(ኢሳት ዜና–ሕዳር 21/2010)
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ እየተባባሰ መቀጠሉ በሚነገርበት በአሁኑ ወቅት የጋምቤላ ክልል ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ መክፈል አለመቻሉን ገለጸ።
በዚህም በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች በሙሉ የጥቅምት ወር ደሞዛቸው እስከ ህዳር አጋማሽ እንዳልተከፈላቸው ታውቋል።
የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ክልሉ ገንዘብ ለመክፈል ጊዜያዊ ችግር እንዳጋጠመው አረጋግጠዋል።
የጋምቤላ ክልል በስሩ የሚያስተዳድራቸው የመንግስት ሰራተኞች በአጠቃላይ 1550 ያህል እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ታዲያ እነዚህ ሁሉ ሰራተኞች ናቸው የጥቅምት ወር ደሞዝ እስከ ሕዳር አጋማሽ ድረስ እንዳልተከፈላቸው የታወቀው።
የመስከረም ወር ደሞዝም የተከፈላቸው ዘግይቶ መሆኑ ተመልክቷል።
ደሞዛቸውን ካላገኙት 1ሺ 547 ሰራተኞች ውስጥ 513ቱ መምህራን መሆናቸውንም መረጃው አመልክቷል።
እነዚህ መምህራን ደሞዝ ይከፈለን በማለት ባለፈው ሳምንት የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውንና ከዚህም ጋር ተያይዞ የመማር ማስተማር ሂደቱ መስተጓጎሉን የከተማዋ ከንቲባ አቶ አከነ ኦፓዳ ለሪፖርተር ጋዜጣ አረጋግጠዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ከመምህራን ጋር ህዳር 18/2010 በተደረገ ምክክር ህዳር 19 ወደ ስራ መመለሳቸውን ገልጸዋል።
የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር በሚያገኘው ገቢና በወጪው መካከል ክፍተት በመኖሩ ለሰራተኞች በአግባቡ ደሞዝ ለመክፈል መቸገሩን ከንቲባው ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የጋምቤላ ከተማ የገቢዎች ጽህፈት ቤት ማንነታቸው ያልታወቀ ሃይሎች ባስነሱት ቃጠሎ መውደሙን ሪፖርተር ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
ቅዳሜ ህዳር 19/2010 በደረሰው በዚህ ቃጠሎ ልዩ ልዩ ሰነዶች፣ኮምፒዩተሮችና ሌሎች የጽህፈት መሳሪያዎችና የቢሮ እቃዎች ወድመዋል።
የከተማዋ ከንቲባ እንደሚሉት በቃጠሎው የተጠረጠሩ 10 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
በተመሳሳይ ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ በጋሞጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ የገቢዎችና ጉምሩክ ጽህፈት ቤት በእሳት መውደሙን መዘገባችን ይታወሳል።
የጋምቤላውና የሳውላው የገቢዎች ጽህፈት ቤት በተመሳሳይ ቀን በእሳት እንዲጋይ መደረጉ የተቀነባበረ ድርጊት ይሁን አይሁን ግን የታወቀ ነገር የለም።
No comments:
Post a Comment