Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, December 13, 2018

መሸፈት ደግ ነዉ ለስልጣን ያሳጫል

ሰመረ አለሙ semere.alemu@yahoo.com
እምዬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሺ ቀርቶ የገደለሺ በላ የሚባለዉ አባባል ለረጂም ዘመን ስሜት ሳይሰጠኝ ቆይቶ ዛሬ ተግባራዊነቱ ላይ ደርሻለሁ።
ቀደም ባለዉ ጊዜ ሰርቶና ጥሮ ግሮ መኖር ያልሆነለት  ዋልጌ ወሮበላ ሰርቶ አዳሪዉን ቀምቶ፤ ገበያተኛዉን አድፍጦና አስበርግጎ፤ መተዳደሪያዉን ነጥቆ፤የሀገር ሰላም አደፍርሶ በዚህም ተፈርቶና ተጠልቶ ተረግሞ ይኖር ነበር። ተፈጥሯዊ ህግ ነዉና በዚህ ዉንብድናዉ እስከ መጨረሻዉ መቀጠል ባለመቻሉ በመጨረሻዉ  የሰዉ እርግማንና ጥላቻ ተደማምሮበት የክፉ ስራዉ  ስበቱ ሲያመዘን በዱላ፤ በገመድ ከቀናዉም በጥይት ተደብድቦ ሳይሰቃይ ያልፋል ሬሳዉም ሰብአዊ ክብር ሳይሰጠዉ በመንገድ ተጎትቶ ለሌላዉ በመቀጣጫነት ያገለግል  ነበር። ልቡ በቁጭት የነደደዉ የባህር ዳር ወጣትም  በረከት ስምኦንን አለበት በተባለዉ ቦታ ቢያገኘዉ እጣ ፈንታዉ ከዚህ የተለየ አይሆንም ነበር።  

ወደዚህኛዉ ዘመን ስንሸጋገር ደግሞ ሺፍትነት የሚጀምረዉ ከጫካና ከመንደር ሳይሆን ከትምህርትና ከነገድ ተቋማት ነዉ። ጥቂት ጀብደኞች አብዛኞቹ በእጽ ሀይል ተገፋፍተዉ ትምህርቱም ሲከብዳቸዉ ሌላ ሀገር የተደረገዉ እኛስ ለምን ይቅርብን በሚል ፉክክር ትርፍ ያመጣል ብለዉ ያሰቡትን ርእስ/ብሶት/ጭቆናን ፈጥረዉ የራሳቸዉን ትርክት ጨምረዉ ተረታቸዉን በእዉቀት ለተጎዳዉና ማገናዘብ ለቸገረዉ ዜጋ በማር ለዉሰዉ ይግቱታል።  ቆየት ብለዉ  ሀይል ሲያገኙ ደግሞ እንደ ህወአት፤ ኦነግ፤ ኦብነግ፤ ኤነግ …ግ  በተራቸዉ አልቀበል ያላቸዉን በጥይት/በዱላ/በቡጢ ደብድበዉ ሃሳባቸዉን አፍንጫዉን ይዘዉ ይግቱታል።ጥቂቶች በግል የጀመሩት ብሶት፤ አመጽ፤ትርክት በግድ ህዝባዊ መልክ እንዲኖረዉ ይደረጋል ከድግግሞሽ  ብዛት ሳናዉቀዉ እኛም የህዝብ ተወካዮች አድርገናቸዉ ትርክታቸዉ ዉስጥ እንወድቃለን። ይህ ነዉ የሆነዉ ባለፉት 40 እና 50 አመታት። ይህ ባይሆን የትግራይ ህዝብ  በአእምሮዉ ለማሰብ እድሉ ቢሰጠዉ እንዴት ህወአትን ሊቀበል ይችላል? ኦሮሞም የእነ ዳዉድ/ሌንጮ/በያን ሀሳብ ከነገረሱ ዱኪ ከራስ ጎበና በላይ ባላከበረዉ ነበር።  እዉነት ለትግራይ ነገድ የአልቤኒያ ኮሚኒዝም በነመለስ የታዘዘለት ከኢትዮጵያዊነት በልጦበት ነዉ አረጋዊ በርሄን አምኖ የህወአትን ትርክት የተጋተዉ? እዉን የኤርትራስ ህዝብ የአፈወርቂና መሰሎቹ ተረት ከታላቅ አገር ዜግነት በልጦበት ነዉ? ጊዜ  እየመለሰዉ ነዉ ወደፊትም ብዙ እናያለን።
