Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, December 18, 2018

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገደሉ


 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ብር ጭኖ በሚጓዙ  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ተሽከርካሪዎች  ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ጨምሮ ሶስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
ባልታወቁ ታጣቂዎች በተፈጸመውጥቃት አንደኛው ተሽከርካሪ ሙሉ በሙሉ መውደሙን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ተሽከርካሪዎቹ 6 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ይዘው ሻኪሶ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ለማድረስ እያመሩ እንደነበረ ታውቋል።
ሻኪሶ ከተማ ለመድረስ 20 ኪሎሜትር ሲቀራቸው ጥቃቱ መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን ብሩን የጫነው አንደኛው ተሽከርካሪ አምልጦ ሻኪሶ በመግባት ገንዘቡን ማስረከቡን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲላ ቅርንጫፍ የኦፕሬሽን ክፍል ሃላፊ አቶ አብዱልፈታህ አብራር ለኢሳት እንደገለጹት ጥቃቱ የተፈጸመው ትላንት ነው።
ከዲላ ቅርንጫፍ ብር ጭነው ወደ ጉጂ ዞን ሃያዲማ ቅርንጫፍ ያመሩት የባንኩ ሰራተኞች በማግስቱ ከሃያዲማ ወደ ሻኪሶ የሚያደርሱት ገንዘብ እንደነበር ነው ሃላፊው የሚገልጹት።
6 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ጭነው በ10 ወታደሮች ታጅበው ከሃያዲማ ወደ ሻኪሶ እያመሩ በነበሩት የባንኩ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ሻኪሶ ለመድረስ 20 ኪሎ ሜትር ሲቀራቸው እንደነበርም ሃላፊው ገልጸዋል።
ማንነታቸው ያልታወቁ ባሏቸው ታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት ከወታደሮቹ ሁለቱ ሲገደሉ የሁለተኛው ተሽከርካሪ ሹፌሩም ህይወቱ ማለፉ ታውቋል።
ታጣቂዎቹ ከሃያዲማ ቅርንጫፍ ወደሻኪሶ ገንዘብ ጭኖ የሚሄደውን ተሽከርካሪ በጥይት መትተው ጎማውን ቢያተነፍሱትም ሹፌሩ በወሰደው ቆራጥ ርምጃ ጎማ የሌለው መኪና እያሽከረከረ ሻኪሶ መግባቱንና ገንዘቡን ከዘረፋ ማስመለጡንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ይህን ተግባር የፈጸመው ሹፌር በተተኮሰበት ጥይት የተመታ ሲሆን ገንዘቡን ካስረከበ በኋላ ወደ ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ለህክምና መግባቱንም ለማወቅ ተችሏል።
የታጣቂዎቹን ማንነት በተመለከተ ኢሳት ባደረገው ማጣራት በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች የሚያሳዩ መረጃዎች ደረሰውታል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የሻኪሶ ንግድ ባንክ ሰራተኛ የኦነግ እንቅስቃሴ ጎልቶ የሚታይበት አካባቢ በመሆኑ በባንኩ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት የሰነዘሩትም የኦነግ ታጣቂች ናቸው ሲል ለኢሳት ገልጿል።
ጉዳዩን በተመለከተ የኦነግ አመራሮች ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ከሁለት ወራት በፊት በተመሳሳይ የኦነግ ታጣቂዎች ጉጂና አማሮ በሚዋሰኑበት አከባቢ ሶስት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የገደሉበትን ጥቃት መፈጸማቸው የሚታወስ ነው።

No comments:

Post a Comment

wanted officials