Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, December 9, 2018

የአዲስ አበባ ሁሉን-አቀፍ ንቅናቄ (አሁን) ምስረታ መግለጫ


ይህ መግለጫ የአዲስ አበባ ሁሉን-አቀፍ ንቅናቄ (አሁን) ምስረታን ያበስራል። አሁን ‘የአዲስ አበባ ባለቤትነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ነው’ የሚልን መሪ ሃሳብ የማእዘን ድንጋይ አድርጎ የተመሰረተ ሲሆን – የምስረታውም ዋነኛ ዓላማ ይህን እሙን ሃቅ በሃገራችን ፖለቲካዊ፥ ኢኮኖሚያዊና፥ ማህበራዊ መስተጋብር ይረጋገጥ ዘንድ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ማስተባበር ነው።

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ከአንድ ምዕት ዓመት በላይ ያገለገለችው አዲስ አበባ ሰበአዊነትን፥ አብሮነትን፥ መከባበርን፥ መወዳጀትን፥ መፋቀርን፥ መዋለድን እና መወሃድን በጎሳና ሃይማኖት ሳትገደብ ከሁሉም ማንነት በጎ በጎውን ወስዳ አዲስ የበለጸገ ማንነት (ዜግነት)ለሁሉም ያለ ልዩነት ያጎናጸፈች፣ እነዚህን ድንቅ እሴቶች የተላበሰ ‘አዲስአበቤ’ ማንነትም መፍጠር የቻለች የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ልብ የሆነች ከተማ ናት፡፡
ሆኖም ግን በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት መሰረት፤ በቋንቋ ላይ የተመሰረተው “የብሔር-ፌደራሊዝም” መዋቅር፤ የአዲስ አበባን ሕብረ-ብሔራዊነት እና ብሔር ዘለል ሕብረ-ቀለማዊ ማንነት የሚያስተናግድበት አስተዳደራዊም ሆነ ርዕዮት-ዓለማዊ ማዕቀፍ የለውም፡፡ አገሪቱን በብቸኝንት ሲገዛ የኖረው የሕውሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ቡድንም ይህንኑ የመዲናይቱን ህልው እና ብዝሃ-ስብጥራዊ ማንነት በመካድ የዘረጋው የመዲናይቱ የአስተዳደርና የአገዛዝ ቀመር፤ በብሔር ተዋፅዖ እየተሰላ የሚሰፈር፤ ከላይ ወደታች፤ የሆነ ሹመት መሆኑ በሚገባ ይታወቃል። አዲስአበባም በዚህ ህገመንግስታዊና መዋቅራዊ በደል ሳብያ በአሁን ወቅት በዘውጌ የፖለቲካ ቡድኖች ወዲህና ወድያ የምትላጋ፣ ስለእራሷ የማትወስን ከተማ ናት፡፡ ስለሆነም፣ ነዋሪዎቿ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ተነጥቀዋል፡፡ በፈቃዳቸው የሚሾሙትና የሚሽሩት እነርሱን የሚመስልና ተጠያቂነቱ ለእነርሱ የሆነ አስተዳደር እንዳይኖራቸው ሆነዋል፡፡ ህልውናቸውና ማንነታቸው ከህግና ከፖለቲካ ምህዳር ላይ ተፍቋል፡፡ ከገዛ ከተማቸው ባለቤትነትም ተሽረዋል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ አዲስ አበባን ብሎም ነዋሪዎቿን ዜጎች እንዳልሆኑ ሁሉ፣ በሰፋሪነት የመፈረጅ፣ በጠላትነት/ደመኝነት የመመልከት ክፉ አባዜ በሰፊው “የአክራሪ ብሔረተኛ የፖለቲካ ኃይሎች” ዘንድ ገኖ ይታያል። ይህም በከተማዋና ነዋሪዎቿ ላይ አብይ የደህንነት ስጋት ደቅኗል፡፡ የአዲስ አበባን ህብረ-ቀለማዊ ማንነት እና የአዲስአበቤዎችን ከተማ ወለድ እሴቶችንና ፍላጎቶችን ከግምት ያላስገባ (ያላገናዘበ) የፖለቲካ አስተዳደር ዛሬም የአዲስአበቤዎች ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል።
ይህንን ሁናቴ በሚገባ በመረዳትና ከመደራጀት በቀር ምርጫ አለመኖሩን በመገንዘብ የአዲስአበባ ሁሉንአቀፍ ንቅናቄ አ.ሁ.ን የተሰኘ የአዲስ አበባን እና የነዋሪዎቿን ሁሉን አቀፍ መብት፥ ፍላጎት፥ ጥቅምና ውክልና የሚያረጋግጥ፤ ኢትዮጵያውያንን የመዲናቸው ባለቤት ለማድረግ የሚሰራ አለም-አቀፍ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ንቅናቄ ተመስርቷል። ከእዚህም አላማው በመነሳት፣ አ.ሁ.ን አዲስአበባን የተመለከቱ ታሪካዊ ምርምሮችን ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ፥ በከተማዋ ጉዳዮች ዙርያ የተለያዩ ዕውቀት የማሰራጫና ግንዛቤ መፍጠርያ መድረኮችን የማዘጋጀት፣ የከተማዋንና የነዋሪዎቿን አንገብጋቢና ዘላቂ አጀንዳዎች በመለየት እነኝያን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ሰላማዊ ዘመቻዎችን አስተባብሮ የመምራት ስራ ያከናውናል። ሌሎች እዚህ ላይ ያልተመለከቱ አላማውን ለማሳካት የሚያግዙ በርካታ ተግባራትንም ለመፈጸም አቅዷል፡፡ አ.ሁ.ን ለአዲስአበባና አዲስአበቤ መብትና ጥቅም ለታመኑና ቁርጠኛ ለሆኑ ለማናቸውም አደረጃጀቶች ሁሉንአቀፍ ድጋፍ የሚያደርግ አለምአቀፍ ንቅናቄ ነው፡፡
አ.ሁ.ን በሁሉም የአለም ክፍሎች ወኪሎች የሚኖሩት ሲሆን በምስረታው ወቅት ወደ 2000 የተጠጉ አባላት አሉት። በቀጣይነትም ማንኛውም ያገባኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ዜጋ በአባልነት እንዲመዘገብ፥ በጊዜ፥ በክህሎትና በገንዘብ በመደገፍ ለአላማችን ከግብ መድረስ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ እናቀርባለን።
የአዲስአበባ ሁሉንአቀፍ ንቅናቄ አ.ሁ.ንን አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ ማግኘትና የንቅናቄው አባል መሆን የምትሹ በሚከተሉት አድራሻዎች ልትጽፉልን ትችላላችሁ፤
1. contactAhunUS@gmail.com
2. contactAhunEU@gmail.com
3. contactAhunETH@gmail.com
በአንድነት አዲስ አበባንና አዲስአበቤነትን እንታደግ!
አዲስአበቤነት ይለምልም !!
ኢትዮጵያ ምንጊዜም በክብር ትኑር !!
የአዲስአበባ ሁሉንአቀፍ ንቅናቄ (አሁን)

No comments:

Post a Comment

wanted officials