ዶ/ር አብይ ስለ ምርጫዉ ተቃዋሚ ተብዬዎችን ሰብስቦ ሲያናግራቸዉ አንዳንዴም እየተቁነጠነጡ አንዳንዴም ከዶ/ር አብይ ቀድመዉ ሃሳብ እንስጥ የሚሉ የዶ/ር አብይ ወዳጂ መስለዉ ክሬዲት ለማስቆጠርና ለመታጨት የሚጨናነቁት ከመግቢያዉ ላይ ከጠቀስነዉ  ሺፍቶች ብዙም የተለዩ አይደሉም። ልዩነታቸዉ  ጸጉራቸዉ የተበጠረ ነዉ፤ ሱፍ ይለብሳሉ፤እንደ ዘመኑ አቀራረብ እንግሊዝኛ ጣል ጣል ያደርጋሉ። ሆኖም የእዉቀታቸዉን ልክ የሚለካ የምርምር ስራዎቻቸዉን ግን  አስነብበዉን  አያዉቁም ብቻ ህዝቅኤል ጋቢሳ ስለ ጫት መጻፉን በአንድ ወቅት አንድ ጽሁፍ ላይ የተነበበ ይመስለኛል ከዚህ በተረፈ የነሱ ልዩ እዉቀትና ስልጠና በተስፋዬ ገ/አብ ትእዛዝና ትምህርት ዜጋን ከዜጋ ማጋጨት እንደምንም ተንሸራቶ ፖለቲካ ዉስጥ ተሸጉጦ መተዳደሪያቸዉን ማመቻቸት ነዉ። 
 ዲማ ነገዎ እሱም ፕሮፌሰር ነዉ መሰል በአንድ የቴሌቭዥን ገለጻዉ በጸጸት ” የአድዋዉን ፊታዉራሪ ገበየሁ ባልቻን አንዴት ኦሮሞ መሆኑን እንዳልሰማ  ሀዘኑን በቁጭት ገልጿል”።ፊታዉራሪ ገበየሁ ባልቻ ነገዱን  ሳይጠየቅ እነ ዲማ ነገዎ በጭራቅ ምስል የሳሏቸዉ አጼ ምንሊክ የኢትዮጵያን ጦር እንዲመራ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ጦር አዛዥ አድርገዉ  ሹመዉት ነበር።ነገዱ ሳይሆን ሀገሩ ለሰጠችዉም ክብር ተመሳሳይ ዋጋ ለመስጠት ገበየሁ የሚያዝዘዉ ጦር እንደ መላላት ሲል የተሰጠዉ ክብርና ሃላፊነት ስለ ከበደዉ ለተዋጊዉ ምሳሌ ለመሆን “ስለ እኔ ወደ ሸዋ በህይወት የሚመለሱ ይናገሩ” በማለት ፈረሱን የሽምጥ ጋልቦ የጦርነቱ እሳት  ላይ ወደቀ እነ ዲማ/ሌንጮ/ዳዉድና መሰሎቻቸዉም አዉሮፕላኑን ከጭብጥ ገንዘብ ጋር አስቀዝፈዉ በስምምነት ወደ ሚያመቻቸዉ አገር ነጎዱ። ገበየሁ ዉድ ህይወቱን  ሳይሳሳ ለነገዱ ሳይሆን ለሀገሩ ሰጠ፤ ምሳሌነቱም ሀገሩን በሚወድ ዜጋ ዘወትር  ሲታሰብ ይኖራል። ከአድዋዉ ድል በሗላም ንጉሰ ነገስቱና የኢትዮጵያ ጦር በገበየሁ ሞት  ከልብ አዘኑ የጦርነቱን ድልም ድባብ ጣለበት።ገበየሁ ከነ ዲማና ከእነ አረጋዊ በርሄ  በላይ በኢትዮጵያዉያን ይከበራል ይዘከራል ኢትዮጵያ ትኖራለች እስካለችም ድረስ ትዉልድ እየተቀባበለ ዉለታዉን ያስታዉሰዋል እነ ዲማና ሌንጮ አረጋዊ ግን በህይወት እያሉ ተረስተዋል። 
በአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ እንጂ ዘሩ ባለመጠየቁ የተደራጀዉን የጥልያን ጦር  ዉጊያ ደረማምሶት ገባ በነዲማ/ዳዉድ/በያን ሱጳ፤ሌንጮ/አረጋዊ  ዘመን ግን ሰዉ በነገዱ ስለተሸነሸነ ትንሿን የዚያድ ባሬን ጦር መቋቋም ተስኖን የሆነዉን አሁን ያለዉ ትዉልድ የሚረዳዉ ይመስለኛል።በእንደነዚህ አይነት የአንድነት ጠላቶችና በክፉ የተመረዙ ግለሰቦች የወደፊት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊቋጭ ዝግጂቱን ማየት በእጅጉ ያሳስባል። ዲማና መሰሎቹ  ሳያዉቁት የሚነገሩን በዘር ልክፍት በመለከፉቸዉ ምክንያት መሳሪያና ወታደሩን ከመቁጠር ይልቅ  ማን የማን ነገድ መሆኑን አድዋ ጦርነት ላይ እንድንመዘግብላቸዉ ነበር የፈለጉት እንዲህ አይነቱን ሰዉ ነዉ ፈረንጂ ዶፍቶር/ፕሮፌሰር እያደረገ ለአፍሪካ የሚልከዉ።
ወገኖች ኦነግን የትኛዉ የኦሮሞ ነገድ ተሰብስቦ ነዉ አንተ ምራን ብሎ ሌንጮን ወይም ዳዉድን የጠየቀዉ? አረጋዊና ህወአትንስ የትኛዉ ትግሬ ነዉ እናንተ ካልመራችሁን ብሎ በድምጽ ብልጫ የተማጸናቸዉ? ኦጋዴንም ሌላዉንም። ዶ/ር አብይ እንዳለዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተቃዋሚ ነን ብለዉ እንቅስቃሴ ያደረጉት መሪዎቹ አንዱም አልሞቱም ተምረዉ ተመችቷቸዉ ሀብት ይዘዉ ይኖራሉ የሞተዉ የድሀ ልጅና እነሱን አምኖ የተመመዉ የዋሁ ወጣቱ ነዉ በአባባሉ እስማማለሁ። ታድያ ይህን ባለ ማግስት እነዚህ መሰሪዎች እነዚህ የህዝብ ዉክልና የሌላቸዉ ወንጀለኞችን ከፊት ለፊቱ ቁጭ አድርጎ ስለ ምርጫ ሲያናግራቸዉ ማየት ትንሺ ግር ያሰኛል።
እስቲ ሁሉም ተመሳሳይነት ቢኖራቸዉም አረጋዊ በርሄን ነጥለን እናዉጣዉ። ዶ/ር አብይ አንዳንዴ እንደ ኮሜድያን ነዉ ቀልድ በጣም ይችላል አቶ አረጋዊ በርሄ ብሎ በስብሰባዉ ላይ ሲጠራዉ ያለምክንያት አልነበረም። አረጋዊ በርሄ የዱፍትርና መመረቂያዉን የጻፈዉ ህወአት ስለተባለዉ ወንጀለኛ የናዚ ስብሰብ የመላእክት ጥርቅም ለኢትዮጵያ ደግ አሳቢ አድርጎ ስሎ ነዉ  እንዲህ አይነት ጥናትና ትርክት ለእዉቀት አስተዋጽኦ ባይኖረዉም ፈረንጆቹ አረጋዊ ስለ ኢትዮጵያ የሚፈልጉትን ሁሉ ካቃበላቸዉ በሗላ ደስ ይበለዉ ብለዉ ወረቀቱን ወርዉረዉለት ይሆናል። ምናልባትም አበበ ገላዉ ምርመራዉን ቢያጠናክር ላይኖረዉም ይችላል። ለማንኛዉም ሆላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንም አይንህ ላፈር ስላሉት እስቲ ማን ማንነቱ በማይታወቅበት ትልቅ ሀገር ሂጄ እድሌን ልሞክር በማለት ወደ አሜሪካ አቀና። እዛም