Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, October 24, 2018

የአማራ ክልል ላወጣው መግለጫ የትግራይን ህዝብ ይቅርታ ይጠይቅ ተባለ


(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 14/2011) የትግራይ ክልላዊ መንግስት በራያ ጉዳይ የአማራ ክልል ላወጣው መግለጫ እንዲጠይቅ  አሳሰበ።
ትላንት ማምሻውን የወጣው የትግራይ ክልል መግለጫ የአማራ ክልል መንግስት የራያ ጉዳይ በሃይል መፍታት አይቻልም በሚል ላወጣው መግለጫ ምላሽ እንደሆነም ተመልክቷል።

በአማራ ክልል መንግስት በኩል የወጣው መግለጫ መሰረታዊ የሆነ ሕገ መንግስታዊ ጥሰት ያለበትና በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረውን አብሮነት የሚጎዳ አደገኛ አካሄድ መሆኑን በመጥቀስ ለትግራይ ህዝብ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና የትግራይ ህዝብ በጥብቅ እናሳስባለን ይላል።
የአማራ ክልል ለማሳሰቢያ እስከአሁን የሰጠው ምላሽ የለም።
የትግራይ ክልል የራያው ውዝግብ ዳግም ከተቀሰቀሰ ካለፈው ቅዳሜ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ያወጣው ማሳሰቢያ ለአማራው ክልል የትላንት ምላሽ መሆኑ ተመልክቷል።
የትግራይ ክልል መንግስትና ህዝብ ሰላሙን አስጠብቆ የክልሉን ውስጣዊ ችግሮች ለመፍታት ሌትና ቀን በሚረባረብበት ወቅት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ያወጣው መግለጫ  ከትንኮሳ የማይተናነስ ጠባጫሪ አቋም ነው ይላል ከመቀሌ ትላንት ማምሻውን የወጣው መግለጫ።
የአማራ ክልል መስተዳድር ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው ሁለቱ ክልሎች በሚያዋሰኑት የወልቃይትና የራያ አላማጣ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የሰላም መታወክ እየገጠመ ይገኛል።
ይህ የሰላም መታወክ ለአማራው ክልል ትልቅ የፀጥታ ስጋት ሆኗል ብሏል።
የትግራይ ክልል መንግስትን ያስቆጣውም ትግራይ እንደምን ለሌላው ሰላም ማጣት ሰበብ ተደርጋ ትወቀሳለች የሚል ነው። መግለጫውንም አሳዛኝና ጠብ ጫሪነት ነው ሲል ወቅሷል።
የትግራይ ክልል የሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ተወላጆች ሕገ መንግስታዊ መብታቸውና ነፃነታቸው ተከብሮ በሰላምና በክብር የሚኖሩባት ክልል ሆና እያለች ዜጎች በማንነታቸው የሚፈናቀሉባትና የአማራ ክልል ሰላም ችግር ፈጣሪ መባሏ አሳዛኖናል ይላል የትግራይ ክልሉ መግለጫ።
የትግራይ ክልል ለየትኛውም አካባቢ የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ሊሆን አይችልም ብሏል።
የተከሰተው ግጭት መነሻው የራያ አካባቢ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ሲሆን ይህንን ጥያቄ ከህዝቡ ጋር በመነጋገር ሕገ መንግስታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም ሆነ በኢህአዴግ ጉባኤዎች አቅጣጫ መቀመጡ ይታወሳል የሚለውን በአማራ ክልል መንግስት መግለጫ የተጠቀሰውን የትግራይ ክልል መስተዳድር ሕገ መንግስቱ በማንነት ጉዳይ ላይ ያስቀመጠውን ስርዓት በመጣስ በሌላ ክልል የውስጥ ጉዳይ ጠልቃ መግባቱን የሚያረጋግጥ መግለጫ ነው ሲል ከሷል።
በዚህም በራያና በወልቃይት አካባቢዎች ለተፈጠሩ ችግሮች የአማራ ክልል መንግስት ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል በማለት የትግራይ ክልል በመግለጫው አስታውቋል።
በአጠቃላይ የአማራ ክልል መንግስት ያወጣው መግለጫ መሰረታዊ የሆነ ሕገ መንግስታዊ ጥሰት ያለበትና በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረው አብሮነት የሚጎዳ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲታረም እና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ለትግራይ ህዝብ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና የትግራይ ህዝብ በጥብቅ እናሳስባለን ሲል ያጠቃልላል።
ለትግራይ ክልል መንግስት ማሳሰቢያ የአማራው መስተዳድር ምላሽ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

No comments:

Post a Comment

wanted officials