Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, October 11, 2017

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 2/2010) በወሊሶ ከተማ ዛሬ ህዝባዊ ተቃውሞ ተካሄደ።



በወሊሶ ከተማ ዛሬ ህዝባዊ ተቃውሞ ተካሄደ




ትላንት በሻሸመኔ ስምንት ሰዎች መገደላቸው ያስቆጣቸው የወሊሶ ከተማ ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት የህወሀት መንግስት በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርድ ጠይቀዋል።

ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስ ተጠቅሞ ሊበትን መሞከሩ ተገልጿል።

በሌላ በኩል በቱሉቦሎና በሱሉልታም ተመሳሳይ ህዝባዊ ተቃውሞ መካሄዱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉት ዜጎች በችግር ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው።

ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ዛሬም በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።

ትላንት አምቦ፣ ሻሸመኔን፣ አዳባንና ኮፈሌን ጨምሮ በሀረርጌ የተለያዩ ከተሞችን ያዳረሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ዛሬም በሌሎች ከተሞች በመካሄድ ቀጥሏል። ወሊሶ፣ ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ፣ ቄሌም ወለጋ፣ አጋርፋ ፣ቱሉ ቦሎ፣ ሱሉልታ ዛሬ ህዝባዊ ተቃውሞ ተደርጎባቸው ውለዋል።

ትላንት ስምንት ሰዎች የተገደለባት ሻሸመኔ ዛሬም መረጋጋት እንደሌለ የተነገረ ሲሆን ተቃውሞ ቀጥሎ መዋሉን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመንግስት ሃይል ወደሻሸመኔ መግባቱንም ለማወቅ ተችሏል።

ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው አምቦ ለሁለተኛ ቀን ተቃውሞ ተካሂዶባታል። በተለይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የመንግስት ለውጥ የሚጠይቅ የተቃውሞ ድምጽ ሲሰማ እንደነበረ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ዛሬ በወሊሶ ከንጋት ጀምሮ ህዝቡ በዋና ዋና መንገዶች ላይ በመውጣት ተቃውሞውን ማሰማቱን ከስፍራው ያነጋገርነው ነዋሪ ገልጾልናል።

ትላንት በሻሸመኔ የተፈጸመው ግድያ የወሊሶን ነዋሪ ማስቆጣቱን የተገለጸ ሲሆን የህወሀት መንግስት በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲለቅም ጠይቋል።

የወሊሶውን ተቃውሞ የመንግስት ታጣቂዎች በአስለቃሽ ጭስ ለመበተን እንደሞከሩ ታውቋል።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ተቃውሞውን በመቀላቀላቸው ሁኔታው ከፖሊስ አቅም በላይ ሊሆን እንደቻለም ያነጋገርነው ነዋሪ ገልጿል።

በወሊሶው ተቃውሞ አቶ አባይ ጸሀዬ ተለይተው ስማቸው ተጠርቶ ተወግዘዋል።

የህወሀት መንግስት ከእንግዲህ አይገዛንም የሚለው መልዕክት ከፍ ብሎ ተሰምቷል። ከተማሪ እስከ አርሶ አደር የተሳተፉበት ይህው ተቃውሞ በሰላም መጠናቀቁን ነው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።

በሌሎች የኦሮሚያ ክልል ከተሞችና አነስተኛ መንደሮች የተካሄዱት የተቃውሞ ትዕይንቶች ተመሳሳይ መልዕክቶች የተላለፉ ሲሆን የኦፌኮ መሪዎች ይፈቱ፣በሶማሌ ልዩ ሃይል የሚካሄደው ማፈናቀልና ግድያ ይቁም፣ የሚሉት ዋናዎቹ መፈክሮች ነበሩ።

በተለይ በምዕራብ ወለጋ ጊምቢና ቄሌም ወለጋ መንገዶች ተዘግተው ተቃውሞ እንደተደረገባቸው ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ችግር ውስጥ መሆናቸውን ኢሳት ያነጋገራቸው የወሊሶ ነዋሪ ገልጸዋል።

በወሊሶ በየቀበሌው ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ምግብ የሚያቀርብላቸው እንደሌለ የተገልጸ ሲሆን በመንግስት በኩል እስከአሁን ምንም ድጋፍ አልተደረገላቸውም ተብሏል።








No comments:

Post a Comment

wanted officials