Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, October 25, 2018

ከኦብነግ ጋር ስለ ህዝበ ውሳኔ የተነሳ ነገር የለም ተባለ


ከኦብነግ ጋር በተደረገው ስምምነት ስለመገንጠልም ሆነ ህዝበ ውሳኔ የተነሳ ነገር የለም ተባለ።
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ከድር የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ባለፈው ቅዳሜ በአስመራ የተደረሰውን ስምምነት አስመልክቶ ‘’በሶማሌ ክልል ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ ከመንግስት ጋር ተስማምተናል’’ ማለቱን በሬ ወለደ ተረር ተረት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

ኦብነግ የሶማሌ ክልል ህዝብ እስከመገንጠል ድረስ ውሳኔ እንዲሰጥ ከመንግስት ጋር ስምምነት ላይ ደርሼ ነው ወደ ሀገር ቤት የምገባው ማለቱን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።
በጉዳዩ ላይ የፌደራሉ መንግስት እስከአሁን የሰጠው ይፋዊ ምላሽ የለም።
ለበርካታ ጊዜያት ተገናኝተዋል። አያሌ ድርድሮችን አድርገዋል። ለዓመታት እየተስማሙ፡ እያፈረሱ ቆይተዋል።
በሸፍጥ ላይ የተመሰረተ ድርድር እያለ የሚወቅሰው ኦብነግ ተደራዳሪዎቹ እየታገቱበትም ድርድሩን ማቆም አልፈለገም።
ከአመራሮቹ መካከል እየካዱ፡ ግንባሩን አፍርሰናል ብለው ከህወሃት አገዛዝ በተደጋጋሚ ሲስማሙ ቢቆዩም ህወሃትም ቀጣይ ድርድር ከመጠየቅ ኦብነግም ሳያቅማማ ጥያቄውን ከመቀበል ወደኋላ ብለው አያውቁም።
አንድም ጊዜ ግን የተሳካ ድርድር ሳያድርጉ የህወሃት አገዛዝ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ገብቷል።
ያለፈው ቅዳሜ በኤርትራ አስመራ የተደረገው የሁለቱ ወገኖች ድርድር ግን አንዳች ውጤት ላይ መደረሱን ነው ዘገባዎች ያመለከቱት።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ተደራዳሪውን ቡድን የመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ‘’የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር በሃገር ቤት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በመወሰን ከስምምነት ላይ ደርሰናል’’ ማለታቸው ተገልጿል።
ኢሳት ከኦብነግ አካባቢ ያገኘው መረጃም ግንባሩ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስኖ ወደሀገር ቤት ለመግባት መስማማቱን የሚያረጋግጥ ነው። የስምምነታቸው ዝርዝር መረጃ ግን ከሁለቱም ወገኖች አልተገልጸም።
ሆኖም የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ለቢቢሲ ሶማልኛ የሰጡት ቃለመጠይቅ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ምክንያቱ ደግሞ የአስመራው ስምምነት የሶማሌ ክልል ህዝብ ህዝበ ውሳኔ ማድረጉን የሚያካትት ነው ማለታቸው ነው።
የግንባሩ የውጭ ግንኙነት ፀሐፊ አቶ አህመድ ያሲን ሼክ ኢብራሂም ከኢትዮጵያ መንግሥት ስለደረሱበት ስምምነት አስመልክቶ እንደገለፁት የሶማሌ ህዝብ ዕጣ ፈንታውን በነፃነት ራሱ መወሰን እንዳለበት ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
በስምምነቱ መሰረትም የራስን ዕድል በራስ መብትን ለመወሰን ህዝበ- ውሳኔ እንዲካሄድና ህዝቡ ከኢትዮጵያ መገንጠል ከፈለገ ያ መብት እንዲከበር፡ መቆየትም ከፈለገ ያ ውሳኔ እንዲከበርለት ውሳኔ ላይ ደርሰናል ነው ያሉት የኦብነጉ ከፍተኛ አመራር አህመድ ያሲን ሼክ ኢብራሂም። ይህንንም ለማስፈጸም ከሁለቱም ወገኖች የተወጣጣ ኮሚቴ እንደሚመሰረት ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ስለአስመራው ስምምነት ግልጽ መረጃ ባለመቅረቡ የኦብነግ መግለጫ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።
ኢሳት ጉዳዩን በተመለከተ ከፌደራሉ መንግስት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ሆኖም በአስመራው ድርድር የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን አባል ሆነው የተገኙት የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ ዑመር በግል ማህበራዊ ገጻቸው ባሰራጩት ጽሁፍ ጉዳዩን በሬ ወለደ ተረት ተረት ሲሉ ነው ያጣጣሉት።
አቶ ሙስጠፋ እንደሚሉት አስመራ ላይ በተደረገው ንግግር ኦብነግ እንደ ሌሎች ትጥቅ ይዞ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ተቃዋሚዎች የትጥቅ ትግሉን አቁሞ ትግሉን በሰላማዊ መንገድ አገር ውስጥ ገብቶ ለማካሄድ ተስማምቷ።
ከዚህ ውጭ ስለ ህዝበ ውሳኔም ሆነ ስለ መገንጠልም የተነሳ ነገር የለም ሲሉ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጠበቀው በሶማሌ ህዝብ ፍቃድና ፍላጎት እንጂ በሌሎች ጩኸት አይደለም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ አቶ ሙስጠፋ ኡመር።
የሶማሌ ክልል ህዝብ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በሰላም ለመኖር የሚፈልግ ህዝብ ስለሆነ  የፓለቲካ ቁማርተኞች መጫወቻ ባያደርጉት ጥሩ ነው በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
በስተመጨረሻ ደግሞ ቢቢሲ አማርኛው ክፍል የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ስለ ሶማሌ ክልል ሕዝበ ውሳኔ የተናገሩት በሚል ያወጣው ሪፖርት ስህተት ነው ብሏል።
ስህተቱ እንዴትና በምን መልኩ እንደተፈጠረ ግን ያለው ነገር የለም።

No comments:

Post a Comment

wanted officials