Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, December 29, 2018

የሻሸመኔ አሳዛኙ ክስተትና የደረሱኝ መረጃዎች | ከአህመዲን ጀበል



ዛሬ ጠዋት ላይ በፌስቡክ ወጣቶች አዛዉንቶችን ሲደበድቡ የሚያሳይ ቪዲዮ ተመለከትኩ፡፡ አንዳንዶች አዛዉንቶቹ የእገሌ ብሄር(ዘር) ስለሆኑ ነው የሚደበድቧቸው እያሉ ሲጽፉ ሌሎች ደግሞ የተደብዳቢዎችን ማንነት ትተው ሽማግሌዎች መሆናቸውን ብቻ እየጠቀሱ አዝነው የጻፉትን አነበብኩ፡፡ ልክ ነው ያሳዝናል፡፡ በሀገራችን ባህል ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በእድሜ ከፍ ያለን ሰው ያውንም ወጣቶች እንኳንስ እያሳደዱ መደብደብ አይደለም አጓጉል ቃላት እንኳ መሰንዘር ነውር ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሻሸመኔ በአንድ ኢትዮጵያዊ ወገናችን ላይ የተፈጸመውን አሳዛኝና አስደንጋጭ የደቦ ፍርድና እርምጃ አስታዉሶኝ ጉደዩ አስደነገጠኝ፡፡ ችግር ቢኖር እንኳ ለህግ ማቅረብ እየተቻለ ስለምን የደቦ ፍርድ እዚያም እዚህም ይሰፍናል? ብዩ አዘንኩ፡፡ ቪዲዮውን በጥሞና ሳየው ደብዳቢዎቹም ተደብዳቢዎቹም ኦሮምኛ ቋንቋ እየተናገሩ እንደሆነ አስተዋልኩ፡፡

ከዚም ጉዳዮን አጣርቼ ለማወቅ ጥረት ጀመርኩ፡፡ የተለያዩ ሰዎች ጋር ደዋወልኩ፡፡ እንደተባለው ግጭቱ በሻሸመኔ እንደሆነና ስፍራው በሻሸመኔ ከተማ ቀበሌ 10 አሌሉ የሚባል ሰፈር ባለው የምዕራብ አርሲ ዞን የእስልምና ጉዳይ ጽ/ቤት (መጅሊስ) ቅጥር ጊቢ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ የተደበደቡት ሰዎች ጀማል መሀመድ፣ሁሴን አብዱልቃድር፣ ዑስማን፣ሙሀመድ አየለ (አልይ) እና አንድ ስማቸውን ማወቅ ያልቻልኳቸው እንደሆኑ ተረዳሁኝ፡፡ ክስተቱም ከ41 ቀናት በፊት በ6/3/2011 እንደተፈጠረ ሰማሁ፡፡ ጉዳዩም ከመጅሊስ ጋር ተያይዞ እንደተፈጠረና ከአንድ ወር በፊት የተደበዱ ሰዎች ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች አቤቶታ እንዳቀረቡም ሰማሁ፡፡ በሀገሪቷ በአንንዳንድ አከባቢዎች እየታየ ስላለው ግጭት የመፍጠር አዝማሚያ ከአንድ ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለዉጥ የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የፌደራል መጅሊስ ፕሬዝዳንት ሀጅ ሙሐመድ አሚን ጀማል በሻሸመኔ መጅሊስ ግጭት ተከስቶ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንደቀረበ የጠቀሱት ኋላ ላይ ትዝ አለኝ፡፡ ወደ ፌደራል መጅሊስ ደዉዩ እንዳረጋገጥኩ የሻሸመኔው ችግር ከ41 ቀናት በፊት የተከሰተው ራሱ መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡ ወደ ሻሸመኔም ደውዩ ጠያየቅሁ ከመረጃ ምንጮቼ የተረዳሁትን ከጉዳዮ መነሻና የእለቱ ችግር እንዴት እንደተከሰተ ጭምር እንደሚከተለው በዝርዝር አብራራለሁ፡፡
