(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 7/2010)
የኢሳትን 7ኛ አመት ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የአለም አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን የገቢ ማሰባሰብ ስራዎችን በማከናወን በሀገራቸው የሚካሄደውን የለውጥ ትግል እያገዙ ነው።
በሰሞኑ ብቻ በዳላስ ቴክሳስና በላስቬጋስ እንዲሁም በአውስትራሊያ አድላይድና ፐርዝ በመቀጠልም በአውሮፓ ኖርዌይ የኢሳት ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ተካሂደዋል።
በዝግጅቱ በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮችና ኢሳት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ ውይይትና ምክክር ተደርጓል።
በዳላስ ቴክሳስ በየአመቱ የሚካሄደው የኢሳት ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት እጅግ ደማቅና በርካታ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት ነው።
በኢትዮጵያዊነት የማይደራደሩት የዳላስ ነዋሪዎች ዘንድሮም የኢሳትን 7ኛ አመት የምስረታ በአል በደማቅ ሁኔታ አክብረዋል።
በዝግጅቱ ኮመዲያን ክበበው ገዳና በመሰንቆ ጨዋታ የሚታወቀው አርቲስት አበበ ፈቃዱ ዝግጅቱን አድምቀውታል።
በስነስርአቱ በክብር እንግድነት የተገኘው ጋዜጠኛ ምናላቸው ስማቸው አገዛዙ ስልጣኑን ለማቆየት ሚዲያን እንደምርኩዝ እንደሚጠቀምና በፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት ሕዝብን ለማደንዛዝ እንደሚሞክር ገልጿል።
እናም ኢሳት ሕዝብ ለመብቱ እንዲታገል የአገዛዙን ድብቅ ሴራዎች በማጋለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ለታዳሚዎቹ አብራርቷል።
በዝግጅቱ ጨረታ ተካሂዶ ከፍተኛ ገቢ መሰብሱም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በኔቫዳ ላስቬጋስ አቶ ኤርሚያስ ለገሰና ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ በተገኙበት የኢሳት 7ኛ አመት የምስረታ በአል ተካሂዷል።
በዚህም የኢሳት ፋይዳዎችና ፈተናዎች በሚል ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ማብራሪያ ስትሰጥ አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ደግሞ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርጓል።
በዚሁ ገለጻውም ለአንድ ስርአት መውደቅ ምልክት ከሆነው አንዱ የቁልፍ ባለስልጣናት ስራ መልቀቅ ዋነኛው መሆኑን ተናግሯል።
በኢትዮጵያ አገዛዙ ባመጣው ጣጣ የብሔር ግጭት ቢነሳ ደግሞ ድሬደዋ፣ አዲስአበባና ሀረር ዋነኛ ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያለውን ስጋት ገልጿል።
በተያያዘ የኢሳትን 7ኛ አመት ምክንያት በማድረግ የኢሳት ማኔጂንግ ዳይሬክተር በተገኙበት በአውስትራሊያ አድላይድና ፐርዝ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተካሂደዋል።
በአውሮፓ ኖርዌይም ተመሳሳይ ዝግጅት መካሄዱን ያገኘንው መረጃ ያመለክታል።
No comments:
Post a Comment