- “ተስማምታችሁ ብትችሉ ይዛችሁ ኑ! ቤታችሁ ነው፤ አገራችሁ ነው፤ ኑ በሏቸው፤”
- “በሥነ ሥርዐት ጨርሳችሁ ከተመለሳችሁ፣ በሚሌኒየም አዳራሽ ዕውቅና እንሰጣለን፤”
/ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ/
†††
- “ተልእኳችሁ፣ የአገርም ጉዳይ ነው፤ መልካም ነገር ሠርታችሁ በውጤት እንደምትመለሱ ተስፋ እናደርጋለን፤” /የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ዴኤታዋ/
- “ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የዕርቅ ቤት ናት፤ መከፋፈል የቤተ ክርስቲያን መገለጫ አይደለም፤ እግዚአብሔር ያሳካላችሁ፤”/ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ/
- “ዘመኑ፥ የሰላም፣ የፍቅርና የዕርቅ ነው፤ ቤተ ክርስቲያንም አርኣያ ኾና የበለጠ መሥራት አለባት፤”/የቋሚ ሲኖዶስ አባላት/
†††
የቤተ ክርስቲያናችንና የአገራችንን ሰላምና አንድነት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተስፋ የተጣለበት የዋሽንግተን ዲሲው ሲኖዶሳዊ የዕርቀ ሰላም ውይይት፣ ሒደቱ የሚፈጸምበት እንጅ በመደራደር ብዛት የሚራዘምበት እንዳይኾን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአደራ መልእክታቸውን አስተላለፉ፡፡
የሀገር ቤቱን ቅዱስ ሲኖዶስ በመወከል የተሠየሙት ሦስቱ ልኡካን አባቶች እንዲሁም የሰላምና አንድነት ዓለም አቀፍ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ስምንት አባላት፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን ወደ አሜሪካ የሚያቀኑ ሲኾን፤ ረፋዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ካነጋገሯቸው በኋላ አበረታተው ሸኝተዋቸዋል፡፡
“ተስማምታችሁ ጨርሳችሁ፣ ብትችሉ ይዛችኋቸው መምጣት እንጅ በመደራደር ብዛት እንዳይራዘም፣ ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ ከፍላችሁ የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲመለስ ጥረት እንድታደርጉ አደራ እላለሁ፤” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ሰላምና አንድነት የአገርም ሰላም አንድነት መኾኑን ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ልኡካን አባቶችም አርኣያ እንዲኾኑ አማጥነዋቸዋል፡፡ በመደራደር ብዛት ጊዜ መግደል እንደማይገባና አስፈላጊ ከኾነም ከዕርቅ በኋላ በውጭ ያሉት ወደ አገር ተመልሰው በአንድነት ሊቀጥል እንደሚችል በመጠቆም የሰላሙን ቀዳሚነት በአጽንዖት ጠቁመዋል – “ድርድር አታብዙ፤ የተለየ ንግግር ካስፈለገ ከዕርቅ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ይቀጥል፤ አንድ ላይ እዚህ መጥቶ መነጋገሩ ይሻላል፤” ብለዋል፡፡
ሲኖዶሳዊው አንድነት፣“ትልቅ ጉዳይ ስለኾነ ነው በዚህ መልኩ የምንሸኛችሁ፤” እንዳሏቸው የጠቀሱት የሰላም ኮሚቴው አባላት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “ወደ ቤታችሁ ኑ፤ አገራችሁ ነው፤ ኑ በሏቸው፤” በማለት ለሒደቱ ሰላማዊ ፍጻሜ ትኩረት በመስጠት ያስተላለፉት መልእክት፣ ልዩ የሓላፊነት ስሜት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡ ለዓመታት የተደከመበት የዕርቀ ሰላሙ ጉዞ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ብለው እንደሚያምኑና በዋሽንግተን ዲሲው ውይይትም ሒደቱ ፍጻሜ እንዲያገኝ የተቻላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የኮሚቴው አባላት አስታውቀዋል፡፡
