እድሳቱን ለማከናወን ወደ ቤተክርስቲያኑ ሊገቡ የነበሩ ሰራተኞችን የግብጽ ጳጳሳትና መነኮሳት ክልከላ ማድረጋቸውን ተከትሎ የእስራዔል ፖሊስ ርምጃ ወስዷል።
ከአንድ ዓመት በፊት ጣሪያው የተደረመሰውን የኢትዮጵያ ገዳም ለማሳደስ ከፍተኛና እልህ አስጨራሽ ትግል መካሄዱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ይዞታ ለመንጠቅ በየጊዜው ሙከራ የሚያደርጉት ግብጻውያን ገዳሙ እንዳይታደስ በሃይል ያደርጉትን ክልከላ የእስራኤል ፖሊስ በማስቆም በዛሬው ዕለት ዕድሳቱ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል።
በኢየሩሳሌም በሚገኘው የዴር ሱልጣን ገዳማት የኢትዮጵያና የግብጽ የሃይማኖት መሪዎች ውዝግብ ሁለት መቶ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።
ኢትዮጵያ በዴር ሱልጣን ገዳም ያላት መብት ከግብጽ ወደ አከባቢው መግባት አስቀድሞ በዙ ዘመናትን ያስመዘገበ እንደሆነ ታሪክ ይመሰክራል።
በ18ኛው ክፍለ ዘመን ኢብራሂም ጉሃሪ የተባሉ ግብጻዊ የሃይማኖት ሰው ከስምንት ረዳቶቻቸው ጋር ወደ ኢየሩሳሌም በማቅናት የይገባኛል ጥያቄ ካነሱበት ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዴር ሱልጣን የውዝግብ ማዕከል ሆኖ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ ነገስታት ትኩረት ባለመሰጠቱ ኢትዮጵያ በዴር ሱልጣን ያላት ይዞታ እየተሸረሽረ አሁን በገዳሙ ጣሪያ የሚገኘው አንድ ቤተክርስቲያን ብቻ ቀርቷል።
ግብጻውያን ይህንንም የቀረውን የኢትዮጵያ ይዞታ ለመንጠቅ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።
በየጊዜው በግብጻውያን በሚነሳ የይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ግጭቶች ሲፈጠሩ እንደነበረ የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ።
ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ የኢትዮጵያ ይዞታ በሆነ የዴር ሱልጣን ገዳም ጣሪያው ተደርምሶ በገዳሙ ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ የሚታወስ ነው።
መደበኛውን ቤተክርስቲያኒያዊ አገልግሎት መስጠት ያልቻለው ገዳሙ ለአንድ ዓመት ያህል በወሰደው ድርድርና ከእስራዔል መንግስት ጋር በተደረገ ስምምነት የእድሳት ተግባሩ እንዲከናወን ፍቃድ መገኘቱን ነው ለማወቅ የተቻለው።
ይሁንና ገዳሙ ተዘግቶ እንዲቀር በሂደትም ቁልፉን ከኢትዮጵያ እጅ ለመንጠቅ የፈለጉት ግብጻውያን እድሳቱ እንዳይከናወን ችግር መፍጠራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በትላንትናው ዕለት እድሳቱን ለማከናወን ወደ ገዳሙ የመጡትን የግንባታ ሰራተኞች እንዳይገቡ ለማድረግ የግብጽ የሃይማኖት አባቶችና ተከታዮች የገዳሙን መግቢያ በር በመዝጋት ብጥብጥ መፍጠራቸውን በቪዲዮ ተደግፎ ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በእስራዔል መንግስት ፍቃድ የተሰጠውን የእድሳት ተግባር የከለከሉት ግብጻውያን በሃይል የግንባታ ሰራተኞቹ ላይ የጣሉት ክልከላ ውደ ግጭት በማምራቱ የእስራዔል ፖሊስ ጣልቃ መግባቱም ተገልጿል።
ከፖሊስ ጋር ግብግብ ውስጥ የገቡት ግብጻውያን በመጨረሻም ፖሊስ በሃይል ከአካባቢው እንዲወገዱ አድርጓቸዋል።
ፖሊስ ግብጻውያን ጳጳሳትንና መነኮሳትን ጭምር በመጎተት ከስፍራው ካራቃቸው በኋላ የእድሳት ስራው ሊጀመር መቻሉ ታውቋል።
በዴር ሱልጣን የኢትዮጵያ ገዳም አበባት አባ ገብረኪዳን ሺፈራው ለኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልዕክት የእዳሳቱ ስራ እስከሚያልቅ በጸሎትና በማንኛውም እገዛ ኢትዮጵያውያን ከገዳማቸው ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
ግብጻውያን ከመንግስታቸው አንስቶ በእስራዔል ነዋሪ የሆኑት ተባብረው የኢትዮጵያን ይዞታ ለመንጠቅ እያደረጉ ያሉትን ግብግብ ኢትዮጵያውያንም በአንድነት ሆነው ገዳማቸውን እንዲታደጉትም ጥሪ ተደርጓል።
No comments:
Post a Comment