የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሃሙስ ሰኔ 28/2010 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ አርበኖች ግንቦት 7፣ ኦነግና ኦብነግን ከዚህ ቀደም አሸባሪ ድርጅቶች ናቸው በሚል የአገዛዝ ሥርዓት የፈረጀውን ፍረጃ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማንሳቱ የሚበረታታና የሚደነቅ ውሳኔ ነው፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ይህንን የምክር ቤቱን ውሳኔ አስቀድሞም ቢሆን ድርጅቶቹ የነጻነትና የዲሞክራሲ ታጋዮች መሆናቸውን በመገንዘብ ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል መድረክ ይፈጥር ሲል የነበረ በመሆኑ፤ ምክር ቤቱ አሁን ከጊዜ ቆይታና በዚህ ፍረጃ ምክንያት በርካታ ዜጎቻችን ከተሰቃዩ እና መሰዋዕት ከሆኑ በኋላ ፍረጃውን ወደማንሳት ውሳኔ በመምጣቱ ሰማያዊ ፓርቲ የሚያደንቅ ቢሆንም በዚህም ምክንያት ለተፈጠረው ቀወስ የታሪክ ተጠያቂዎች መኖራቸው ፓርቲያችን ያምናል፡፡ ይህ በእንዲህ እናደለ የተላለፈው ወሳኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ሰማያዊ ፓርቲ እምነቱ የጸና ነው፡፡
የኦሮሞ ህዝብን ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብት ለማረጋገጥ ኦነግ እጅግ መራር ትግል ሲያካሂድ እንደቆየ ሰማያዊ ፓርቲ ይገነዘባል፡፡ በተመሳሳይ ኦብነግ የሶማሌ ኢትዮጵያውያን ዜጎች መብታቸው አንዲከበር ከአብራኩ የወጡ ልጆቹ ዲሞክራሲን ለማስፈንና እንደሌሎች ወንድሞቹ በሃገራቸው እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ዋጋ ሲከፍሉ እንደቆዩ በገሀድ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ ምርጫ 97ን ተከትሎ የአገዛዙ ሥርዓት የህዝብን ድምጽ በመቀማት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በእምቢተኝነት በመርገጥ ያሳየውን ጭፍን አምባገነን አገዛዝ፤ ከኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ ለማውረድሁሉን አቀፍ ትግል በማድረግ የህዝብን ድምጽና ዲሞክራሲያዊ መብት እናስመልሳለን በማለት አርበኞች ግንቦት 7 ተመስርቶ ላለፉት 10 ዓመታት ትግል ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህ ድርጅቶች ለነጻነት ሲያደርጓቸው የነበሩት ትግሎች፤የአገዛዙ ሥርዓት በሰላማዊ ትግል ለመፎካከር ያደርጉት የነበረውን ቀና አካሄድ መዝጋቱ አማራጫቸው አድርገው ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ፓርቲያችን ያምናል፡፡ ይህ አማራጭ የዜጎችን ህይወት፣ ንብረት የሚያወድምና አሸናፊ ተሸናፊ በሌለው በወንድማማቾች መካከል የሚካሄድ ደም መፋሰስ ውስጥ ከቶን የነበረ አሳዛኝ የታሪካችን ምእራፍ ነው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ይሄንን አሳዛኝ የታሪካችን ምዕራፍ ለመዝጋት እና የሃሳብ ብዝሃነትን የምታስተናግድ አገር እውን ለማድረግ በተለያዩ የፖለቲካ መስመር ተደራጅተው ሲታገሉ ለነበሩትን የፖለቲካ ተዋናዮች ጥሪ ማቅረባቸው የምንደግፈው ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህን ድርጅቶች ሆነ በተለያየ አካባቢ መብቶቻቸውን ለማስከበር ትጥቅ አንግበው በዱር በገደሉ የሚዋደቁት ዜጎቻችን፤ ለዚህ ያበቃቸው መሰረታዊ የሰብዓዊና የዲሞክራሲ ጥያቄ እውን ለማድረግ የሰው ሃይል፣ ትጥቅና ስንቅ አደራጅተው እየተንቀሳቀሱ የነበረ፤ እንደ ዜጋ ለዲሞክራሲ መስፈን መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጁና ከቤት ንብረታቸው ተለይተው የነበሩ መሆናቸውን ሰማያዊ ፓርቲ ይገነዘባል፡፡
እነዚህ ድርጅቶችም ሆነ ሌሎች ቀድመው በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴያቸውን አፍኖ የነበረው የተለያዩ ህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች፤ የሲቪክ መብት ፣የመደራጀትና የሰብአዊ መብት መከበርን የሚጻረሩ አዋጆች እንዲሁም ተቋማት ነጻ፣ ገለልተኛ እና ፍትሃዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል እርምጃ በቀጣይ በተጨባጭ ማከናወን ካልተቻለ ለዲሞክራሲ ትግሉ " እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው" እንዳይሆን ትልቅ ስጋት እዳለው ሰማያዊ ፓርቲ ሳይገልጽ አያልፍም፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በተለይ በሕብረብሔራዊ አስተሳሰብና በሰላማዊ ትግል የሚታገሉ ድርጅቶች ጋር አብሮ ከመስራት ጀምሮ እስከ መዋሃድ የሚደርስ እርምጃ ለማከናወን ፈቃደኛ እንደሆነ ከዚህ ቀደም በስራ አስፈጻሚና በምክር ቤት ደረጃ በተሰጡ ተደጋጋሚ መግለጫዎች ላይ አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡ አሁንም ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር አብሮ ከመስራት እስከ ውህደት ድረስ ለመስራት ፓርቲያችን ፈቃደኛ በመሆኑ የአርበኞች ግንቦት 7 ድርጅት አመራሮች ጋር በመገናኘት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ፡-
