በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በጸረ ሽብርተኝነት አጋርነት ከአሜሪካ ጋር መተባበሩን እንደመደበቂያነት ተጠቅሞ እየፈጸመ ካለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆጠብ በአሜሪካ በዲሞክራሲና ነጻነት ላይ የሚሰራ ድርጅት ባልደረባ አስታወቁ።
በአሜሪካ ኮንግረስ ተረቆ የሚገኘውን ኤች አር 128 በሚባል የሚታወቀውን ህገ ውሳኔ አሜሪካ በአስቸኳይ ማጽደቅ አለባት ሲሉም ተናግረዋል።
በአሜሪካ በዲሞክራሲና ነጻነት ላይ በሚሰራው ፍሪደም ሀውስ በተባለው ድርጅት ውስጥ የአፍሪካ ፕሮግራም ኦፊሰር የሆኑት ዮሴፍ ባድዋዛ በድርጅቱ የመረጃ መረብ በለቀቁት ጽሑፍ በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የጸረ ሽብር አጋር ስለሆነ ብቻ በተቃዋሚዎቹ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግድያና እስር አሜሪካ በዝምታ ማለፍ የለባትም።
ኤች አር 128 የተባለውን ሕገ ውሳኔ በአፋጠኝ በማሳለፍ አገዛዙ እየፈጸመ ላለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በገዛ ዜጎቹ ላይ ወንጀል የሚፈጽም እንዲሁም በአገዛዙና በሕዝቡ መካከል ጤናማ ግንኙነት በሌለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ የአሜሪካ የጸጥታ አጋር መሆን አትችልም ብለዋል።
ኤች አር 128 ሕግ የሚወጣ ከሆነ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የጸረ ሽብር ትብብር ታቋርጣለች በማለት በቅርቡ በአገዛዙ እየተሰጠ ያለውን የውሸት ማስፈራሪያ አሜሪካ ቸል በማለት ጠንካራና የማያወላውል አቋሟን ማሳየት አለባት።
ይህም በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለመጠበቅና እያንዣበበ ያለውን ቀውስ ለመከላከል ወሳኝ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉ ዮሴፍ ባድዋዛ ጽፈዋል።
ሕጉን በማጽደቅ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላለው አገዛዝ ጠንከር ያለ መልዕክት ልታስተላልፍ ትችላለች ሲሉም አስፍረዋል።
የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት የጸረ ሽብር ትብብር አቆማለሁ የሚለውን የኢትዮጵያ መንግስትን የውሸት ማስፈራሪያ ወደ ጎን በመተው ሕጉን በአስቸኳይ ማጽደቅ አለባቸው ብለዋል።
በአሜሪካ ኮንግረስ የኮሎራዶ ተወካይ ማይክ ኮፍማን በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያውን አምባሳደር ባናገሩበት ወቅት ሕጉ የሚጸድቅ ከሆነ ሀገሪቱ የጸረ ሽብር ትብብሯን ታቋርጣለች እንዳሏቸው በኮሎራዶ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት መናገራቸውን ጽሑፉ አስታውሷል።
ጸሐፊው ሲያጠቃልሉም በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ መቼም ቢሆን እንዲህ አይነቱን ማስፈራሪያ እስከመጨረሻው ገፍቶበት አያውቅም። በጸረ ሽብሩ ላይ ላለመተባበር ቢወስን ማን እንደሚጎዳ ጠንቅቆ ያውቃል ብለዋል።
No comments:
Post a Comment