በታጣቂዎች ተከበናል፣ለቃችሁ ውጡ ተብለናል፣ የሚደርስልን የለም የሚሉት የገዳሙ መነኮሳት በተኩስ ድምጽ ተሸብረናል በማለት ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ አቅርበዋል።
ከጥቅምት ሰባት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ገዳሙን ለቀው እንዲወጡ ከፍተኛ ማዋከብ እየተፈጸሙ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
የሜኤሶ ወረዳ አስተዳዳሪ ከታጣቂዎቹ ጎን በመሆን ገዳሙን ለቀው እንዲወጡ መነኮሳቱ ላይ ጫና እየፈጠሩ መሆኑም ተገልጿል።
መነኮሳቱ ቤተክህነትና መንግስት እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያትክ አቡነ ማቲያስ እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ላይ ካህናትንና ክርስቲያኖችን ማጥቃትና ማፈናቀል ቤተክርስቲያንን የማዳከም አንዱ ስልት ነው ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል።
የተመሰረተው በ13ኛው መቶ ክፍለዘመን ነው። መስራቹ ደግሞ አቡነ ሳሙዔል ነበሩ።
በአህመድ ግራኝ የወረራ ዘመን ጥቃት ደርሶባቸው ከጠፉ ገዳማት አንዱ ነበር።
ከእነደገና የተቋቋመው በ1911 እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው።
በቀድሞ ሀረርጌ ክፍለሀገር በአሁኑ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ሚኢሶ ወረዳ የሚገኘው የአሰቦት ገዳም፣ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተቆራኙ አጋጣሚዎችን አስተናግዷል።
በተለይም በሶማሊያ ወረራ ወቅት፡ በሶማሊያ ጦር ጥቃት የደረሰበት የአሰቦት ገዳም አብዛኛው ክፍሉ ወድሞ እንደነበር የታሪክ መጽሃፍት ያስረዳሉ።
በወረራው ጊዜ በገዳሙ የነበሩ ከ500 በላይ መነኮሳት ታቦት ይዘው አካባቢውን ጥለው የተሰደዱ ሲሆን ገሚሶቹ በሶማሊያ ጦር ታስረው ወደ ሞቃዲሾ መወሰዳቸውን ነው ለማወቅ የተቻለው።
ገዳሙ አሁን ያለበትን ገጽታ እንዲይዝና ዳግም እንዲሰራ ያደረጉት ቀዳማዊ ሃይለስላሴ እንደሆኑም ተመልክቷል።
በገዳሙ ታሪክ አሳዛኝ ተብሎ የሚጠቀሰው ሌላው ክፉ አጋጣሚ በ1984 ዓም እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር በአክራሪ ታጣቂዎች በተወሰደ ርምጃ 16 የገዳሙ መነኮሳት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው እንደሆነም ማስታወስ ተችሏል።
ገዳሙ በተለያዩ ጊዜያት ፈተና ውስጥ የከተቱት አጋጣሚዎች የተፈጠሩ ቢሆንም ሰሞኑን የተከሰተው ግን አደገኛ እንደሆነ ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ የሚያመለክተው።
ሃራ ተዋህዶ የተሰኘው በቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ የሚያተኩረው ድረ ገጽ እንዳተተው የገዳሙ መነኮሳት የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው።
ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ገዳሙ በታጣቂዎች ተወሯል። በቁጥር 25 የሚሆኑ በነፍሰ ወከፍ መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች በገዳሙ ይዞታ በሆነው ደን ውስጥ ድንኳን ተክለው መነኮሳቱ ላይ በመተኮስ እያስፈራሩ ናቸው።
ታጣቂዎቹ የኦነግ ወታደሮች መሆናቸውንና በደን ውስጥ የሚገኙትም የሶማሌ ጦር ወደ ገዳሙ ይገባሉ የሚል መረጃ ደርሶን ነው በማለት ምላሽ ነው መስጠታቸውን ነው የተናገሩት መነኮሳቱ።
ሆኖም የኦነግ ታጣቂ መሆናቸውን የሚናገሩት ወታደሮች ገዳሙን ለቀን እንድንወጣ እያስፈራሩን ነው፣ ከበው በተኩስ እሩምታ ሰላም እያሳጡን ነው ያሉት መነኮሳቱ አቤት የምንልበት አጥተናል ብለዋል።
የሜኤሶ ወረዳ አስተዳዳሪ ለመነኮሳቱ ጥበቃ እንዲደረግ ከምዕራብ ሀረርጌ ዞን ትዕዛዝ ቢተላልፈላቸውም ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ገዳሙን ከከበቡት ታጣቂዎች ጋር አብረው መነኮሳቱ አከባቢውን ለቀው እንዲሄዱ በማስፈራራት ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
ባለፈው ሰኞ ከምሽቱ 2 እስከ 4 ሰዓት የቀለጠ ድምጽ ይሰማ እንደነበርና በትላንትናው ዕለት ሌሊት ሁለት አብሪ ጥይቶች ወደ ገዳሙ መተኮሳቸውን ገልጸዋል።
መነኮሳቱ የ1984 ዓይነት ዕልቂት እንዳይደገም ስጋት ውስጥ ገብተናል ያሉ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዱሱ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንዲያስታውቅላቸው ጠይቀዋል።
በጉባዔ ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፓትሪያርኩ አቡነ ማቲያስ ካህናትንና ክርስቲያኖችን ማፈናቀልና ማጥቃት ቤተክርስቲያኒቱን ለማዳከም እየተወሰዱ ካሉ ስልቶች አንዱ ነው ማለታቸው ተገልጿል።
No comments:
Post a Comment