የሻሸመኔ ከተማ ህዝብ በከተማዋ በስልጣን ላይ የነበሩት የመጅሊስ አመመራሮችን አትወክሉንም ብሎ ይቃወም ነበር፡፡ በኋላ ላይ የህዝቡ ጫና ሲበዛባቸው በመጅሊስ መሪነት የነበሩ ሰዎች ከሕዝቡ ከምንጣላ ብለው በ15/10/2011 ከሥልጣን ለቀው የቢሮውን ቁልፍ ለሀገር ሽማግሌዎች አስረከቡ፡፡ ሽማግሌዎችና ዓሊሞች በጉዳዩ ላይ እየመከሩ ሳለ በሰኔ 26 ቀን 2010 የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አሸማጋይነት ተቋቋመ፡፡ የመጅሊሱን ቢሮ ቁልፍ የተረከቡት ሽማግሌዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቋቋመው ኮሚቴ አማካኝነት ለዉጥ እስኪመጣ እንጠብቅ በሚል የሻሸመኔ ከተማና የምዕራብ አርሲ ዞን መጅሊስ ቢሮ ታሽጎ እንዲቆይ ይወስናሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ከአምስት ወራት በፊት የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ ደብዳቤ በመጻፍ እነእገሌን በመጅሊስ መሪነት ሾሜያለሁ ብሎ ደብዳቤ አስይዞ ይልካል፡፡ የተላኩት ሰዎችም በተይም በረብሻው ስፍራ ቆሞ ለህዝቡ የሚናገረው ጀማል መሀመድ የተሾሙበትን ፖስታ ይዞው ለዞኑና የከተማው አስተዳደሮች ፖሊስና የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊዎች ጋር ይሄዳል፡፡ ከአከባቢው ያገኘሁት መረጃ እንደሚለው ናደው የሚባለው የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ ጉዳዩ የህዝበ ሙስሊሙ እንጂ የኛ አይደለም፡፡ ሕዝቡን ጠይቅ እኛን አይመለከትም ይለዋል፡፡
ቀጥሎም በከተማዋ ታዋቂ የሆኑ ዓሊሞችን እነ ሼህ ሀጅ አደም፣ሼህ አሊ ቡታንና ሼህ መሀመድ በዳሶ ያናግራል፡፡ አግዙኝ ይላል፡፡ እነርሱም ‹‹ችግር ልትፈጥር ካለሆነ በቀር አርፈህ ተቀመጥ›› ይሉታል፡፡ የዚህ በዚህን ጊዜ የከተማው አስተዳደር ፖሊስና የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊዎች ችግር እንዳይፈጠር አርፈው እንዲቀመጡና ከህዝቡ ጋር እንዳትጋጩ ብለው ይመክሯቸዋል፡፡ የሻሸመኔ ከተማ የእስልምና ጉዳይ ጽ/ቤትን ከፍተው ለመግባት ስፍራው ከተማ መሃል ስለሆነና ቁልፉም በሀገር ሽማግሌዎች እጅ ስለሆነ ችግር ይፈጥርብናል ብለው ይሰጋሉ፡፡ ቀጥሎም የሻሸመኔ ከተማ መጅሊስ ቢሮ ተዘግቶ እያለ አዲሱን የሻሸመኔ መጅሊስን ቢሮ ወደ ምዕራብ አርሲ ዞን መጅሊስ ቢሮ ቅጥር ጊቢ አዙረናል፡፡ እኛም ተመርጠናል ብለው በከተማዋ መስጊዶች ማስታወቂያ ይለጥፋሉ፡፡
