቦች የሚበዙባት አገር ስትሆን፣ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ጉራግኛ፣ ከምባትኛ፣ ሲዳምኛ… ወዘተ የሚባሉ ቋንቋዎች በተነፃፃሪ አገላለጽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠሩ ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች ናቸው። ከአራችን በስተቀር ሌላ ኢትዮጵያ የሚባል አገር የለም። የኢትዮጵያን ስም እቀይራለሁ ብሎ የሚነሣ ግለሰብም ሆነ መንግሥታዊ አካል ስም በማጉደፍ በሕግ ሊከሰስም ይችላል፤ የአገርን ክብር የሚነካ ያውም በኢትዮጵያዊ የሚፈጸም ድፍረት ውሎ ያድር ይሆናል እንጂ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ፍርድ እና ከሕግ ተጠያቂነት አያመልጥም።



ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!



ተፈራ ድንበሩ

No comments:

Post a Comment

wanted officials