ሳይጠራ በየስብሰባዉ አዘጋጆቹ ጎን በመቀመጥ ከአጀንዳዉ ጋር ያልተያያዘ ጥያቄ በመጠየቅ በማሳከር ወደ ሚዲያ ተቋማት እየደወለ ጠይቁኝ እያለ በማሰልቸት የፖለቲካ ተክለ ሰዉነቱን ገነባ። ተቃዋሚ ነኝ ብሎ በተገኘበት ቦታ ሁሉ መለስ ዜናዊን እንጂ ህወአትና አስነዋሪ ስራዉን ሳይተች ለዳግም ጥፋት የመለሰን ሌጋሲ በእሱ መንገድ ሊያስቀጥል ወደ ዶክተር አብይ ጉባኤ አቀና። 
በተመሳሳይ ሁኔታ ናቅፋ ላይ 5000 የትግሬን ወጣት መርቶ የኢትዮጵያን ወታደር ለእርድ ያቀረበ አርከበ እቁባይ 6 ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ዶፍቶር ተብሎ መመለሱ ተነግሮናል የመመረቂያዉ ጽሁፉም  ኢፈርት ስለተባለ የዘረፋ ቡድን እንደሆነ ይነገራል።  ይህ የሌባ ድርጅት ህገወጥ ስምምነቶችን አድርጓል፤ የተበደረዉን የህዝብ ገንዘብ መጥፎ ብድር በማለት አሰርዟል፤በጠራራ ጸሀይ ቡና ከዲፖ አሰርቋል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁሉ ወስዶ ለራሱ አድርጓል።  ምርመራዉ ሲጀመር  የአርከበ ጥናታዊ ጽሁፍም ከግምት ይገባል የሚል እምነት አለን አርከበም በጻፈዉ በራሱ ማስረጃ ወደ ቃልቲ ይወረወራል (ፍትህ በኢትዮጵያ መጥቷል ከተባለ) ፈረንጅም የጋዳፊን ልጅ የሀሰት ዱፍትርና እንደቀማዉ ሁሉ ከአርከበም ተቀምቶ ዶክተር የሚለዉ ያለችሎታዉ የተሰጠዉ ማእረግ በሚገባዉ ማእረግ በአቦይ  ይተካል።
ወገኖች በጣም ያሳዝናል በኢትዮጵያ ዉስጥ  እየተሺከረከረ ብሄራዊ ባህላችን የሆነዉ የገደለንን ሀገር ላይ ያመጸን የከዳን ባንዳ ማክበርና ማባባል ነዉ። አጼ ሐይለ ስላሴ ባንዳ ሆዳም ነዉ ምቾት ይወዳል ጥልያን የሰጠዉ ምቾት ቢቀርበት እራሱን ይሰቅላል አገር ጤና ይነሳል ብለዉ በማሰብ የአንድነት ሀይሉ የትም አይሄድም አገሩን ይወዳል በሚል መንፈስ ባንዳዉን ሲንከባከቡት የአንድነት ሀይሉ አኩርፎ የሰሜን የአገራችንን ከፍልና የባህር በራችንን በኩርፈኞች ተነጠቅን። ለዚህም አረጋዊ በርሄና ድርጅቱ ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ።
በዶር አብይ ዘመንም  በመጥፎ ሃሳብ የተመረዙ ተቃዋሚ ነን ባዮችን በመለመን፤ በማክበር፤ ሆቴልና ዊስኪ በማቅረብ ፤ ወደ ሀገር ቤት በማስገባት ህዝቡ ተስፋ የጣለበት የቲም ለማ ራእይ እንዲጨልም ሆነ። ይህ በመሆኑም ዳዉድ ኢብሳ በድፍረት ማን ማንን ትጥቅ ያስፈታል ብሎ በድፍረት ተናገረ ሁለተኛ መንግስት መሆኑንም ጠቆመ ራቅ ብሎ ያልቻለዉን ከዉስጥ እንዲበትነን ህጋዊ ፈቃድ ተሰጠዉ። ኦቦ ጁዋር መሀመድም ከፈለግሁ ኦሮምያን መገንጠል ማን ከለከለኝ ብሎ በብሔራዊ ቴሌቭዥን ደሰኮረ የህወአትን ማኒፌስቶ የቀረጸዉ አረጋዊ በርሄ  ከዶር አብይና ከበታች ሹማምንት ቀድሞ ሀሳብ ሰጭ ሁኖ ተገኘ፤’ ከጅምሩ የወደፊቱ ጉዟችን ተስፋ መጨለሙም በገሀድ ታየ። እነዚህ ግለሰቦች በሺፍትነቱ ዘመን በተለያዩ ወንጀሎች የተሳተፉ ህይወት የቀጠፉ ወሮበሎች  ቤታቸዉ ቃልቲ መሆን ሲገባዉ መፍሄ ፈላጊ ሁነዉ መታየታቸዉ እዛ አገር ምን እየተሆነ እንደሆን መረዳት ይከብዳል። 
አረጋዊ በርሄ የህወአት ፈጣሪ፤መሪ፤የወታደራዊ ክንፍ አዛዥ ሁኖ በሰራበት የሽፍትነት ስራዉ በትግራይ የሚኖሩ አፍቃሪ ኢትዮጵያዉየንን ከመፍጀት ባሻገር የመንግስት ተቋማት ላይ ከፍተኛ በደልና ዘረፋ የፈጸመ  የዜጋን ህይወት በመቅጠፍ ቀጥተኛ አመራር በመስጠት የተሳተፈ መሆኑ እየታወቀ ሰዉ እንደጠፋ ሁሉ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ሃሳብ ሰጭ ሆኖ ስናየዉ ልባችን አዝኗል።  ጌታቸዉ አሰፋን እያደኑ አረጋዊ በርሄን ህገ መንግስት አርቅቅ፤ ሀሳብ ስጥ፤ በፖለቲካ ተሳተፍ ብሎ መጋበዝስ ምን የሚሉት ትያትር ነዉ? ለመሆኑ አረጋዊ በርሄ ድርጂት አለዉ ወይ? ግደይ ዘርአጽዮን አንዱ ወንጀለኛ የድርጅቱ አባል ነዉ ሁለት ሰዉ ድርጅት ሁኖ እንዴት የኢትዮጵያን መጻኢ ጊዜ ከሌሎች ጋር በግርግር ተቀላቅሎ እንዲወስን ይፈቀድለታል? ጎበዝ የሰዉ ደሀ አይደለንም ከታሪክ እንማር እንጂ ኤርትራ ወደ እናት አገሯ ስተቀላቀል እንደነዚህ አይነት መርዘኛና ወንጀለቾችን ከአንድነት ሀይሉ በላይ ክብር ሰጥተን በመፍትሄ አሳትፈን ችግሩ ለዚህ ትዉልድ ተረፈ። በነ አረጋዊና በእነ ሌንጮ/ዳዉድ… ስንገረም እነ ስለሺም ሰብሰብ ብለን ድርጅት እንፍጠር ብለዉ ተሰባስበዋል መሰል ወይ ጣጣ ስንቶቻችን እናዉቃቸዋለን እነዚህን ሰዎች?።
ጎበዝ ስለ ቤተሰብ አይደለም የምንመክረዉ አረገዊ በርሄና ግደይ ዘራጽዮን በክብር ተጠርተዉ የወንጀላቸዉ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከነሱ በተጻራሪ ከኢትዮጵያዊነት ጋር የቆሙ ህወአት በነብስ የሚፈልጋቸዉ እነ አቶ ገ/መድህን አርአያ እነ አቶ ጌታቸዉ ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)  ምን ይሰማቸዋል?  በነገራችን ላይ ከ30ሚሊዮን በላይ የአማራን ህዝብ በስምም ሆነ በመልክ የማያዉቀዉን አማራን በጠላትነት ፈርጆ በፖሊሲ ደረጃ ሲንቀሳቀስ የነበረዉ የህወአቱ አረጋዊ በርሄና የህወአትን አስተሳሰብ ተግተዉ ስፍር ቁጥር የሌለዉን አማራ የፈጁ እነ ዳዉድ ኢብሳንና ሌሎች ኦነጎችን ጨምሮ  በዚያ መድረክ ላይ መገኘት አሁንም የአማራን ህዝብ ከመጥላትና ከመናቅ የመጣ ስለሆነ የአማራ ነገድ ለሚመጣዉ ክፉ ዘመን እራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል እላለሁ። 
