የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ አመራር የነበረው አንዱአለም አራጌ በዘፈቀደ እርምጃ አለምአቀፍ ሕግን በመጣስ በአገዛዙ መታሰሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ።
ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመውና አግባብ ያልሆኑ እስሮችን የሚያጣራው የመንግስታቱ ድርጅት ቡድን አንዱአለም አራጌ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቅ ጥሪ አቅርቧል።
አንዱአለም አራጌ ከእስር እንዲለቀቅና የጉዳት ካሳ እንዲከፈለው የወሰነው የዘፈቀደና ሕገወጥ እስሮችን የሚያጣራው የተባበሩት መንግስታት ቡድን ነው።
አምስት ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎችን ያካተተው የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ቡድን አንዱአለም አራጌ በጸረ ሽብር ሕግ ስም የታሰረው በሕገወጥ መንገድ ነው ብሏል።
እንደ ቡድኑ ሪፖርት ገለጻ አንዱአለም አራጌ ሀሳቡን የመግለጽ መብቱን ተጠቅሞ አገዛዙን ከመተቸት ውጪ የሰራው ጥፋትም ሆነ ወንጀል የለም።
እናም የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ መሪው አንዱአለም አራጌ በአስቸኳይ እንዲለቀቅና የጉዳት ካሳም እንዲከፈለው የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ቡድን ጥሪ አቅርቧል።
የአንዷለም አራጌ ጉዳይ እንዲጣራ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥያቄ ያቀረበውና ከእስር እንዲፈታ ዘመቻ የሚያደርገው ፍሪደም ናው የተባለው ድርጅትም የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ቡድን ውሳኔን አወንታዊ ሲል አወድሶታል።
የፍሪደም ናው የሕግ ተጠሪ ኬት ባርዝ እንዳለችው አንዱአለም አራጌን ለእስር የዳረገው ለፍትህ በመጮሁና በሰላማዊ መንገድ የአገዛዙን ገመና በማጋለጡ ብቻ ነው።
እናም በተባበሩት መንግስታት አጣሪ ቡድን የውሳኔ ሀሳብ መሰረት በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ አንዱአለም አራጌን ያለምንም ቅድመ ሁኔታና በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀው ጥሪ አቅርባለች።
አንዱአለም አራጌ በጸረ ሽብር ሕጉ ሰበብ ተከሶ የእድሜ ልክ እስራት ከተፈረደበት በኋላ ካለፉት 7 አመታት ጀምሮ በወህኒ ቤት ይገኛል።
አንዱአለም አራጌ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን አሁንም በእስር ላይ ሆኖ ለፍትህና ለነጻነት በመጮህ ላይ ይገኛል።
አንዱአለም አራጌ ያልተሄደበት መንገድና የሀገር ፍቅር እዳ የተባሉ መጽሀፍቶችን በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ ለሕትመት አብቅቷል፡፡
No comments:
Post a Comment