1ኛ. በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ተቋማትን ነጻና ገለልተኛ ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ህዝብ እና ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ከሚመራው መንግስት ጋርመነጋገር በሚቻልበት መንገድ ላይ፤
2ኛ. ሁሉም በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ የተለያዩ ድርጅቶች ሰራዊቶቻቸውን ሳይበትኑ ሃገርን መጥቀም የሚችሉ ዜጎች የሚሆኑበትን እና እንደፍላጎታቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል ሆነው በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ ፤
3ኛ. የዜጎች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በእኩልነትና በተቋም ታግዞ ማስከበር የሚችል፣ የህዝብን አብሮ የመኖርና የመተማመን መንፈስ የሚያጎለብት እና ከጎረቤት አገራት ጋር በመተሳሰብ በጉርብትና መንፈስ ሊያኖረን የሚችል የዜጎች ተሳትፎ በነጻነት የሚያሳትፍ ህገ መንግስት ተዘጋጅቶ እውን በሚሆንበት ሁኔታ ላይ በዋነኝነት እንዲወያይ የሰማያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ወስኗል፡፡
በመሆኑም ይሄንን ውይይት ስኬታማ እንዲሆን ለማድረግ ከዚህ ቀደም ከሌች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንድንሰራ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የነበረው የሰሜን አሜሪካ ሸንጎ አሁንም ይሄንን ቅን አካሄዱንና እሳቦቱን በመጠቀም ፓርቲያችን ከአርበኞች ግንቦት 7 ድርጅት ጋር ለመስራት የሚያደርገውን ከፍተኛ ፍላጎትና ጥረት እንደ ከዚህቀደሙ ሁሉ ከፍተኛ ሚናውን እንደሚጫወት የሰማያዊ ፓርቲ እምነት ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሰማያዊ ፓርቲ አጥብቆ የሚደገፍ ከመሆኑ በተጨማሪ፤ የኢትዮ-ኤርትራ ሁኔታ በዘላቂነት የሁለቱ አገሮችና እና ሕዝቦችን ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ መስተጋብር በይብልጥ የተሳለጠ እንዲሆን እና የሁለቱ አገሮች የጋር ጥቅም ለመጠበቅ በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት እና እንቅስቃሴ ሰማያዊ ፓርቲ የበኩሉን አሰተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በተለይ በሁለቱ ወንድማማች አገሮች መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀው ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታ በአዲስ ምዕራፍ በመቀየር የኢትዮ-ኤርትራ ወንድማማችንት ለማጠናከር በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት የተጫወተው ሚና ሰማያዊ ፓርቲ ያደንቃል ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከላይ በተጠቀሱት እና በሌሎች ወቅታዊ አንገብጋቢ የሀገራችን ጉዳዮች ላይ ሰማያዊ ፓርቲ ለጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ደብዳቤ በማስገባት በውይይት የሀገራችንን ችግር ለመፍታት የበኩሉን በጎ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁነቱን እየገለጸ ወደፊቱ በደብዳቤውና በውይይቱ ፣ ዙሪያ የደረስንበትን ዝርዝር መግለጫ ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን፡፡
በመጨረሻም በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው ለውጥ ስኬታማ የሚሆነው በዜጎች የሰከነ እና ዘመን ተሸጋሪ በሆኑ አስተሳሰቦች ላይ ሲመረኮዝ ብቻ እንደሆነ ሰማያዊ ፓርቲ ይገነዘባል፡፡ ስለሆነም ለጊዜያዊ ስልጣን ማጣት አልያም ዝና እና ሃብት ተብሎ ትልቅ የሆነውን ዜጎችን በእኩልነት የሚኖሩባት አለኝታ የምትሆን ሃገራችንን በጋራ በመገንባት ፋንታ " እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል " እንደሚለው ብሂል ወደ እኩይ መንገድ ተመለስን እንዳንገባ ሃገራዊ ጥሪውን ሰማያዊ ፓርቲ በድጋሚ ለማቅረብ ይወዳል፡፡
ሐምሌ 3 ቀን 2010ዓ.ም
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር !
ሐምሌ 3 ቀን 2010ዓ.ም
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር !
No comments:
Post a Comment