(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 3/2010)
የአባይ ዋና ምንጭ በሆነው ጣና ሐይቅ ላይ እምቦጭ በተባለው አረም እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ከኦሮሚያ ክልል ወደ አማራ ክልል የተንቀሳቀሱት ወጣቶች አረሙን የመንቀል ዘመቻ መጀመራቸው ታወቀ።
ጣና ኬኛ ወይንም ጣና የኛ ነው በሚል መሪ ቃል ወደ ጎጃም የተንቀሳቀሱት ወጣቶች በየስፍራው በተለይም በደብረማርቆስ ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በበርካታ አውቶቡሶች ተሳፍረው ጣና ሃይቅን ከአረም ለመታደግ በሚደረገው ዘመቻ ተሳታፊ ለመሆን የተንቀሳቀሱት ወጣቶች ከሳምንቱ አጋማሽ ጀምሮ አረሙን በመንቀል ጣናን ለመታደግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን በምስል ተደግፈው ከተሰራጩት መረጃዎች መመልከት ተችሏል።
ይህን የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችን እንቅስቃሴ ብዙዎች በአድናቆት እየጠቀሱ በማህበራዊ መድረኮች አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።
በ2008 ሐምሌና ነሐሴ መንግስት በኦሮሚያና በአማራ ክልል ተወላጆች ላይ ያካሄደውን ግድያ ተከትሎ በጎንደርና በአዳማ የሁለቱ ክልል ወጣቶች አንዱ ለሌላው የሰጠውን አጋርነትም በማስታወስ ላይ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ ትልቁ ሃይቅ የሆነውና የአባይ ወንዝ አብይ ምንጭ እንደሆነ የሚታወቀው ጣና እምቦጭ በተባለው አረም በከፍተኛ ደረጃ መወረሩ ይታወሳል።
ይህም በመንግስት በኩል በቂ ትኩረት አላገኘም በሚል ተቃውሞዎች እየቀረቡ ሲሆን በአደጋው መጠን ችግሩን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችም አልታዩም።
84 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዲሁም 66 ኪሎ ሜትር ያህል የጎን ስፋት ባለው የኢትዮጵያ ትልቁ ሃይቅ ጣና ላይ በእምቦጭ አረም እየደረሰ ያለው ጉዳት ከሀይቁ ባሻገር በአባይ ውሃ ፍሰት ላይም ተጽእኖው የጎላ እንደሚሆን ባለሙያዎች ያሳስባሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የጣና ሃይቅን የወረረውን እምቦጭ አረምን ለመከላከል ወደ አማራ ክልል የተንቀሳቀሱት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች በደብረማርቆስ ከተማ የጠበቃቸው ደማቅ አቀባበል ወጣቶቹ በባህር ዳር እንዳያልፉ ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል።
የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎችም የድምጽ መሳሪያዎችን ጭምር ይዘው ወደ አደባባይ በመውጣት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችን ለመቀበል ከተዘጋጁ በኋላ በባህርዳር እንዳያልፉ የተከለከሉበት ምክንያት ግልጽ አልሆነም።
ተልኳቸውን ጨርሰው ሲመለሱም ባህርዳር በምሽት እንዲገቡና በማለዳ እንዲወጡ ፕሮግራም መደረጉም እያነጋገረ ይገኛል።
No comments:
Post a Comment