Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, July 11, 2018

ለአ/አበባ ሀ/ስብከት ችግሮች አጣሪ ኮሚቴ ሰብሳቢው፣ ከሀገረ ስብከቱ ገቢ እንዲከፈላቸው የታዘዘው 50ሺሕ ብር እያነጋገረ ነው



pat megabe kahinat haile ze collusion
  • መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም፣የአጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ናቸው፤
  • ለኮንዶሚኒየም ግዥ የተበደሩትን መክፈል ስላቃታቸው ርዳታ ተፈቀደላቸው፤
  • ገንዘቡ የሚከፈላቸው ከሀገረ ስብከቱ ገቢ ላይ ሲኾን፣ማጣራቱ ግን አላለቀም
  • ለምን ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ አይከፈልም?በምንስ አግባብ ሊፈቀድላቸው ቻለ?
†††
  • ሌሎች ሊቃውንትና ሠራተኞችስ በተመሳሳይ ቢጠይቁ ይፈቀድላቸዋል ወይ?
  • ኮንዶሚኒየም ከገዙ፣የተከራዩትን የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ቪላስ ያስረክባሉ ወይ?
  • ልዩ ሀ/ስብከት ካልተነሣ የፓትርያርኩ የጓሮ ሽንኩርት መኾኑን ይቀጥላል፤”
  • “የመዋቅር ለውጥ እንጅ፣የ4 ወይም የ44 ጳጳሳት ምደባ አይታገደውም!”
†††
ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ፣ በቤተ ክርስቲያኒቷ ሕግ ፊት እኩል የመታየት፤ በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በሀብት ወይም በሌሎች ከሚፈጸም አድሎአዊ አሠራር የመጠበቅ መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ ኾኖም ሕግ መደንገጉ ብቻ፣ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ግንባር ቀደም ኾና የምትቆመውን ቤተ ክርስቲያናችንን፣ በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከመነቀፍና ከመተቸት አላዳናትም፡፡መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ሌብነትን መከላከል፣ ዘረኝነትን መዋጋት አለመቻሉ፤ በሚሰጠውም ምክር የማስተካከያ እርምት ለማድረግ በጎ ፈቃድ አለመታየቱ፣ በቁጥር አንድ ከፈጠራቸው ክፍተቶች አንዱ፣የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደኾነ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደረጃ ሳይቀር ታምኖበታል፡፡
የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የኾነው አዲስ አበባ፣ ለችግሩ በዋና ማሳያነት ሲጠቀስ፣ 253 አገልጋዮች ከሌብነትና ጠባብነት መስፋፋት ጋራ ተያይዞ በሚፈጸም አድልዎ ከሥራ እንደተፈናቀሉና እንደታገዱ በምልኣተ ጉባኤው ላይ ተገልጿል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በሕዝብና በመንግሥት አካላት ዘንድ፣ አገልጋይ ለመቅጠርም ኾነ ለማዛወር፣ እንደየሥራው ዘርፍና ምድብ ለቦታው ለመስማት በሚዘገንን መልኩሊቃውንትን በማጉላላትና ገንዘብ በመቀበል ቤተ ክርስቲያኗን በሚያሳዝን መልኩ ያስተናግዳል እየተባለ ይተቻል፤ ችግሮቹ ዕለት ተዕለት ከመባባሳቸውና መፍትሔ ካለማግኘታቸው የተነሣ፣ የቤተ ክርስቲያን ሀብት የኾኑ የአብነት መምህራን የባለጸጋ ቤት ዘበኛ/ጥበቃ ኾነዋል፤”ብሏል – በምልዓተ ጉባኤው ላይ ለመነሻ የቀረበውና ወቅታዊ ችግሮችን የሚዳስሰው ጥናት፡፡