የተወሰኑ የሀገር ሽማግሌዎች ከዚህ በፊት በመጅሊስ ምርጫ ጊዜ በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ነበረ የተባለው ጀማል መሁመድን ከዚህ በፊት በማንኛውም መልኩ የመጅሊስ አባል ሳትሆን እንዴት በመጅሊስ መሪነት ተመረጥኩ ትላለህ ብለው ያናግሩታል፡፡ ይኸው የኦሮሚያ መጅሊስ መርጦ ላከኝ ያለበትን ደብዳቤ ብሎ ያሳያቸዋል፡፡ ሽማግሌዎቹ ‹‹እውነት የኦሮሚያ መጅሊስ መርጦህ ቢሆን እንኳ ከህዝቡ ሁሉ ጋር ተጋፍጠህ አትችልም፤ ደብዳቤን ደብቀህ ኑሮህ ኑር›› ይሉታል፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ እርሱም አሻፈረኝ ብሎ በመጅሊስ መሪነት ተሾመ የተባለው ጀማል መሀመድም በ02/3/2010 ደብዳቤ በመጻፍ (በኦሮምኛ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ በእጄ ገብቷል) የሻሸመኔ ከሕዝበ ሙስሊም ስብሰባ ይጠራል፡፡ በዚህን ጊዜ የከተማው ሽማግሌዎችና ዓሊሞች በስብሰባው ቢገኙ ላልመረጧቸው የመጅሊስ መሪዎች እርቅና መስጠት ይሆናል ብለው ቀሩ፡፡ ሰዉም እንዲቀር ሲሉ በየመስጊዱ ለሕዝቡ አስተላለፉ፡፡ በዚህ ጊዜ የተወሰኑ ወጣቶች በስፍራው ተገኝተው ‹‹ማንናችሁ? በምን ስልጣን ጠራችሁን?›› ብለው እየጠየቁ ግርግሩና ድብደባው ተከሰተ፡፡ ይህንኑ የሚያሳየዉን ቀጣዩን ቪዲዮ ይመልከቱ፡፡ ኦሮምኛ ለማትሰሙት ደግሞ በዚህ ቪዲዮ ላይ የሚተላለፈውን ንግግር እንደሚከተለው ተርጉሜ አቅርቤያለሁ፡፡
– ተናጋሪ (በበረንዳው መድረክ ላይ የቆመው)፡- …መምጣት ስላልቻሉ…(ብሎ ቪዲዮው ይጀምራል)
– ከሰዉ መካከል፡- ማነው የጠራን?
– ተናጋሪ፡- እኔ ነኝ፡፡
– ከሰዉ መካከል፡- ለምን ጠራኸን? አንተ ማንነተህ?
– ተናጋሪ፡- እኔ ጀማል መሀመድ ጃርሶ እባላለሁ፤
– ከሰዉ መካከል፡- የሥራህ ድርሻ ምንድነው? ሚናህ ምንድነው? ለምን ጠራኸን?
– ከከመድረክ ተናጋው ጎን የቆሙት ሽማግሌ(በመጅሊስ መሪነት ተሸሙ የተባሉትና ኃላ ላይ ከተደበደቡት መካከል አንዱ ናቸው) ፡- ችግር የለውም ተራ በተራ ተናገሩ፡፡
– ከዉ መካከል፡- አንተ አያገባህም እንደፈለግነው እንጠይቃለን፡፡ ንግግራችን ከርሱ ጋር ነው፤ካንተ ጋር አልተነጋገርንም፡፡
– እንደፈለግነው እንጠይቃለን አያገባህም፡፡
– ከሰዉ መካከል፡- አንተ ሽማግሌ እርሱ እኔ ነኝ የጠረኻችሁ ብሏል አንተ ምንም አያገባህም ዝም በል፡፡
– ከመድረክ፡- ጌታችሁን ፍሩ
– ከሰዉ መካከል፤-አንተ ራስህ ጌታህን ፍራና ዉረድልን፡፡
– ከሰዉ መካከል፡- አንድ ሰው ሲጠይቅ ሌሎቻችሁ ዝም በሉ፡፡
– ከሰዉ መካከል፡- ዝም በል አፍህን አትክፈት፡፡
– ከሰዉ መካል፡- ምን ልትሆን ፈለግክ?
