በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው ስነ ስርአት የኢፌዴሪ 4ኛ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዲፕሎማትነት የረዥም አመታት ልምድ አዳብረዋል።
ከንግስት ዘውዲቱ ወዲህ የመጀመሪያዋ እንስት ርዕሰ ብሔርም ሆነዋል።
በ1942 አዲስ አበባ ከተማ የተወለዱትና የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት የተከታተሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ከፍተኛ ትምህርታቸውን በፈረንሳይ ሞንተሌ ዩኒቨርስቲ ተከታትለዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በተፈጥሮ ሳይንስ የወሰዱት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአለም አቀፍ ግንኙነት ስልጠና መውሰዳቸውም በፓርላማው በተነበበው የሕይወት ታሪካቸው ላይ ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ የሴት አምባሳደር በመሆን ያገለገሉትና በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ የሴት ፕሬዝዳንት የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ በጅቡቲ፣በፈረንሳይና በተለያዩ ሃገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል።
በአፍሪካ ህብረትና በኢጋድ የኢትዮጵያ ተወካይ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዳይሬክተር በመሆንም አገልግለዋል።
በቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባንኪሙን በኬንያ የተባበሩት መንግስታት ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣በአዲሱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኖዮ ጉተሬዝ በአፍሪካ ሕብረት የተባበሩት መንግስታት ተወካይ እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት የተባበሩት መንግስታት ቢሮ ሃላፊ ሆነው ማገልገላቸውንም ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል።
የ69 አመቷ ዲፕሎማት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሁለት ወንድ ልጆች እናት እንደሆኑም ታውቋል።
ለሚቀጥሉት 6 አመታት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት በመሆን የተሾሙት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ላለፉት 5 አመታት በፕሬዝዳንትነት ካገለገሉት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ዛሬ በይፋ የፕሬዝዳንትነቱን ስልጣን ተረክበዋል።
በበአለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር ለሃገሪቱ ሰላም የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ እንደሚያግዙም ቃል ገብተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ የአዲስ አባባ ንግድ ምክር ቤት ባካሄደው ምርጫ ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት በኋላም የአባይ ባንክ ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል።