Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, January 30, 2014

በ2014 የዓለም የመፈንቅለ መንግሥት አደጋ ካንዣበበባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ 25ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡


coup map
“በ2030 ከሚከሽፉ መንግሥታት አንዷ ኢትዮጵያ ነች”
በያዝነው የአውሮጳውያን ዓመት ሊከሰቱ የሚችሉ የመፈንቅለ መንግሥት አደጋዎች ይፋ ሆኑ፡፡ በርካታዎቹ በአፍሪካ አገራት ሲሆኑ አደጋው ካንዣበበባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ 25ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በአሜሪካ የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑት ጄይ ዑልፌልደር የተለያዩ የሒሳብ ስሌቶችን በመጠቀም የ2014ዓም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ትንበያ ከሆነ 40 አገራት ቀይ የአደጋ ምልክት በርቶባቸዋል፡፡ ስለ ጉዳዩ ሲናገሩ መፈንቅለ መንግሥት እንዲሆን የሚመኙት ነገር ባይሆንም የመከሰቱ ጉዳይ ግን መነገር ያለበት ነው ይላሉ ምሁሩ፡፡
በተለያዩ የአሜሪካ አንጋፋ ጋዜጦች ላይ የተዘገበው ይኸው ጥናት እንደሚያመለክተው በዓለማችን ላይ 40 አገራት ከፍተኛ የመፈንቅለ መንግሥት አደጋ ያነጣጠረባቸው መሆናቸውን በጥናቱ ተገልጾዋል፡፡ አብዛኛዎቹም ከአፍሪካ መሆናቸው አሁንም አህጉሪቱ ለበለጠ ቀውስ የተጋለጠች መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡
forecast-dot-2014በቀዳሚነት የመፈንቅለ መንግሥት የሚያሰጋቸው አገራት ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ማሊ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኒጀር፣ ጊኒ ቢሳው እና ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክና ደቡብ ሱዳን ናቸው፡፡ ከአውሮጳ ምንም አገር በዝርዝሩ ውስጥ ያልገባ ሲሆን ዩክሬይን አደጋው ጥላ ካጠላባቸው በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሆናለች፡፡ ከወደ አሜሪካ ዩኳዶርና ሃይቲ ቀዩ የአደጋ ምልክት የታየባቸው ሲሆን ከእስያ ታላንድ፣ አፍጋኒስታን እና ፓኪስታንን ጨምሮ ስድስት አገራት የመፈንቅለ መንግሥት የቀይ ምልክት አደጋ ካለባቸው 40 አገራት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከ40ዎቹ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ 25ኛ ላይ ትገኛለች፡፡ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ህወሃት/ኢህአዴግ ሥልጣኑን ለራሱ ታማኞች ብቻ በመከፋፈል እንዲያም ሲል በቤተሰብ ደረጃ በማውረድ እየሸነሸነው በመሆኑ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የበይ ተመልካች ሆኗል፡፡ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሰሞኑን ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ አዲስ አድማስ ሲዘግብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን እና የነጻው ሚዲያ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ገልጾ ነበር፡፡
አፋኝ ሕጎችን በማውጣትና ማንኛውንም ዓይነት የግለሰብ መብት በመንፈግ በአንጻሩ ሊኖር የማይችል የቡድን መብት አስከብራለሁ የሚለው ህወሃት/ኢህአዴግ በተመሳሳይ የሚወጡ መረጃዎችን በማጣጣል ዋጋ ቢስ ሲያደርግ መቆየቱን የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በየጊዜው የሚያነሱት ነጥብ ነው፡፡ በተቀረው ደግሞ “ልማት፣ ህዳሴ፣ ውዳሴ፣ … ” በማለት የለውጥ ሃሳብ ከመጣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ይስተጓጎላሉ በሚል በሕዝቡ ዘንድ ማደናገሪያ በመፍጠር በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎች “ጸረ ልማት” በማለት እንደሚወነጅላቸው ያማርራሉ፡፡ በምርጫ ማጭበርበርና ማንኛውንም ፖለቲካዊ ሆነ ማኅበራዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በሙሉ ቁጥጥር ሥር ማዋል ኢህአዴግ በሥልጣን ለመቆየት የሚጠቀምባቸው ዓይነተኛ መንገዶቹ እንደሆኑ በስፋት ይጠቀሳል፡፡
ይህንን የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ የቀመሩት ምሁር ስሌታቸውን ለማቀናበር የተለያዩ መረጃዎችን መጠቀማቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የአገራቱ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ በቅኝ ግዛት የመያዝ ሁኔታ፣ የአገራቱ ዕድሜ፣ ከነጻነት በኋላ የኖሩበት ዓመታት፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ የእርስበርስ ግጭት፣ የነጻ ምርጫ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በየቀጣናው ያለ የመፈንቅለ መንግሥት እንቅስቃሴ፣ ወዘተ የተወሰኑት ናቸው፡፡ ይህንን አያይዘውም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ ማድረግ የግድ መፈንቅለ መንግሥት ይሆናል ማለት እንዳይደለ ነገር ግን አደጋውን ተመልክቶ አስፈላጊ እርምጃዎች በመውሰድ እንዳይሆን መከላከል ዓይነተኛ አማራጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ (ካርታዎቹ የተወሰዱት ከጄይ ዑልፌልደር ብሎግ ነው)

No comments:

Post a Comment

wanted officials