በትላንትናው ዕለት በአማራ ክልል ምንጃር ውስጥ የተካሔደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣ ሰዎች መታሰራቸው ታወቀ፡፡ ለእስር የተዳረጉት ሰዎች በተቃውሞዉ ላይ ድምጻቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ከየቤታቸው ታድነው እስር ቤት ተወርውረዋል፡፡ በትላንቱ ተቃውሞ ላይ በርከት ያለ የምንጃር ህዝብ አደባባይ ወጥቶ የህወሓትን አገዛዝ እንደማይፈልግ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ዛሬ ከስፍራው የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት፣ ከተማዋ ውጥረት ነግሶባት ውላለች፡፡ በተለይ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የታጠቁ ፖሊሶች በመዘዋወር አካባቢውን ሲቃኙ መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአካባቢው ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞ ማሰማት የጀመረው፣ በአካባቢው የመብራት አገልግሎት ከተቋረጠ አስራ አምስት ቀናት ስለተቆጠሩ በመሆኑ ነው፡፡ ጉዳዩ ያበሳጨው የአካባቢው ማኅበረሰብ ለሚመለከታቸው የወረዳው አካላት ጥያቄውን ሲያቀርብ ቢቆይም፣ ሰሚ ባለማግኘቱ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞ ለማሰማት መገደዱን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
‹‹ተቃውሞ አሰምታችኋል ከተማ በጥብጣችኋል›› ተብለው የታሰሩት ሰዎች በቀጣይ ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ ይመስረትባቸው ወይም በነጻ ይለቀቁ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ ለማወቅ የተደረገው ጥረት ባይሳካም፣ ከሀያ በላይ ወጣቶች መታሰራቸውን ከመረጃዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ሲዘዋወሩ የነበሩ የታጠቁ ፖሊሶች፣ መንገደኛውን ሲያዋክቡ እና ሲያመናጭቁ እንደነበር የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment