Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, December 1, 2018

በመቱ ከተማ ሰልፍ ተካሄደ | በቤኒሻንጉል 66 ሰዎች በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ



በቤኒሻንጉል እና ኦሮሚያ ክልል ድንበር ከተሞች አካባቢ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች እና የክልሉ ፖሊሶች መገደላቸውን ተከትሎ በም ዕራብ ኦሮሚያ የሚደረገው ሰልፍ ቀጥሏል:: በዛሬው ዕለት በመቱ ከተማን ጨምሮ በሌሎችም የም ዕራብ ወለጋ ከተሞች መንግስት የዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ የሚጠይቁ ሰልፎች ሲካሄዱ ውለዋል::
ኦዴፓ በዜጎች ላይ ደም ማፍሰስ የፈጸሙትን እና ሌቦችን የገቡበት ገብቼ እይዛቸዋለሁ ሲል መግለጫ ማውጣቱን ዘ-ሐበሻ ዘግቦ ነበር::
በሌላ ዜና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት በማጥፋትና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ 66 ሰዎች በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው እንዳሰፈሩት፥ ፖሊስን ጨምሮ በአካባቢው የበርካታ ነዋሪዎችን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ በማጥፋትና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ 66 ሰዎች በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለዋል:: የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል::
ከቤኒሻንጉል ሳንወጣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካመሸ ዞን የቀጠለውን አለመረጋጋት የሸሹ ወገኖች ዛሬ ወደ አማራ ክልል ቻግኒ ከተማ መምጣታቸውን የአማራ ቲቪ ዘግቧል። ተፈናቃዮቹ በእግራቸው በመጓዝ የመጡ ሲሆን፣ የሞቱ ሰዎችን መንገድ ላይ ማየታቸውን ተናግረዋል።
የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ቢኖርም ካማሸ ዞንን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘው መንገድ አለመከፈቱም ተገልጿል። መንገዱ ከተዘጋ አራት ወር አልፎታል::
ከካማሺ ዞን ‹‹ያሶ ወረዳ›› አካባቢያቸውን ትተው ቻግኒ ከተማ የገቡት እነዚሁ 45 የሚሆኑ ወገኖች ችግሩ እየከፋ በመምጣቱ ስጋት ውስጥ መግባታቸውንና በዚህም አካባቢውን ለቀው መምጣታቸውን ; ሌሎችም እየተከተሉ መሆኑን ገልጸዋል::
ተፈናቃዮቹ በቻግኒየከተማ አሥተዳደሩ ቢሮ ውስጥ ተጠልለዋል፡፡ ከሁለት ቀናት በፊትም ከካማሺ ዞን ሸሽተው የመጡ 69 የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች በዚሁ ሥፍራ ተጠልለው እንደነበር የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አረጋየሁ ወረደ ተናግረዋል::
ቤኒሻንጉል ዜጎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ሆነዋል፤ የዕለት ምግብ ፍጆታቸውንም ለማግኘት ተቸግረዋል፡፡ የቤኔሻንጉል ክልል መንግሥትም ከአቅሜ በላይ ነው ብሏል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials