ከፌደራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ሰመራ ገቡ
(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 16/2011)የአፋር ክልል ገዢ ፖርቲ አብዴፓ ውስጥ የተፈጠረውን መሰንጠቅ ተከትሎ ከፌደራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ሰመራ መግባታቸው ተገለጸ።ለውጡን በሚደግፉና በሚቃወሙ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አብዴፓ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ፓርቲውን ለሁለት መክፈሉ ታውቋል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ስዩም አወል ምክትላቸውን ጨምሮ የቀድሞ የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት ኢስማዔል አሊሴሮንና ሌሎች 18 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ትላንት አግደዋል።
በፕሬዝዳንቱ የታገዱት አመራሮችም በፊናቸው ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ የለውጡ አደናቃፊ የተባሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ማገዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ከፌደራል ወደ አፋር ያቀኑት ከፍተኛ አመራሮች አልታውቁም። የአፋር ህዝብ ተቃውሞውን ማሰማቱን ቀጥሏል።
የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አብዴፓ ለሁለት መሰንጠቁ በአፋር ህዝቡ እያሰማ ላለው ተቃውሞ ትልቅ ድል ተደርጎ እየተወሰደ ነው።
ፓርቲውን በአመራርነት የያዙት ሰዎች ከአዲስ አበባው የፌደራል መንግስት ይልቅ ለመቀሌው የህወሃት ቡድን ታዛዥ ናቸው የሚለው ተቃውሞ ላለፉት አራት ወራት የአፋር ክልል ከተሞችን አዳርሷል።
በተለይም የክልሉ ፕሬዝዳንትና የአብዴፓ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ስዩም አወል የህወሃት ረጅም እጅ በፓርቲው ውስጥ ጉልበት እንዲኖረው መፍቀዳቸው ጠንከር ያለ ተቃውሞ አስከትሎባቸዋል።
ህወሃቶች የአፋርን ጨውና ማዕድን በበላይነት እንዲቆጣጠሩና ፍጹም የበላይ እንዲሆኑ አድርገዋል የሚባሉት አቶ ስዩም አወል በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ አፋር ምድር እንዳይገባ ሲከላከሉ ነበር ተብሏል።
ባለፈው ሀምሌ ወር ወደ አፋር ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአፋር ወጣቶች ጋር እንዳይገናኙ ገደብ የጣሉት አቶ ስዩም አወል ከባህር ማዶ ወደ ሀገር ቤት የገቡ የአፋር የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አክቲቪስቶች ወደ ክልል እንዳይመጡ እንቅፋት በመፍጠር ክስ እንደቀረበባቸው የሚታወስ ነው።
የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ገአስ አህመድ በአዲስ አበባ መግለጫ በመስጠት የፌደራሉ መንግስት በአፋር እየተካሄደ ያለውን አፈና እንዲያስቆም መጠየቃቸው ተገልጿል።
ያለማቋረጥ በአፋር ክልል ለወራት ሲካሄድ የነበረው የህዝብ ተቃውሞ በዋናነት አቶ ስዩም አወል የሚመሩት የክልሉ አስተዳደር ስልጣን እንዲለቅ፣ እንዲሁም የህውሃት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም የሚጠይቅ ነው።
ከየአቅጣጫው ጫናው የበረታበት የአፋር ገዢ ፓርቲ ለሁለት መሰንጠቁ ሲገለጽ የህዝቡ ተቃውሞ ሰሚ እያገኘ ለመምጣቱ አመላካች ነው ተብሏል።
ፓርቲውን ለሁለት የሰነጠቀውም ለውጡን በሚቃወመው የአቶ ስዩም አወል ቡድንና ስልጣን ለቀን ለአዲስ አመራር እንስጥ በሚለው ምክትል ፕሬዝዳንቱ በሚመሩት እንጃ መሀል ነው።
ክልሉን ለረጅም አመታት የመሩት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል አሊ ሴሮም የህዝብ ድምጽ ይሰማ በልው አቋም መያዛቸውን ነው ያገኘነው መረጃ የሚያመልክተው።
ለሁለት የተከፈለው ፓርቲው የጎሳን መስመር መከተሉ ደግሞ በቀጣይ የእርስ በእርስ ግጭት እንዳያስከትል ስጋት ፈጥሯል።
አቶ ስዩም ፓርቲውም በጎሳ ለሚዛመዱት ሰው አስረክባለሁ ማለታቸው ስጋቱን ጨምሯል።
ሁለቱም ቡድኖች በየፊናቸው የእገዳ ውሳኔ ማስተላልፋቸው የተገለጸ ሲሆን ከህዝብ ወገን የቆመው የምክትል ፕሬዝዳንቱን ቡድን ለማጥቃት የአቶ ስዩም አወል አንጃ የህወሀትን ድጋፍ እየፈለገ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ዛሬ እንደተሰማው ደግሞ የአፋር ገዢ ፓርቲ መስንጠቅን ተከትሎ የሚፈጠረውን አደጋ ለማስቅረትና መፍትሔ ለመስጠት ከፌደራል መንግስት ከፍትኛ የኢህ አዴግ አመራር ቡድን ወደ አፋር አቅንቷል።
ስለአመራር ቡድኑ ዝርዝር መረጃ ባይገኝም እየተጠናከረ የመጣውን የህዝብ ብሶት መልስ ለመስጠት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ከውሳኔ መድረሱን የሚያመላክት ርምጃ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የአቶ ስዩም አወል አንጃ ከስልጣን ከተወገደ ህወሀት በአፋር የሰነዘረው ረጅም እጅ ሊቆረጥ የሚችል ነው ተብሏል።
No comments:
Post a Comment