Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, October 16, 2017

የኬንያ ፖሊስ ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞችን በጥይትና በአስለቃሽ ጋዝ እየበተነ ነው


የኬንያ የፖሊስ ሃይል በሀገሪቱ በድጋሚ ከሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞችን በጥይትና በአስለቃሽ ጋዝ እየበተነ መሆኑ ታወቀ።
የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሕዝቡ ለተቃውሞ እንዳይወጣ ጥሎት የነበረውን እገዳ ውድቅ ቢያደርግም የሀገሪቱ ፖሊስ ግን ሰልፈኞቹን ከመበተን ወደ ኋላ እንዳላለ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን በድጋሚ የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፍትሃዊ ሆኖ ስለመካሄዱ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም ሲሉ ተደምጠዋል።
የኬንያ ፍርድ ቤት ሕዝቡ ለተቃውሞ እንዳይወጣ መንግስት የጣለውን እገዳ ውድቅ ቢያደርግም የሀገሪቱ የፖሊስ ሃይል ግን የተቃውሞ ሰልፈኞቹን በጥይትና በአስለቃሽ ጭስ መበተን አለማቆሙን መረጃዎች አመልክተዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጅ ቦኒፋስ ሟንጊ ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገረው ፖሊስ በአስለቃሽ ጋዝ ካኒስተር ተኩሶ ስለመታው ደረቱ ላይ የመቁሰል አደጋ አጋጥሞታል።
ኬንያ ቀስ በቀስ ወደ ፈላጭ ቆራጭነት እየሄደች ነው።መቃወም መሰረታዊ የሆነ የማይደፈር መብት ነው።ፖሊስ ለሕዝቡ ሳይሆን በስልጣን ላይ ላለው ፕሬዝዳንት የቆመ መሆኑን አሳይቷል ሲል አሶሼትድ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የኬንያው ፕሬዝዳንት የፖሊስ ሃይልን በመጠቀም ተቃውሞውን ለመጨፍለቅ እየሰሩ ነው ሲሉ ይከሳሉ።
ባለፈው ነሐሴ ከተደረገውና የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ከሻረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወዲህ ፖሊስ 67 የሚሆኑ የተቃውሞ ሰልፈኞችን ተኩሶ መግደሉ ተዘግቧል።
በኬንያ በድጋሚ የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሚቀጥለው ሐሙስ እንደሚደረግ ቢታወቅም የተቃዋሚ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ግን በምርጫው እንደማይሳተፉ ባለፈው ሳምንት መግለጻቸው ይታወቃል።
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ግን ራይላ ኦዲንጋ ምርጫውን እንደማይሳተፉ በሕጋዊ ፎርም ላይ አልሞሉም በሚል በምርጫ ወረቀት ላይ ስማቸውን እንደሚያሰፍር ገልጿል።
ኦዲንጋ የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ስር ነቀል ለውጥ አልተደረገበትም በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ ምርጫም ተአማኒነት የለውም በሚል ከምርጫው ራሳቸውን አግልለው ደጋፊዎቻቸው በየቀኑ ተቃውሞ እንዲያደርጉ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ባለፈው ነሐሴ በተደረገው ምርጫ 54 በመቶ ድምጽ በማግኘት ያሸነፉትና ነገር ግን በሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማጭበርበር ተፈጽሟል በሚል ውድቅ የተደረገባቸው ተቀማጩ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ድጋሚ ምርጫው በታቀደለት መሰረት እንዲካሄድ በመወትወት ላይ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የምርጫ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ሮዝሊን አኮምቤ በደረሳቸው የግድያ ዛቻ ምክንያት ወደ አሜሪካ መሸሻቸው ታውቋል።
ከቢቢሲ ጋር ትላንት ከኒዮርክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ የምርጫ ኮሚሽኑ አሁን ባለበት ሁኔታ የሚካሄድ ከሆነ ምርጫው ተአማኒነት አይኖረውም ሲሉ ተናግረዋል።
የምርጫ ኮሚሽኑ ሃላፊም ዋፋላ ቸቡካቲ አሁን ሀገሪቱ ባለችበት ሁኔታ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ለማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

Bildergebnis für የኬንያ የፖሊስ ሃይል

No comments:

Post a Comment

wanted officials