እነኝህን ችግሮች በምርመራ አጣርቶ ሪፖርት እንዲያቀርብ፣ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ባለፈው ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. አምስት አባላት ያሉበት ኮሚቴ የሠየሙ ሲኾን፣ ሰብሳቢው ደግሞ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊ መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም ናቸው፡፡ ኮሚቴው በተቋቋመበት የፓትርያርኩ ደብዳቤ መሠረት፣“የሀገረ ስብከቱን የአስተዳደር ችግር፣ የሙስና ተግባርና ሌሎችንም የአሠራር ጥሰቶች” በተበዳዮች አቤቱታና የማስረጃ ሰነዶች እያጣራ ሰንብቷል፡፡ ኾኖም፣ የምርመራ ሪፖርቱን አጠናቅሮ እንዲያቀርብ የተቀጠረበት ከአራትና አምስት ያልበለጡ ቀናት በቀሩበት ዛሬ፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ ከሀገረ ስብከቱ እንዲወስዱ የተቀፈደላቸው የ50ሺሕ ብር ርዳታ በከፍተኛ ደረጃ እያነጋገረ ይገኛል፡፡
pat megabe kahinat haile letter - Copy
መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ርዳታውን የጠየቁት፣የኮንዶሚኒየም ቤት ሲገዙ ከግለሰብ የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈል“ከአቅሜ በላይ ስለኾነብኝ ነው፤” በሚል ነው፡፡ ቋሚ ሲኖዶስ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ 50ሺሕ ብር ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እንዲሰጣቸው መወሰኑንና በውሳኔውም መሠረት፣ከሀገረ ስብከቱ ገቢ ላይ ገንዘቡ ወጪ ኾኖ እንዲከፈል ትእዛዝ ተላልፏል፡፡
መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የመምሪያ ሓላፊነት ደረጃ ያሉ ቢኾንም፣ ከአምስት ዓመት በፊት በጡረታ መሰናበታቸውንና በአሁኑ ወቅት በኮንትራት ውል መቀጠላቸውን የጠቀሱ አስተያየት ሰጭዎች፣“እንደ ቋሚ ሠራተኛ እንዴት ብድግ ተደርጎ ይሰጣቸዋል?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የመኖርያ ቤት ችግር፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱም የሀገረ ስብከቱም ብዙ ሠራተኞች ችግር እንደመኾኑ፣ “ቋሚ ሲኖዶሱ ተመሳሳይ ጥያቄ በእኩልነት ያስተናግዳል ወይ?” ለሚለው ጥያቄአቸው ምላሽ ይሻሉ፡፡
በቀድሞው መንግሥት የተወረሱ ቤቶችንና ይዞታዎችን ለማስመለስ እየተደረገ ባለው ጥረት የሚታወቁት መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ፣ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በአነስተኛ ክፍያ በተከራዩት ቪላ ቤት ነው እየኖሩ የሚገኙት፡፡ ለኮንዶሚኒየም ግዥ ዕዳ መክፈያ ርዳታ መጠየቃቸው በራሱ ባይነቀፍም፣ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸውና ለቤተ ክርስቲያን የደከሙ ሊቃውንትስ ምን ያህል ታይተዋል? ወደገዙት ኮንዶሚኒየም ቤት ገብተው የተከራዩትን ቪላ ያስረክባሉ ወይስ እንደተለመደው የተከራይ አከራይ ኾነው መብላታቸውን ይቀጥላሉ? የሚልም ጥያቄ አላቸው፣ አስተያየት ሰጭዎቹ፡፡
Debramarkos faithfuls petition