ምንም እንኳን አበክረን ይህ የነገድ አስተዳደር ጥቅም እንደሌለዉ ብንገልጽም ዶ/ር አብይ  በአንድ ስብሰባ  ጁዋር መሀመድና ኦነጋዉያን  በተደጋጋሚ እንደሚነግሩን ስልጣን ለመያዝ የብሄር ስብጥር በግድ መኖር አለበት  ብለዉናል። ይህ አካሄድ አሁንም ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን  በተደጋጋሚ ያለመሰልቸት  ብዙ ወገኖች በምሁር እይታ ስጋታቸዉን ገልጸዋል። ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከተከበረና ከተካበ ነገሮች ሁሉ በዜግነት እሳቤ ከገቡ ኢትዮጵያዊ ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌልኛዉ ጫፍ አገሬ ነዉ ብሎ ካመነ የዘር ኮታ ከሚሰጠዉ በላይ የዜግነት እሳቤ ጥቅም መስጠቱን በተለያዩ አስተዳደሮች ተመልከትናል። ሐኪም ወርቅነህ፤ቡልቻ ደመቅሳ፤ክፍሌ ዳዲ፤ኮማንደር ዘለቀ፤ዳዊት ዮሀንስ፤ጸሀዩ እንቁስላሴ ፤ ገርማሜ ነዋይ ከብዙ በጥቂቱ  በተመደቡበት አካባቢ ለትዉልድ ቀያቸዉ ከሰጡት አገልግሎት በላይ ታላቅ ስራ በመስራታቸዉ ስማቸዉ ዘወትር በአካባቢዉ ነዋሪ ከሚዘከርላቸዉ ስመ ጥር ዜጎች ጥቂቶቹ  ናቸዉ። ይህ በብሄርና በሀይማኖት ስብጥር የሚደረገዉ አስተዳደር ለሃሳቡ አራማጆች መተዳደሪያ ይሰጥ ካልሆነ በስተቀር  ለአንድነትና ለመልካም አስተዳደር ምንም ጥቅም እንደሌለዉ እያሳሰብን እንግለዞችና ፈረንሳዮች በመካከለኛዉ ምስራቅ በነገድና በሀይማኖት አቧድነዉ አካባቢዉ ምስቅልቀሉ ሲወጣ እነሱ ዳኛም ፤ አስታራቂም፤ መሳሪያ ሻጭና ህንጻ ገንቢም  ሁነዉ ከወንጀሉ ተጠቃሚ ሆኑ እንጂ አካባቢዉ አሁንም የጦር አዉድማ ከመሆን በስተቀር የተፈለገዉ ሰላም አልመጣለትም ።
 ዶ/ር አብይ፤ ገዱ አንዳርጋቸዉ፤ለማ መገርሳ፤ብርቱካን ሚደቅሳ  ጊዜ ወስደዉ እነዚህ የጦር ወንጀለኞችን የዜጋን ህይወት በጥይት የቀጠፉትን፤ በዘረፋ የተሳተፉትን  እንደ ነጻ አዉጭና ተቃዋሚ ሁነዉ የቀረቡትን ድርጅቶች በገፍ እንደ ተቃዋሚ ድርጅት ከመዉሰዽ ይልቅ  የኢትዮጵያ ህዝብ መክሮበት ፕሮግራማቸዉ ታይቶ የአባሎቻቸዉ ብዛት  ተቆጥሮ በዘመናቸዉ ከወንጀል ነጻ መሆናቸዉ ተረጋግጦ በግልጽ ሃሳቡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተሺጦ ተቀባይነት ካገኘ በሗላ በዚህኛዉ ሳይሆን ለወደፊት በሚመጣዉ ምርጫ እንዲሳተፉ እንዲደረጉ እንደ ዜጋ እያምላከትኩ ይህ ባለመሆኑ ግን  እስከ መርዛቸዉ ገብተዉ እንዲያቦኩ ከተፈቀደ ነገሩ ሁሉ ታጥቦ ጭቃ ከመሆኑም በላይ  ዉጤቱም ያለ ጥርጥር የከፋ ይሆናል። ተስፋ የተጣለባቸዉ መሪዎቻችንም በእጅ ጠምዝዝ ፖለቲካ እጅ መስጠት እንደሌለባቸዉም ከወዲሁ ማመላከት እንወዳለን። 
ዶ/ር አብይ ገዥም ተቃዋሚም ሁኖ ለነዚህ በሀሳባ ለተጎዱ ተቃዋሚ ነን ባዮች ሰብሰብ በሉ 3 በቂ ነዉ ብሎ ሃሳብ ሲሰጥ ጩሉሌዉ አረጋዊ በርሄ ዶር አብይ ከመጨረሱ  ምናልባት ሃሳቡን ሊለዉጥ ይችላል ብሎ በመስጋት  ሃሳቡን የተቀበለዉ ያለምክንያት አልነበረም። ሰዉየዉ ተንኮልን ተክኖበታል የድርጅት አባላትም የሉትም አረናል ትግሬ ከተባለዉ የአብረሀ ደስታ ድረጅት ጋር ካልተደመረ በስተቀር። አረጋዊ ሁለት መሰረታዊ ፕሮግራሞች አሉት አንዱ ጊዜ ጠብቆ እርቅና ሰላም የሚለዉን ከማንም በላይ አጉልቶ ማጮህ ነዉ በዚህም ሁለት ጥቅሞችን ያገኛል ይኸዉም የህወአት ወንጀለኞችን ከህግ ተጠያቂነት ማዳን ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ እሱም በዚህ ግርግር ከሰራዉ ወንጀል ነጻ ሁኖ የፓርላማ ወምበረን በማግኘት ዶ/ር አብይን በመማጸን ያሰበዉን ክፉ ስራ ማስፈጸም ይሆናል። ጎበዝ ደቡብ አፍሪካ ሌላ ኢትዮጵያ ሌላ በደቡብ አፍሪካ ወንጀለኞች ወንጀላቸዉ ተፍቆ ቀደም ሲል የያዙትን እንደያዙ ሳይሳቀቁ ተንደላቀዉ እየኖሩ ነዉ የሞተዉ የቆሰለዉ አካሉ የጎደለዉ ከነ ስቃዩ ይኖራል የእነ አረጋዊ ፕላንም በዚህ መልኩ እንዲቀጥል ነዉ። ፍትህ ለያንዳንዱ ዜጋ መድረስ አለበት የሺብሬ ደሳለኝን መስዋትነት አንርሳ። 
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ መሪ ይሄዳል ይመጣል መሪዎች የሚያደርሱት በደል መከራዉ ላንተ ነዉ ይህ እንዳይሆን መሪዎችህን ከመምረጠህ እድሉን ከመስጠትህ በፊት የሀገርና የአንድነት ፍቅራቸዉን ካደረጉት አስተወጽኦና ከሰሩት ወንጀል ጋር በማነጻጸር በድምጽህ ቅጣቸዉ እምቢ በላቸዉ አንተ አምጽ እንጂ እነሱ እንዲያምጹብህ እድል አትስጣቸዉ ስንቴ ያታልሉሀል ቀላማጂ ምላሳቸዉን ሳይሆን ስራቸዉን መርምር። ሐይል የህዝብ ነዉ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

No comments:

Post a Comment

wanted officials