የኒዩክለር ጦር መሳሪያን ለማስወገድ አለም አቀፍ ዘመቻ የተባለ ድርጅት የዘንድሮውን የ2017 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸነፈ።
በምህጻረ ቃል ኢካን ተብሎ የሚታወቀው አለም አቀፍ ተቋም የዘንድሮው የሰላም ኖቤል አሸናፊ የሆነው የኒዩክለር አደጋ ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ለአለም አደጋ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ነው።
እናም ተቋሙ የጸረ ኒዩክለር ስምምነት እንዲኖር ላደረገው ጥረት ሽልማቱን ማግኘቱ ታውቋል።
የኖቤል ሽልማቱን ያገኘው ተቋም በአውስትራሊያ ተመስርቶ በአሁኑ ጊዜ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ጽህፈት ቤቱ የሚገኝ ነው።
የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ የዘንድሮውን የሰላም ሽልማት አሸናፊ ለምን በኒዩክለር ጉዳይ ላይ እንዳደረገ አምስት የትንታኔ ምክንያቶች ተቀምጠዋል።
አንደኛውና የመጀመሪያው በአለም ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኒዩክለር ስጋት እየጨመረ መሆኑ ነው።
ከዚሁም ጋር ተያይዞ 9 ሃያላን የሚባሉ ሀገራት ስምምነቱን እስካሁን አለመፈረማቸውና እነዚሁን ለማበረታታትና ጥሪ ለማድረግ መሆኑንም ነው የተገለጸው።
ከእነዚሁ ሀገራት መካከል አሜሪካ፣ሩሲያ፣ብሪታኒያና ቻይና መገኘታቸው ደግሞ ሸላሚውን ድርጅት አሳስቦታል።
እናም ሀገራቱ ጥልቅ ውይይት በማካሄድ በአሁኑ ጊዜ ጥንቃቄ የተመላበት ኒዩክለርን የማስወገድ ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል።
ለሽልማቱ ሁለተኛ ምክንያት ያደረገው ደግሞ አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ በአሁኑ ጊዜ በኒዩክለር ጉዳይ መፋጠጣቸው ነው ተብሏል።
በተለይም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኒዩክለር ታጥቃለች የምትባለውን ሰሜን ኮሪያ ከምድረ ገጽ አጠፋታለሁ ማለታቸው ብዙዎችን ማሳሰቡ ይታወሳል።
ሌላው ሶስተኛ ምክንያት ደግሞ የኢራን የኒዩክለር ስምምነት በ6 ሀገራት መካከል ቢፈረምም አሜሪካ ከዚሁ ሂደት እወጣለሁ ማለቷ የብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑ ትኩረት እንዲስብ አድርጓል።
የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ድርጅት ከዚህ ቀደም ለ4 ጊዜ ያህል በጸረ ኒዩክለር ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማትና ግለሰቦችን ሸልሟል።
አሁንም በዚሁ ላይ አለም አቀፍ ዘመቻ የሚያካሂደውን ተቋም የሰላም ኖቤል መሸለሙ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱን አሳይቷል ተብሏል።
የኒዩክለር ጦር መሳሪያን ለማስወገድ አለም አቀፍ ዘመቻ በምህጻረ ቃሉ ኢካን የተባለው ድርጅት የዘንድሮውን የሰላም ኖቤል ማሸነፍ ከተበሰረ በኋላ የድርጅቱ መስራች ቲልማን ሩፍ ደስታቸውን ገልጸዋል።
ድርጅቱ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የሚገኝና በአንድ መቶ ሀገራት ውስጥ የሚንቃሳቀስ መሆኑ ታውቋል።
No comments:
Post a Comment