ከሁሉ በላይ አነጋጋሪ የኾነው ግን፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የኮንትራት ሠራተኛ እስከኾኑ ድረስ የገንዘብ ርዳታው ለምን ከዚያው እንዲሰጣቸው አልተደረገም? የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የርዳታ ድርጅት ነው ወይ የምእመናንን ገንዘብ እያነሡ የሚሰጡት? የሚል ነው፡፡ የሀገረ ስብከቱን የሙስና ተግባራትና የአሠራር ጥሰት የሚያጣራ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኾነው እያለና የማጣራቱ ውጤት ተጠናቆ ውጤቱ ባልታወቀበት ኹኔታ አግባብነት ይኖረዋል ወይ?“በማጣራት ሒደት የተገኙ ማስረጃዎችን መደራደሪያ እያደረጉ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብቶችና ጥቆሞች አሳልፈው የሚሰጡ፣ ከተበዳዩ ይልቅ ዘራፊውን ነጻ የሚያወጡ ሐሰተኛ ሪፖርቶችን ማቅረብ በተለመደበት ኹኔታ፣አድርባይነት ለሚጫናቸው መጋቤ ካህናቱ፣ ለ“አጣሪነታቸው” ውለታ የተከፈለ እንዳይኾን እንሰጋለን?” ይላሉ፡፡
በቋሚ ሲኖዶስ የተላለፈ ውሳኔ እንደኾነ ቢገለጽም፣ ቋሚ ሲኖዶሱ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የተዘረዘሩ ተግባራትና ሓላፊነቶቹን ማስጠበቅ እንዳልቻለ፣ ረዳት ሊቀ ጳጳሱ በፓትርያርኩ አሻፈረኝ ባይነት በስሙ ከተመደቡበት “የሐሰት የሹመት ደብዳቤ” በላይ ማሳያ የለም፡፡በምልዓተ ጉባኤውም ባይኾን ቋሚ ሲኖዶሱ በወጉ ተወያይቶ የያዘውና የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ፓራፍ ያደረጉበት ቃለ ጉባኤና ደብዳቤ ሳይኖር፣ብፁዕ ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም፣ በቅዱስ ሲኖዶስ እንደተመደቡ ተደርጎ በአቀባበል መርሐ ግብሩ ላይ የተነበበው ደብዳቤ፣ ፍጹም ሐሰትና የለየለት ፓትርያርካዊ እብሪት ነው፡፡
ከዚህ በመነሣት፣ በልዩ ሀገረ ስብከት ሽፋን ፓትርያርኩ እንዳሻቸው ከሚወስኑበት የአዲስ አበባ ገቢ፣ ችግሩን እያጣሩ ለሚገኙት ለመጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም አላግባብ እንዲሰጥ የታዘዘው የ50ሺሕ ብር የገንዘብ ርዳታ፣በቋሚ ሲኖዶስ የተወሰነ ነው፤ ቢባል ማንን ያሳምናል? ለአዲሱ ሥራ አስኪያጅስ፣ እንዲህ ዐይነትና መሰል ትእዛዛት ፈተና አይኾኑባቸውም ወይ?
sealite mih2010d
በሌብነትና ጎሠኝነት የሚገለጽ አድሏዊነትና የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚያምሰው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ መድኅኑ የኾነውንና ከ96 በመቶ በላይ ሊቃውንትን፣ ካህናትን፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ድጋፍ ያረጋገጠውን የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥእስካልተገበረ ድረስ፣ በልዩ ሀገረ ስብከት ሽፋን፣ የፓትርያርኩ የጓሮ ሽንኩርት መኾኑን ይቀጥላል!
ሌላ ሌላውን ትተን፣ ከመደበኛ ደመወዛቸው ውጭ በየወሩ በሀገረ ስብከቱ የደመወዝ መክፈያ መዝገብ ተካትተው የዚያኑ ያህል ይወስዳሉ መባሉ ሳይበቃ፣ለነዳያን በረከት እንዲናኙ” በሚል በየወሩ 150ሺሕ ብር እንደሚወጣ የሀገረ ስብከቱና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች እየተቹበት ያለ የባጀ ወግ ነው፡፡ እናም ሀገረ ስብከቱ፣ ከሰው ኃይሉና ፋይናንሳዊ ሀብቱ አኳያ፣በስትራተጅያዊ ተቋማዊ የአመራር ለውጥ ራሱን ችሎ እንዲመራ ከማድረግ ውጭ፣ስንኳን በረዳት ሊቀ ጳጳስ ቀርቶ በአራትም ኾነ በ44 ሊቃነ ጳጳሳት መመራቱ ከቶውኑም አይታደገውም!!

No comments:

Post a Comment

wanted officials