በአዲስ አበባ ለአንድ ሳምንት ግምገማ ሲያደርግ የቆየው የጋምቤላ ክልል ገዢ ፓርቲ በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁትን ሊቀመንበሩንና ምክትላቸውን በሌሎች መተካቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበርና የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱትና ምክትላቸው አቶ ሰናይ አኩዎር ይቅርታ ጠይቀው በለቀቁበት የአዲስ አበባው ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መገኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በጋምቤላ የጋትሉዋክ ቱት አመራር ከስልጣን እንዲወርድ የተቃውሞ ሰልፍ ሲደረግ ቆይቷል።
በዚህ ተቃውሞ በተወሰደ የሃይል ርምጃም በትንሹ አስር ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
ለወራት የዘለቀው የህዝብ ጩሀት በመጨረሻም ሰሚ አገኘ።
የጋምቤላ ክልል ነዋሪ አመራሩ እንዲነሳለት ህይወቱን የገበረለትን ተቃውሞ ሲያደርግ ነበር የቆየው።
ባለፉት ሶስት ወራት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ለፌደራሉ መንግስት ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል።
በአመራር ላይ ያለው የጋትሉዋክ አስተዳደር በኢትዮጵያ የመጠውን የለውጥ ሂደት የሚያደናቅፍ ከመሆኑ ባሻገር የህወሀት የጭቆና አገዛዝን ማስቀጠል የመረጠ በመሆኑ በአስቸኳይ ይነሳ የሚለው ጥያቄ ተነስቷል።
ተቃውሞው በተለይ የክልሉ ፕሬዝዳንት ላይ ያነጣጠረ ነበር።
ለዚህም ሁለት ምክንያቶች ይነሳሉ። አንደኛው የክልሉ ፕሬዝዳንት ጋትሉዋክ ቱት በትውልድ ደቡብ ሱዳናዊ በመሆናቸው በስደት ወደኢትዮጵያ ለገቡትና በቁጥር በጋምቤላ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ለሚበልጡ ደቡብ ሱዳናውያን ያደላሉ የሚል ነው።
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከህወሀት አገዛዝ ጋር እጅና ጓንት ሆነው የክልሉን ህዝብ ለጭቆናና ብዝበዛ እየዳረጉት እንደሆነ ይጠቀሳል።
የህወሃት ዘመን አፈናና በደል ጋምቤላ ተጠናክሮ መቀጠሉን ህዝቡ በምሬት ይገልጻል።
በቅርቡ ለውጡን ለመታዘብ ሀገር ቤት የገቡትን በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆኑት ዶክተር ማኛንግን ጨምሮ ከ10 በላይ አክቲቪስቶችን የግትሉዋክ ቱት አስተዳደር ማሰሩ ተቃውሞውን አጠናክሮታል።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ፕሬዝዳንት አቶ ኦባንግ ሜቶ ወደ ጋምቤላ ባመሩ ጊዜ የጋቱዋክ ቱት አመራር የፈጠረውን ችግር መነሻ በማድረግ በአዲስ አበባ መግለጫ የሰጡት አቶ ኦባንግ የፌደራሉ መንግስት በጋምቤላ አስተዳደር ላይ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸውም የሚታወስ ነው።
ለወራት የህዝብ ብሶትና እሮሮ ከተሰማ በኋላ ትላንት ምላሽ መገኘቱን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
አዲስ አበባ የገቡትና ግምገማቸውን ከጀመሩ አንድ ሳምንት የሆናቸው የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጋህአዴን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከአንድ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን አሳውቀዋል።
ህዝብ ለውጥ እንደሚፈልግ፣ አመራሩ እንቅፋት ሆኖ እንደቆየ አባላቱ ጠንከር ያለ ግምገማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የህዝብ ተቃውሞ የቀረበባቸው አቶ ጋትሉዋክ ቱትና ምክትላቸው አቶ ሰናይ አኩዎር በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸው ተስምቷል።
ፓርቲው አቶ ኦሙድ ኡጁሉን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አኙአያ ጃከን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡም ታውቋል፡፡ አቶ ኦሙድ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ክልሉን እንደሚመሩ ነው የተገለጸው።
በግምገማው ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ መገኘታቸው ታውቋል።
የክልሉ ህዝብ ልማት የተጠማ በመሆኑ አዲሱ አመራር ጊዜውን በግል አጀንዳዎችና ሽኩቻ ከማጥፋ ይልቅ ራሱን ከጎሰኝነትና ከጥላቻ በማጽዳት የክልሉን አመራር በማጠናከር የህዝቡን ችግር ሊፈታ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ ገልጸዋል።
ከኃላፊነት የተነሱት አመራሮችም በድርጊታቸው ተጸጽተው ይቅርታ መጠየቃቸው እና ህዝቡን ለመካስ በተመደቡበት የስራ መስክ ለመሰማራት መወሰናቸውም ተመክልቷል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የጋምቤላ አክቲቪስቶች ግን የጋትሉዋክ አመራር አባላት ለፈጸሙት የግድያና የዘረፋ ወንጀል በህግ ሊጠይቁ ይገባል ባይ ናቸው።
No comments:
Post a Comment