(Celebrity Worship)
(ግሩም ተበጀ)
ክፍል አንድ
✍️ City Lights የተሰኘውን የቻርሊ ቻፕሊንን ፊልም ለመመረቅ አልበርት አይንስታይንና ቻርሊ ቻፕሊን ሎስ አንጀለስ እንደገቡ፣ የሎስ አንጀለስ ነዋሪ ግልብጥ ብሎ ነበር የተቀበላቸው።
✍️ የህዝቡ እንዲህ በነቂስ ወጥቶ እነሱን መቀበል፣ የሚዲያው ወከባ ሁሉ፣ ለአይንስታይን ፍፁም ግራ የሚያጋባ ነበር የሆነበት። በዚህ ወከባ መሃል፣ ቻርሊ ቻፕሊን ወደ አይንስታይን ጆሮ ጠጋ ይልና እንዲህ ይለዋል፣
✍️ “ይሄ ሁሉ የሰዉ ግርግር ለምን ይመስልሃል…እኔ ስለገባኋቸው ነው - አንተ ደግሞ ስላልገባሃቸው !”
✍️ የሆነው ሆኖ አይንስታይን እግሩ የአሜሪካን አፈር ከረገጠበት ጊዜ አንስቶ ባስተዋለው የአሜሪካ ህዝብና ሚዲያ ለስመ-ጥሮች ባለው ከልክ ያለፈ አምልኮ እንደተገረመ ነበር።
✍️ በየሄደበት ቦታ ሁሉ፣ እንደልዩ ፍጡር የሚከበውን የሰው አጀብ ባየ ቁጥር፣ አጠገቡ ያሉትን የሚጠይቀው ጥያቄ፣ “ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ሰው ስራዬን አንብቦ ተረድቶ ነው?” የሚል ነበር፡፡
👉 ፈፅሞ…!
✍️ እንዲያውም፣ የአይንስታይንን አጠቃላይ የአንፃራዊነት ንድፈ-ሃሳብን በተመለከተ የምትጠቀስ አንዲት ቀልድ አለች።
✍️ የአይንስታይንን አጠቃላይ የአንፃራዊነት ንድፈ-ሃሳብን በእንግሊዝኛ ተናጋሪው ዓለም እንዲታወቅ ያስቻለውን እንግሊዛዊውን ሳይንቲስት ኤዲንግተንን አንድ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፡፡
✍️ “ለመሆኑ፣ አጠቃላዩን የአንፃራዊነት ንድፈ-ሃሳብ የሚረዱ ሰዎች ሦስት ብቻ ናቸው ይባላል፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ትላለህ?” “በእውነት…?” ይላል ኤዲንግተን ተገርሞ፣ “ለመሆኑ ሦስተኛው ሰው ማን ይሆን?” (እንግዲህ ሁለቱ ሰዎች፣ ራሱ ኤዲንግተንና አይንስታይን መሆናቸው ነው።)
✍️ አይንስታይን በደንብ በሚያውቃት አውሮፓ ውስጥ በአሜሪካ ያየው ዓይነት የተደራጀ ህዝባዊ የዝነኞች አምልኮ (Celebrity Worship) የለም። ስራውን ያነበቡ ሊያናግሩት ይመጣሉ፤ በታላቅ ሳይንቲስትነቱ አክራሪ የናዚ ወጣቶች እንኳ ያከብሩታል፡፡
✍️ ከዚህ አልፎ ግን፣ የአሜሪካው ዓይነት ፍፁም ያበደና ከልክ ያለፈ፣ ወደ አምልኮ ያዘነበለ ህዝባዊ አድናቆት ግን የትም አላጋጠመውም። “ስራዬን አንብቦ ያልተረዳ ሰው እንዴት ያደንቀኛል…” ሲል የሚሞግተው አይንስታይን፣ ስራውን ሳያነቡና ሳይረዱ የሚያደንቁትን ሰዎች ጉዳይ እንደ ስድብ ነው የሚቆጥረው።
✍️ ኋላ ላይ ግን፣ አይንስታይን፣ የአሜሪካን ህዝብና የሚዲያ ባህል ይበልጥ እየገባው ሲመጣ፣ ጭራሽ በጉዳዩ ላይ ምክር ለጋሽ ሆኖ አረፈው።
✍️ ለዓለም ሰላም የሚታገለውን አንድ የሂሳብ ፕሮፌሰር፣ አይንስታይን እንዲህ ነበር ያለው፣ “የዓለም ሰላም የምትለውን ኃሳብ እርሳው። ይልቅ ዝም ብለህ ሂሳብህን ስራ…ከዛ ታወቅ…ያኔ የፈለግከውን ብትላቸው ይሰሙሃል። አሁን ግን አንዲህ ታዋቂ ሳትሆን፣ ምን ሃሳብህ ድንቅ ቢሆን፣ ማንም የሚያዳምጥህ የለም።”
✍️ እንግዲህ የዛሬ 60 ዓመት ገደማ አሜሪካ እንዲህ ነበረች። የአሁኑ ደግሞ ጨርሶ ብሶባት ምሁራኖቿ ወደ አንዳች ታላቅ ባህላዊ ክስረት እያመራን ነው እያሉ ነው።
✍️ በአሜሪካ የባህል ግዛት ውስጥ ሆነን፣ ከምዕራቡ ዓለም የተገኘውን ቁሳዊም ሆነ ባህላዊ ኮተት በመሰብሰብ የተጠመድነው እኛም ብንሆን፣ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ሀገር በቀል ችግሮቻችን ባሻገር፣ ይሄን አደገኛ ርካሽ ባህላዊ ክስተት እያራገብን ስለሆነ እጅጉን የሚመለከተን ጉዳይ ነው።
✍️ አሜሪካ ውስጥ በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት፣ ከሦስት አሜሪካውያን አንዱ፣ ስመጥርና ዝነኛ ሰዎችን በማምለክ ስነ-ልቦናዊ አባዜ (Celebrity Worship Syndrome) ተጠምደዋል ሲል ይጠቁማል።
✍️ ጥናቱ፣ ይህ ስነ-ልቦናዊ ጣጣ የተለያዩ ደረጃዎች እንዳሉት ጠቅሶ፣ አንዳንድ የዚህ ስነ-ልቦናዊ አባዜ ተጠቂዎች ከሚያመልኩት ዝነኛ ሰው ጋር አንዳች የነፍስ ጥምረት አለን ብለው እንደሚያምኑ ይጠቅሳል።
✍️ ይህ ዓይነት ስነ-ልቦናዊ ክስተት ደግሞ በፋንታው ወሰን ለለቀቀ የቀን ህልምና እሱን ተከትሎ ለሚመጣው ለማህበራዊ ህይወት ውጥንቅጥ እንደሚዳርግ ግልፅ ነው።
✍️ ሌሎች የዚህ ስነ-ልቦናዊ ጣጣ ሰለባዎችም ቢሆኑ፣ የሚያመልኩትን ስመ-ጥር ሰው ህይወት አሳዶ በመከታተል አባዜ በመጠመድ፣ የራሳቸውን የኑሮ ኃላፊነት ሲዘነጉ ተሰተውሏል።
✍️ ብስጩነትና፣ ተለዋዋጭ ባህሪም ቢሆን በዚህ ስነ-ልቦናዊ ጣጣ ተጠቂዎች ላይ ተደጋግሞ የሚስተዋል ክስተት ነው። የችግሩ አስፈሪ ጎን ያለው ግን፣ የአንዳንድ የጥናቱ ተሳታፊዎች የዝነኛ አምልኮ ደረጃ እዚህ ድረስ የመድረሱ ጉዳይ ነው፤ “ምንም ያህል ጉዳዩ ህገወጥ ቢሆን፣ የማደንቀው ሰው አድርግልኝ ቢለኝ የማላደርገው ነገር የለም!”
✍️ እዚህ ድረስ የሚደርስ ነው እንግዲህ የዝነኞች አምልኮ ጣጣ ጉዳይ። በዚህ ጉዳይ ላይ የፃፈችው ካርሊን ፍሎራ፣ የአንድ ወቅት የዝነኛ ገጠመኟን (Celebrity Encounter) እንዲህ ስትል ትገልፀዋለች
✍️ “ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው፣ ብሪትኒ ስፒርስ ከነአጀቧ በአለቃዬ ቢሮ በኩል ስታልፍ አየኋት። ኮራ ዘና ባለ አረማመድ በአጠገቤ ስታልፍ…በድንጋጤ ፊቴ ሲግል ይታወቀኛል። እንደምንም የሞት ሞቴን በጠረጴዛዬ ላይ አሻግሬ ልጨብጣት እጄን ዘረጋሁ። ብሪትኒ በቀጥታ ዓይኔ ውስጥ እየተመለከተች፣ ያን ገዳይ ፈገግታዋን ፈገግ ሰትል፣ እውነቴን ነው የምላችሁ ደንዝዤ ቀረሁ።
✍️ ከዛ በኋላ ወዲያውኑ ለጓደኞቼ እየደወልኩ አስደናቂውን የዝነኛ ገጠመኜን ማብሰር ጀመርኩ። ‘እንዴት አምሮባታል መሰላችሁ…እስከ ወለሉ የሚደርሰው ነጭ የሃር ኮቷ…ቆዳዋ ደግሞ…’ እያልኩ”
✍️ “ግን አንድ ነገር ልብ ልትሉ ይገባል…” የምትለው ፀሐፊዋ፣ “እኔኮ ፈፅሞ የብሪትኒ አድናቂ አልነበርኩም። ታዲያ ለምንድነው ብሪትኒን ማግኘቴ ይሄን ያህል አቅሌን እስካጣ ያደነባበረኝ” ስትል ትጠይቃለች።
✍️ መልሱ ግን፣ በአብዛኛው በምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም በአሜሪካ ስር እየሰደደ ከመጣው ልቅ የሆነ የዝነኛ አምልኮ (Celebrity Worship) ጣጣ የሚዘል አይደለም።
✍️ የዚህ ባህላዊ ውዥንብር ዋንኛ መጠንሰሻ ደግሞ፣ በሆሊዉድ የሚመራው የምዕራቡ ዓለም የፊልም፣ የሙዚቃና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ነው። “ከዚህ ሁኔታ ጀርባ ምንም ዓይነት የተለየ ድብቅ አጀንዳ የለም…” የሚሉት የኒውዮርክ ታይምሱ ሃያሲ ማርቲን ሜየር፣ “ብዙ ታላላቅ የሰው ልጅን ፈተናዎች በአሸናፊነት የተወጣው የምዕራቡ ዓለም ስልጣኔ፣ በስተመጨረሻ፣ ከመሰላቸትና ከድብርት ጋር ታላቅ ትንቅንቅ ገጥሟል” ይላሉ።
✍️ በዕርግጥም የመዝናኛው ኢንዱስትሪ በማኅበረሰቡ ሁለንተና ፊት የሚያዛጋውን ታላቅ የድብርትና የመሰላቸት ዓዚም ለመግፈፍ ብዙ አዳዲስ ድርጊቶችን መዘገብ፣ ጀግኖችን ፈልፍሎ ማውጣት ይጠበቅበታል።
✍️ በዚህ ተግባር የምዕራቡ ዓለም የመገናኛ ብዙሃንና የመዝናኛ ኢንዱስትሪው አልሰነፉም የሚሉት የናሽናል ሪቪው ፀሐፊ ፖል ሆላንደር፣ “ችግሩ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ነው” ባይ ናቸው።
✍️ “የህዝቡ የአዲስ ነገር አምሮት አጅጉን ስለበረታ ከዚህ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የአዝናኝና አስደናቂ ክስተት አቅርቦት ሊኖር አልቻለም።
✍️ ሰዉ፣ በሚዲያው፣ ብዙ አዳዲስና አስደናቂ ክስተት፣ ብዙ ብዙ ጀግኖች ማየት ይፈልጋል” የሚሉት ሆላንደር፣ “እውነተኛ አስደናቂ ክስተቶችና የምር ጀግኖች ደግሞ ከስንት አንዴ የሚከሰቱና አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ በመሆናቸው፣ የስልቹውንና ማለቂያ በሌለው የአዳዲስ ነገሮች አምሮት የተለከፈውን ህዝብ ፍላጎት ለማሟላት፣ ሚዲያው አዳዲስ ዝነኞችን ከየትም እያነሳ ወደ መፈብረክ አምርቷል” ይላሉ።
**************************
👉 ውድ የኢንፎ ቶሎ ቤተሰቦች ጽሁፉን ስላነበባችሁልን ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ክፍል ሁለትን ነገ የምናቀርብላችሁ ይሆናል፡፡ እስከዚያው በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያላችሁን አስተያየት አጋሩን፡፡ መልካም ቀን፡፡
No comments:
Post a Comment