አክለውም፣“በሥነ ሥርዐት ጨርሳችሁ ከተመለሳችሁ፣ በሚሌኒየም አዳራሽ 25ሺሕ ታዳሚዎች ባሉበት ዕውቅና እንሰጣለን፤ ሰላም ግቡ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይኹን፤ እዚያ ስመጣ እንገናኛለን፤” በማለት ዶ/ር ዐቢይ በከፍተኛ ደረጃ አበረታተው እንደሸኟቸው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሐምሌ 21 እስከ 23 ቀን በአሜሪካ ሦስት ከተሞች(ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎሳንጀለስና ሜኒሶታ)ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን ጋራ የሚያካሒዱት ውይይት አመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢ የኾኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዋም፣ በትላንትናው ዕለት ለልኡካኑ አሸኛኘት አድርገውላቸዋል፡፡ ተልእኳቸው፣ የአገርና የሕዝብ ሰላምና አንድነት ጉዳይም እንደኾነ ጠቅሰው፣ “በውጤት እንደምትመለሱ ተስፋ እናደርጋለን፤” በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
በተመሳሳይ ኹኔታ፣ ትላንት ከቀትር በኋላ በመንበረ ፓትርያርኩ ለልኡካን አባቶችና ለሰላምና አንድነት ኮሚቴው አባላት ጸሎትና አሸኛኘት የተደረገላቸው ሲኾን፣ “ፈጽማችሁ እንድትመጡ” የሚለው መልእክት አጽንዖት እንደተሰጠው ተመልክቷል፡፡
የወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በዚሁ የሽኝት መርሐ ግብር፣ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰላምና የዕርቅ ቤት በመኾኗ፣ “ስለ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት መሥራት አለብን፤” ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ መከፋፈል የቤተ ክርስቲያን መገለጫ እንዳልኾነና ልኡካኑ ለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሒደት ፍጻሜ የተቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ እግዚአብሔር ያሳካላችሁ፤ ሲሉም ጉዟቸውን ባርከዋል፡፡
የዕርቀ ሰላም ሒደቱ፣ ቅዱስነታቸው የሰሜን አሜሪካ ሊቀ ጳጳስ እያሉ የጀመሩት እንደነበር ያወሱት በአሸኛኘቱ ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በበኩላቸው፣ አሁንም በቅዱስነታቸው ዘመነ ክህነት መፈጸሙ፣ “መልካም አጋጣሚና ዕድል ነው፤” ብለዋል፡፡ ዘመኑ፥ የፍቅር፣ የሰላምና የዕርቅ እንደኾነ ገልጸው፣ የዕርቀ ሰላም ሒደቱ፣ ቤተ ክርስቲያን በአርኣያነትና በምሳሌነት የምትጠቀስበት በመኾኑ ልኡካኑ የበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያም ኾነ በአሜሪካ የሚገኙ ብፁዓን አባቶች፣ ላደረጉላቸው ትብብርና ለሰጧቸው ቀና ምላሽ ልባዊ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ኹለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት ዓለም አቀፍ ኮሚቴ አባላት፣ “በኹለቱም በኩል ያሉ አባቶችን በማስማማት በቅርቡ የሰላምና የፍቅር ብሥራት ለኢትዮጵያ ይኾናል፤” ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ምሽት ወደ አሜሪካ የሚያቀኑት ሦስቱ ልኡካን አባቶች፡- ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ እና ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ ከእነርሱም ጋራ አብረው ከሚጓዙት መካከል የሰላምና አንድነት ዐቢይ ኮሚቴው አባላት ዶ/ር ንጉሡ ለገሰ እና ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ ካሳ፣ ከአዲስ አበባው ቅርንጫፍ ደግሞ ዶ/ር አብርሃም አስናቀ፣ ዶ/ር ደምሴ፣ አቶ ብርሃን ተድላ፣ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴና አቶ ግርማ ዋቄ የሚገኙበት ሲኾን፣ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም በዚያው በአሜሪካ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