(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 7/2010) አቶ በረከት ስምኦን ከስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን መንግስት ማረጋገጫ ሰጠ።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ስለ አቶ በረከት ከስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ የምናውቀው ነገር የለም ብለው ነበር።
ነገር ግን ከአንድ ቀን በኋላ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ አቶ በረከት የመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ለመንግስትና ለፓርቲ መገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል።
ከሳምንት በፊት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ከያዙት መንግስታዊ ስልጣናቸው ሃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት አቶ በረከት ስምኦን የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በተባለው ተቋም በአቶ አባይ ጸሐዬ ስር በምክትል ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ እንደነበርም ታውቋል።
መልቀቂያም ያቀረቡት ከዚህ ሃላፊነታቸው ለመነሳት እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 7/2010 ለፓርቲና ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንዳረጋገጡት አቶ በረከት ስምኦን የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አስገብተዋል።
ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ከአንድ ቀን በፊት ግን ስለ አቶ በረከት ከስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ የምናውቀው ነገር የለም ብለው ነበር።
መንግስት የቀረበውን የስራ መልቀቂያ እየተመለከተው መሆኑን የገለጹት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊው ዶክተር ነገሬ ሌንጮ አቶ በረከት ስራ ለመልቀቅ ስለፈለጉበት ምክንያት የታወቀ ነገር አለመኖሩንም ጠቁመዋል።
አቶ በረከት ስምኦን በአቶ አባይ ወልዱ ከሚመራውና በጄኔራል ሳሞራ ድጋፍ ከሚደረግለት የሕወሃት አንጃ ጋር ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ምንጮች ይገልጻሉ።
የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የመቀሌ ስብሰባ ላይ በአቶ ስብሐት የሚመራው አንጃ አባላት በአንጋፋ አመራርነት ስም መጋበዛቸውን ተከትሎ በፓርቲው ውስጥ ያለው የሃይል አሰላለፍ ለአቶ በረከት ከንግድ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢነት መባረር ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል።
እሳቸውም ቀሪ ቦታዎቻቸውን በፈቃዳቸው መልቀቅ እንደመረጡም ተመልክቷል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አቶ በረከት ስምኦን ስልጣን ለመልቀቅ ስላቀረቡት ጥያቄ ለየትኛውም መገናኛ ብዙሃን መግለጫ አልሰጡም።
እሳቸውም ህዝቤንና ድርጅቴን ብአዴንን ከውርደት ለመጠበቅ ስል ስልጣን ለቀኩ የሚል መግለጫ እንደአባዱላ ይሰጣሉ ተብሎም በመጠበቅ ላይ ነው።
No comments:
Post a Comment