በሻኪሶ ዛሬ ከባድ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተካሄደ።
በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋና የአካባቢው ነዋሪዎች ለተቃውሞ የወጡት ሜድሮክ ኢትዮጵያ በአካባቢው የሚያከናውነውን የወርቅ ማውጣት ስራ ለተጨማሪ 10 አመት እንዲታደስለት ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።
የሰልፈኞቹ ለተቃውሞ መውጣት ምክንያቱ ይህ ነው ይባል እንጂ ዋነኛ ጥያቄያቸው ግን የወያኔ ስርአት ይብቃን የሚል ነው።
ሜድሮክ ኢትዮጵያ በሻኪሶ የወርቅ ማዕድን ለማውጣት ከህወሃት መንግስት ጋር የተፈራርመው የ20 አመት ውል ጊዜው ተጠናቋል።
ነገር ግን ተቋሙ አሁንም በአካባቢው የወርቅ ማውጣት ስራውን ለማከናወን እንዲችል ውሉ ለ10 አመት እንዲታደስለት ጥያቄ አቅርቧል።
ነገር ግን ላቀረበው ጥያቄ ከሕወሃት መንግስት ምላሽ ከማግኘቱ በፊት የአካባቢው ነዋሪ በራሱ ምላሽ ሰጥቶታል።
በአራቱም አቅጣጫዎች እየተመመ በሻኪሶ ከተማ ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰአት ላይ ለሰላማዊ ተቃውሞ የተሰባሰበውና 6 ኪሎሜትር ያህል በመጓዝ ድምጹን ያሰማው ሕዝብ ቁጥር ደግሞ ቀላል የሚባል አይደለም።–በ10 ሺዎች የሚቆጠር እንደነበር በሰልፉ ላይ የተገኙት የከተማዋ ነዋሪ አረጋግጠውልናል።
እሳቸው እንደሚገልጹት ከሆነ ሰልፈኞቹ ሜድሮክ ኢትዮጵያ የሰራው ለራሱ ጥቅም እንጂ ለእኛ አይደለም የሚል መልዕክትን ይዘዋል።
ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እስከ መንግስት ሰራተኞችና ሌሎቹን የሕብረተሰብ ክፍሎች ያካተተው የተቃውሞ ሰልፍ መነሻ የወርቁ ጉዳይ ብቻ አልነበረም ይላሉ።
ሰለፈኞቹ በወያኔ ስርአት አላግባብ የተጫነብን ግብር ይነሳልን ሲሉም ከፍ ባለ ድምጽ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።
ሰልፈኞቹ ያሰሙት በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ይበቃናል የሚለው መልዕክትም ሌላው ነበር ይላሉ ለኢሳት መረጃውን ያደረሱ ነዋሪ።
ሰልፈኞቹ ወደ ተቃውሞ ሲወጡ 5 ያህል ጥያቄዎችን በመያዝ ነበር።
ሰልፈኞቹ በማጠቃለያቸው የያዟቸውን ጥያቄዎች ለአባገዳዎች ያቀረቡ ሲሆን እነዚህ ጥያቄዎቻቸው በአስቸኳይ ምላሽ ካላገኙ ለሌላ ተቃውሞ እንደሚነሱ አስረግጠው ተናግረዋል።
ለተቃውሞ አደባባይ የወጣው ህዝብ ድምጹን አሰምቶ በሰላማዊ መንገድ ከጨረሰ በኋላ የሀገር ሽማግሌዎች በምርቃታቸው ሰልፉ እንዲጠናቀቅ አድርገዋል።
No comments:
Post a Comment