– ከሰዉ መካከል፡- አንተ ሕዝቡን የጠራህበትን ተናገር፡፡ ማን እውቅና እንደሰጠህ ተናገር፤ በህገወጥ መንገድ እዚህ ጊቢ ማን እንድትገባ እንደፈቀደልህ ተናገር፡፡ ይህ ጊቢ የሙስሊሙ ሕዝብ ነው፡፡ ከሌቦች እጅ ወስደን ቆልፈናል፡፡ ማን እንድትከፍት እንዳደረገህ ተናገር-ንገረን፡፡
– በዚህ ጊዜ በበረንዳው መድረክ ከጀርባ የቆመው ወጣት በመድረክ ላይ የቆመውን ተናጋሪ ከጀርባ ገፍቶ አስወረደው
– ከሰዉ መካከል፡ ተዉ ተዉ
– ምን ልትሆን ነው?
– ግርግሩና ድብደባ ተጀመረ፡፡
በዚህ መለኩ ግጭቱ ተፈጠረ፡፡ የቆሰሉ ሰዎችም ነበሩ፡፡ ጉዳዩን የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ሼህ ተማም፣ሼህ አሊ ቡታ፣ ዉሽታና ዳንሱሬ በመያዝ በእርቅ እየፈቱት ነው፡፡ የተጎዱ ሰዎች ለመታከሚያ 200 ሺህ ብር ያስፈልገናል ሲሉ የሀገር ሽማግሌዎቹ 10ሺህ ብር እንዲሰጥ ወስነዋል፡፡ ለአሁን የደርስኩበት መረጃ ይህን ይመስላል፡፡ እዚህ ላይ በግልጽ መጥቀስ የምፈልገው በአሁኑ ሰዓት ልክ በብሄርና ጎሳ ግጭት እየተፈጠረ እንዳለው በሃይማኖትም ግጭት ለመፍጠር አንዳንድ ሙከራዎች እንዳሉ እንደኮሚቴ በግልጽ ከመንግስት ጋር ተወያይተናል፡፡ መልኩን እየቀያየረ ቢመጣም ግጭት በተለይ በዚህ የሽግግር ወቅት ለማን እንደሚጠቅም ግልጽ ነው፡፡ ይህንን በመረዳት ኮሚቴው ከእስካሁኑ በተለየ መልኩና በፍጥነት መጓዝ እንደሚገባ ከሚመለከተው አካል ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህም ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በተከታታይ ኮሚቴው ይፋ የሚያደርጋቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህን በመረዳት እያንዳንዱ ዜጋ ምንም ያክል ስሜት የሚነካ ነገር ቢከሰት የመፍትሄው እንጂ የችግሩ አካል እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባል፡፡
የሻሸመኔው ጉዳይ ላይም ምክንያት የሆኑ ሁሉ ከየትኛውም ወገን ይሁኑ ተለይተው ለህግ ማቅረብ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም እንደ ሙስሊምነታችን የሻሸመኔው ችግር በሙስሊሞች መካከል ያውንም አንድ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ ወጣቶች በአባቶች ላይ መከሰቱ አሳፋሪና ብዙ የሚያስተምረን ሊሆን ግድ ይላል፡፡ የቱንም ያክል ልዩነት ቢኖር የሰውነት ክብር፣ የኢትዮጵያዊነት ባህልና የጋራ ማንነት ሉጋም ሆኖ ካልያዘን ከባድ ጊዜ ከፊታችን እንዳለ ያሳየናል፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሰጋን በመሆኑ ስሜት ዉስጥ ገብተን ችግሩን ከማራገብ ቆም ብለን ዘላቂና ሀገር ዐቀፍ መፍትሄ እንድንሻ ሊገፋፋን ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials