Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, October 29, 2017

አፈወርቅ ተክሌ እና “ቪላ አልፋ”


አፈወርቅ ተክሌ እና “ቪላ አልፋ”



የ“ቪላ አልፋ” አዲሱ መልክ

ከበዓሉ ግርማ

(1961 ዓ.ም)

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

አዲስ አበባ ውስጥ የተደረገውን፣ በመደረግ ላይ ያለውንና ወደፊት የሚደረገውን ሁሉ እንደመጠጥ ብርጭቆ አንስተው የማስቀመጥ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ከተሜዎች አሉ። ሰሞኑንም ከሰላምታ በኋላ አርዕስተ ነገር አድርገው የያዙት ትችት ቢኖር ስለ አፈወርቅ ተክሌ (ወልደ ነጐድጓድ) አዲሱ የቪላ አልፋ መልክ ነው።

ትችቱ እንደተቺዎቹ የበዛ ቢሆንም አንዳንዶቹ፣

“ተርፎት፣ የሚሠራውን ቢያጣ ለመመጻደቅ ያደረገው ነገር ነው” ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ (በተለይ የፍሮይድን ሳይኮሎጂ ከእጅ ጣታቸው እንደዋዛ የሚያንቆረቁሩት ተቺዎች) የዚህን ዓለም ጉዳይ ወደጎን ብለው፣

“አፈወርቅ ከአካባቢው ውጭ ወይም በላይ ሆኖ በራሱ የፈጠራ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚጥር ሰው በመሆኑ ነው እንዲህ ያለውን ቪላ የሠራው” በማለት ይናገራሉ።

“ግላዊ ልዩነቱን ለመግለጽ ያደረገው ነገር ነው” የሚሉም አሉ።

ያም ሆነ ይህ የነቀፌታዎቹ መነሾ ሠዓሊው አፈወርቅ ቪላ በመሥራቱ አይደለም። ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችን የገነቡት በሰው አፍ አልገቡም። በግል መኖሪያቸው የሰማኒያና የመቶ ሺህ ብር ዘመናይ ቪላዎችን የሠሩት ዓይን አልበላቸውም።

“ታዲያ የአፈወርቅ ስም እንደ ትኩስ ድንች እያንዳንዱ አፍ ውስጥ የሚገላበጥበት ምክንያት ምን ይሆን?” ብለን ብንጠይቅ መልሱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን።

ጐንደር የሚገኘውን የአፄ ፋሲልን ግንብ የሚመስል ባለአንድ ፎቅ መኖሪያ ቤት ባለንበት ክፍለ ዘመን በመሥራቱ ነው ልዩው ነገር። ሌላ ሰው ቢያስብም ሥራ ላይ የማያውለውን ነገር አፈወርቅ ግን በመሥራቱ ነው።

የዚህ አይነት ቤት (ወይም ካስል) በመሥራት አፈወርቅ በዘመናችን የመጀመሪያውና የመጨረሻው ሰው ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም ቤቱን የቀየሰው መሐንዲስ G. Boscarino እንዳለው፤

“እንዲህ ያለው ቤት ውስጥ ከአፈወርቅ በስተቀር ሌላ ሰው ቢኖርበት፣ ቤቱ አሁን ያለውን ዋጋና ጥቅም ሊሰጥ አይችልም”።

አዎን፣ ከአፈወርቅ በስተቀር እንዲህ የመሰለውን ቤት አልሞ የሚሰራ የለም። የሚሰጠውን ጥቅምም በይበልጥ የሚያውቀው እሱው ብቻ ነው።

እንዲህ የመሰለውን መኖሪያ ቤት ለመሥራት ምን እንዳሳሰበው፣ ከተሰራ በኋላ የሚሰጠውንም ጥቅም እንዲነግረኝ ጠይቄው ነበር። ለማናገር ፈቃደኛ ቢሆንም ጊዜ አልነበረውም።



አናጢዎቹ በየደቂቃው ይጠሩታል።

በተመለሰ ቁጥር “የአገራችን አናጢዎች ለምን አንድ መስመር በትክክል ለመሥራት አይችሉም?” በማለት ይገረም ነበር።

እነሱም በበኩላቸው እሱ አሁን በቅርብ ጊዜ የሠራውን የእንሥራ ተሸካሚ ሥዕል፤ በተለይ ወተት መስሎ በጃኖ ጥለት የታጠረውን ቀሚሷን፣ አለንጋ የመሳሰሉትን ጣቶቿንና ሕልም መሳይ ውበቷን አይተው መገረማቸው አልቀረም።

ገና ተመልሶ ቁጭ ከማለቱም ቀለም ቀቢዎች ይጠሩታል።

አዎን፣ “የሰሜን ተራራ” የተባለውን ሥዕል (ኅብረ ቀለሙ ልብ መስጦ፣ ዓይን ማርኮ፣ የአእምሮ ሰላም የሚፈጥረውን) የሠራ ሰው ለተራ ቀለም ቀቢዎች ችሎታ ልዩ አድናቆት ሊኖረው አይችልም።

አሁንስ አፈወርቅን የሚጠራው ሰው የለም ብዬ በመተማመን ጥያቄዬን ወርውሬ፣ ብዕሬን ከወረቀት ለማገናኘት ስቃጣ፣ አንድ ጽጌረዳ አበባ የት እንደሚተክሉ የቸገራቸው፣ ወይም አበባ የያዘውን ሳጥን የት እንደሚያስቀምጡ ግራ የገባቸው ለምክር ይጠሩታል። ሳያማክሩት ያስቀመጡት፣ ወይም የተከሉት እንደሆነ ኋላ ማንሳታቸው አይቀርም።

አፈወርቅ ደጋግሞ እንደሚለው፣

“ማንኛውም ነገር ከተፈጥሮ ጋር በመዋሀድ በኅብረ ቀለሙና በአቀማመጥ አቅዱ ለአእምሮ ዕረፍትና ሰላምን ካልሰጠ አእምሯችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚመራ ነገር የመፍጠር ችሎታ ሊኖረው አይችልም። ከተፈጥሮ ኅብረት ጋር ሥራችንንና ኑሯችንን ለማስተባበር ካልሞከርን ውበትን ለመፍጠር አንችልም። ለኔ ከፍተኛው ምኞቴ ይህ ነው – ኅብረት ከተፈጥሮ ጋር። ይህንን ከፍተኛ ምኞት ለመግለፅ የምፈልገው በምሠራቸው ሥዕሎች ብቻ ሳይሆን በአኗኗሬም ጭምር ነው”።

ሠራተኞቹም ደከሙ። ከአንድ ሰዓት ጀምሮ ያራውጣቸው ነበር።

ጥሪው እያነሰ ሄደ። ቁጭ ለማለት ቻልን።

“ይህን ቤት መሥራት ከጀመርኩ ወዲህ የተማርኩት ነገር ቢኖር የቤት ሥራ ምን ያህል ብስጭትና ድካም እንደሚያስከትል ለማወቅ መቻሌን ነው። ወደ ሰላማዊው የሥዕል ሥራዬ የምመለስበት ጊዜ በመቃረቡ ደስ ይለኛል” አለና እግሩን ዘርግቶ ወለሉ ላይ ዘፍ አለ።

በሁለት ወር ያልቃል ተብሎ የታሰበው ቤት አሁን አራተኛ ወሩን ሊጨርስ ነው። በአራት ወር ውስጥ አፈወርቅ ሦስት ሥዕሎች ብቻ ነበር ለመሥራት የቻለው። የቀረውን ጊዜ ያዋለው በቤቱ ሥራ ላይ ነበር።

“ቪላ አልፋ” የተሠራው በአሥር ዓመት ፕላን መሠረት ሲሆን ቤቱን ለመሥራት አፈወርቅ ከሚሸጣቸው ሥዕሎች ዋጋ አንድ ሦስተኛውን ለዚህ ፕላን ቆጥቦ ነበር። ሆኖም የቆጠበው ገንዘብ ስላልበቃው የአዲስ አበባ ባንክ ብድር ሰጥቶታል።

ይሁንና በኔ በጠያቂው በኩል ሃያ ስድስት በሃያ ስድስት ሜትር ካሬ መሬት ላይ የተሠራው አዲሱ ቤት ይህን ያህል የሚያስደንቅ ወጭ የሚጠይቅ መስሎ አልታየኝም። አፈወርቅም ስንት ገንዘብ እንደጨረሰ ትክክለኛ ዋጋውን ሊገልጽልኝ አልፈቀደም።

ቤቱን የአፄ ፋሲልን ግንብ አስመስሎ ለመስራት ያነሳሳውን ነገር ሲገልጽልኝ እንዲህ አለ፣

“ስለ አፄ ፋሲል ግንብ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽና ይህ የጥንት ቅርሳችን ተሻሽሎ ለዘመናይ ኑሮ ለመዋል መቻሉን ለማሳወቅ ነው። አዎን የኮራና የከበረ ቅርስ እያለን የቤት ፕላን ከውጭ የምንቀዳበት ምክንያት አይታየኝም።”

አፈወርቅ ለሚሠራው ነገር ሁሉ ምክንያት አለው።

በቤቱ ውስጥ ያለ ምክንያት የሚደረግ ነገር የለም። የአበባ ማስቀመጫው እሱ በፈለገበት ቦታ እንዲኖር የተደረገው ያለ ምክንያት አይደለም። የቤቱ ቆርቆሮ ቀይ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው። ቤቱ ነጭ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው።

አንድ ሥዕል አንድ ግድግዳ ላይ በአንድ በኩል እንዲሰቀል የተደረገበት ያለ ምክንያት አይደለም። ቤቱ የተሠራው ለመኖሪያ ብቻ ሳይሆን ሌላ ምክንያት አለው። ቤቱም ቀለሙም አቀማመጡም – ሁሉም ባንድነት ተዋህደው ኅብረት መፍጠር አለባቸው።

“ይህን የመሰለ ቤት የሠራሁበት ምክንያት አለኝ። የሠራኋቸው ሥዕሎች በተሠሩበት አካባቢ እንዲታዩ ለማድረግ ሲሆን፣ እንዲሁም እንግሊዝ ሀገር ተማሪ ሳለሁና በታላላቅ አውሮፓ ከተማዎች እየተዘዋወርኩ ሥዕል በምሠራበት ወቅት፣ ብዙ ሠዓሊዎች ቤታቸው ይጋብዙኝ ነበር።”

“አሁንም በተራዬ እዚህ በመጋበዝ አንድ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊ እንዴት እንደሚኖር ለማሳየትና ከዚህም አልፎ ከሀገራችን የታሪክ ቅርስ ጋር ለማስተዋወቅ ነው። እንግዶቼ በውብ ነገር ተከበው ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ከማድረግ ሌላ የዕለት ኑሮዬን እንዴት እንደማሳልፍ እንዲያውቁም ጭምር ነው።”

“ከዚህ ቀደም ቤቴ በግንብ አጥር ተከቦ ታፍኜ ስኖር ነበር። አሁን ግን የቤቱ ሰገነት ወደ ውጭና ወደ እሩቅ ለመመልከት ያስችለኛል። ሰገነቱ ላይ ወጥቼ የአዲስ አበባ ተራራዎችን ለማየት እችላለሁ። ላንድ ሠዓሊ እንዲህ ያለው የመዝናናት ትዕይንት ጠቃሚው ነው።”

አዎን፣ ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም።

ቤቱ አንድ ሺህ ሜትር ካሬ ላይ መሠራቱ ምክንያት አለው። የመሬት ቁጠባን ለማስተማር ነው።

ሦስቱ መስኮቶች ሦስት አይነት ቀለማት የተቀቡበት ምክንያት አለው። የፀሐይዋን ዕለታዊ ጉዞ ተከትለው እንዲያንጸባርቁ ለማድረግ ነው።

የቤቱ ክፍሎች አቀያየስ ምክንያት አላቸው። ሃምሳ አራት ሥዕሎች ባንድ ጊዜ ለማሳየት እንዲቻል ታስቦ የተደረገ ነገር ነው። እንዲሁም እያንዳንዱ ክፍል ከየጠቅላይ ግዛቶች የሚገኙትን ጌጣጌጦች ማሳያ ሊሆን ይችላል።

የጸሎት ወይም የሀሳብ ማጠንጠኛ ክፍሉ የአክሱም ጽዮንን መልክ የያዘ ነው።

የምሥጢር በሩ ያለ ምክንያት አልተሠራም። አፈወርቅ ካንዱ ክፍል ወደ ሌላ ሳይታይ ለመዘዋወር እንዲችል ነው።

የጋራጁም ስፋትና ቀለም ያለ ምክንያት አልተደረገም። ሁለት መኪናዎች እንዲይዝ ከመሆኑም በላይ የጋራጁ ቀለም ከመኪናዎቹ ቀለም ጋር ተዋህዶ ኅብረትን ለመፍጠር እንዲችል ታስቦ ነው።

አዎን፣ በአፈወርቅ ቤት ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም።

በዓሉ ግርማ

በዓሉ ግርማ ፋውንዴሽን መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ

.

[ምንጭ] – መነን (ሚያዝያ ፳፱፣ ፲፱፻፷፩)፤ ገጽ ፲፮-፲፯።

No comments:

Post a Comment

wanted officials