በኢየሩሳሌም የሚገኘው ዴር ሱልጣን ገዳም አደጋ ላይ መሆኑ ተገለጸ።
ከላይ በግሪክ ቤተክርስቲያን የተጀመረው ግንባታ ገዳሙን እያፈረሰው በመሆኑ አንደኛው ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ መዘጋቱን በእስራኤል የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በተለይ ለኢሳት ገልጿል።
የሚካኤል ቤተክርስቲያን በጣሪያው ላይ በደረሰበት መደርመስ የተዘጋ ሲሆን የመድሃኒዓለም ቤተክርስቲያንም የመናድ አደጋ አንዣቦበታል ተብሏል።
ጉዳዩ ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን በእስራኤል ከሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር ትላንት ስብሰባ ማድረጋቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ኤምባሲም ሆነ የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እስከአሁን ያደረጉት ነገር ባለመኖሩ የዴር ሱልጣን ይዞታን ኢትዮጵያ ልታጣ ትችላለች የሚለው ስጋት በሰፊው እየተሰማ ነው።
በዴር ሱልጣን የሚካኤል ቤተክርስቲያን ባለፈው መስከረም 12 የሚካኤል ንግስ ይከበር ነበር። ምዕመናን የዕለቱን መርሃግብር ተከታትለው ጨርሰው ከወጡ በኋላ የቤተክርስቲያኒቱ ጣሪ መደርመሱ ተሰማ።
በአጋጣሚ መርሃግብሩ ተጠናቆ በመሆኑ እንጂ በሰው ህይወት ላይ አደጋ የሚፈጥር ክስተት እንደነበር በዕለቱ የታደሙ ሰዎች ይናገራሉ።
ከላይ የግሪክ ቤተክርስቲያን እያካሄደ ያለው ግንባታ ለመደርመሱ ምክንያት እንደሆነም ይነገራል። በእስራኤል የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን እሸቱ እንደሚሉት ሁለቱ ቤተክርስቲያናት አደጋ ውስጥ ወድቀዋል።
የሚካኤል ቤተክርስቲያን ጣራ በመደርመሱ ምክንያት ተዘግቷል። በፖሊስ እንዲታሸግም ተደርጓል። በዚህም የተነሳ ምንም አይነት መንፈሳዊ አገግልግሎት አይሰጥም።የመድሃኒያዓለም ቤተክርስቲያንም እየፈረሰ ነው።
በገዳሙ አናት ላይ በግሪክ ቤተክርስቲያን ላለፉት ስድስት ዓመታት እየተካሄደ ያለው ግንባታ በእርጅና ላይ ያለውን ዴር ሱልጣንን ጨርሶ እንዳያጠፋው የሚሰጉ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን ማሰማት ጀምረዋል።
ይህ ገዳም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ይዞታ፣ በኢትዮጵያ ስም የሚታወቅ ገዳም መሆኑን በመጥቀስ እየደረሰበት ያለው የመደርመስ አደጋ አፋጣን መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባ እየተነገረ ነው።
ቅርሶች እየተበላሹና እየተሰባበሩ መሆናቸው ደግሞ አደጋውን የከፋ አድርጎታል ይላሉ አቶ ተስፋሁን።
የገዳሙ ህልውና ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን ትላንት እስራዔል ከሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር ስብሰባ አድርገዋል።
በእስራኤል የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጉዳዩ ላይ እስከአሁን ዝምታ መምረጡ ይነገራል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ትኩረት ባለመስጠቷ ገዳሙ ባለቤት እንደሌለው ተቆርቋሪ በማጣቱ ወደፊት ዴር ሱልጣን ላይ ኢትዮጵያ ያላት መብት ሊነጠቅ ይችላል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ አድሯል።
የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን እሸቱ ይህ የኢትዮጵያ ቅርስ የገጠመው አደጋን ለመታደግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
No comments:
Post a Comment