Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, October 15, 2018

የአፋር ልዩ ሃይል የተቃውሞ ሰልፍ ባደረጉ ወጣቶች ላይ ጉዳት አደረሰ


 በአዋሽ ሰባተኛ የአፋር ልዩ ሃይል የተቃውሞ ሰልፍ ባደረጉ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሙ ተገለጸ።
በአፋር ክልል የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ በቀጠለበት በዚህን ወቅት ልዩ ሃይሉ አዋሽ ሰባተኛ ላይ የወሰደው ርምጃ ቁጣን ቀስቅሷል።

በርካታ ወጣቶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአይን እማኞች ገልጸዋል።
የአፋርን ክልል የሚመራው ፓርቲ ለውጥ አደናቃፊ ነው በሚል በክልሉ በአብዛኛው አከባቢ የተጀመረው ተቃውሞ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ህወሃት በአፋር ክልል የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት የተቃውሞው አንዱ ጥያቄ መሆኑም ይነገራል። አፋሮች ፌደራል መንግስቱ ድምጻችንን ይስማ በማለት ላይ ናቸው።
አሁን ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ የአፋር ክልል ገዢ ፓርቲ አብዴፓ ለሁለት መሰንጠቁ ተሰምቷል።
አዋሽ ሰባተኛ ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ በሚወስደው መስመር ላይ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት።
ካለፈው ወር ጀምሮ በመላው አፋር ክልል የተነሳው ተቃውሞ አዋሽ ሰባተኛ ዛሬ ሲደርስ የገጠመው ብርቱ የታጣቂ ሃይል ርምጃ ነበር።
የአፋር ክልል አመራሮች ከስልጣን እንዲወርዱ በመጠየቅ የተጀመረው ተቃውሞ በአዋሽ ሰባተኛ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ የአዋሽ ሰባተኛው የተቃውሞ ሰልፍ ከወረዳው አስተዳደር ፍቃድ ተነፍጎት ነበር።
ወጣቶቹ ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ አይጠበቅብንም ብለው በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ለማድረግ አደባባይ ሲወጡ የአፋር ክልል ልዩ ሃይል ርምጃ መውሰዱን ነው የደረሰን መረጃ ያመለከተው።
በቆመጥና በመሳሪያ ሰደፍ ከፍተኛ ድብደባ የፈጸመው የአፋር ክልል ልዩ ሃይል የተቃውሞ ሰልፉ እንዲበተን አድርጎታል።
በዚህ ጥቃት ከ20 በላይ ወጣቶች ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ባለፈው ሳምንት በዘጠኝ የአፋር ክልል ወረዳዎች በተካሄደ ተቃውሞ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ስልጣን እንዲለቅና በሃገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ለውጥ ወደ አፋር እንዲገባ ተጠይቋል። መደመርም የአፋርን መሬት ይርገጥ ብለዋል ወጣቶቹ።
አሁን በደረሰን ዜና ደግሞ የአፋር ክልል ገዢ ፓርቲ አብዴፓ ለሁለት ተሰንጥቋል።

ለውጡን በሚደግፉና የነበረውን ስርዓት በሚያስቀጥሉ የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል በተፈጠረ ልዩነት ፓርቲው ለሁለት መከፈሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በህወሃት ይደገፋሉ የተባሉት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ስዩም አወልን ጨምሮ 19ኝ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ለውጡን እንደሚያደናቅፉና በነበረው አመራር ክልሉ መቀጠል አለበት ብለው አቋም የያዙ መሆናቸው ታውቋል።
የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመሩትና 17 ተጨማሪ አባላት ያሉት ሁለተኛው ቡድን የአፋር ህዝብ ለውጥ ያስፈልገዋል፣ አሁን ያለው አመራር ስልጣን ይልቀቅ የሚል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ዛሬ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ስዩ አወል ምክትላቸውን ጨምሮ 18ቱን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዛሬ ማገዳቸው ተሰምቷል።
የአቋም ልዩነት ያሳዩትና ለውጡን የሚደግፉት አባላትም ፕሬዝዳንቱን ማገዳቸው ታውቋል።
የአፋር ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አብዴፓ በህዝቡ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ምክንያት ለሁለት መሰጠንቁን ተከትሎ የጎሳ ግጭት ይከሰታል የሚል ስጋት እንዳለም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials