Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, January 12, 2014

ኢትዮጵያ ለምን ኋላ ቀረች? ……….……. በግርማ ሞገስ

ኢትዮጵያ ለምን ኋላ ቀረች? ……….……. ግርማ ሞገስ
ኢትዮጵያ ከውጭ ወረራ ረጅም የነፃነት ዘመን እንዳላት የአገር ተወላጅ እና የውጭ አገር የታሪክ ተመራማሪዎች
ያረጋግጣሉ። ይሁን እንጂ በስልጣኔ ግን ብዙም እንዳልገፋች ይኸው ዛሬ የእኛም ትውልድ ሳይቀር የሚያየው ሃቅ
ነው። ይኽ እንዴት ሊሆን ቻለ? ረጅሙን የነፃነት ዘመን በስልጣኔ ወደፊት ለመራመድ ለምን አልተጠቀመችበትም
ኢትዮጵያ? ምን ስትሰራ ነበር? የሚሉት የቁጭት ጥያቄዎች የሁላችንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች
ናቸው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን በራሳቸው አነሳሽነት አውሮፓውያን ጎብኚዎችን እና ሚሲዮናውያንን እየተከተሉ
ከአገራቸው ወጥተው የፖለቲካ ሳይንስ፣ የህክምና፣ የምህንድስና፣ የኢኮኖሚ፣ የመንገድ ስራ የመሳሰሉ ዘመናዊ
(Secular) ትምህርት ቀስመው አገራቸውን ለመርዳት ወደ አገራቸው የተመለሱት የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ
ምሁራን የእነ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ (1886-1919) ሁሉ የቁጭት ጥያቄ ነበር። በጣት የሚቆጠረው
የነገብረ ሕይወት ትውልድ የውጭ ትምህርት ቀስሞ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ባፄ ምኒልክ ዘመን ነበር። ይሁን
እንጂ ለዘመናዊነት በር የተከፈተው ባፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን እንደነበር፣ በኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በ1942
ዓመተ ምህረት (እ.ኤ.አ. 1950) የአዲስ አበባ የተፈጥሮና የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ መከፈቱን፣ ኮሌጁ የተደራጀው
በኢትዮጵያ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት በንቃት ይሰሩ በነበሩ ካናዳውያን እየሱሳውያን
(Jesuits) ሲሆን የተማሪዎቹ ቁጥር ከ100 በታች እንደነበር ክፍሉ ታደሰ (The Generation, p. 15-16)
ያመለክታል። እሱም ቢሆን እጅግ ዘግይቶ የመጣ በውቅያኖስ ላይ ያረፈ ትንሽ ጠብታ ያህል ነበር።

ይኽን የቁጭት ጥያቄ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያም በተለይ የቅኝ አገዛዝን አፍላ እሳት ስለተሸከሙት ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ
(1872-1889) በጻፈበት “ዐፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚለው መጽሐፉ ደጋግሞ ያነሳዋል። ባፄ ዮሐንስ
ዘመን ኢትዮጵያ እንግሊዘኛ ቋንቋ አጥርቶ የሚናገር እና በአውሮፓ እየተዘዋወረ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር
የተማረ ሰው አልነበራትም። የዘመኑን የአለም ፖለቲካ አውቆ የአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎችን ድብቅ የፖለቲካ
ፍላጎት ለነገስታቱ የሚመክር አንድም ሰው ኢትዮጵያ እንዳልነበራትም። በዚህ ምክንያት ለምሳሌ ያህል ካፄ ሠርፀ
ድንግል (1556-1590) ወዲህ ጀምሮ በቱርኮች/ግብጾች እጅ የነበረችውን የምጽዋን ባህር በር ታሪካዊ ባለቤት ወደ
ሆነችው ኢትዮጵያ ለማስመለስ የታሪካዊ እና የህጋዊ ባለቤትነት ጥያቄ ያነሱትን ዐፄ ዮሐንስ እንግሊዝ የቅርብ
ወዳጃቸው እና የቤት ውስጥ መካሪያቸው መስላ ከቀረበቻቸው በኋላ ከጀርባቸው ግን ከኢጣሊያ ጋር ተመሳጥራ
ምጽዋን ከቱርኮች/ግብጾች ወደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ወደ ኢጣሊያ እንድትሸጋገር ማድረግ የቻለችው የዘመኑን አለም
አቀፍ ፖለቲካ ከጋዜጣዎች እየተከታተለ ከአለም አቀፍ ህግ ጋር እያጣቀሰ ኢትዮጵያን የሚመክር አንድም ምሁር
ስላልነበራት እንደነበር በማስታወስ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ በቁጭት ደጋግሞ ይተርካል “ዐፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ
አንድነት” በሚለው መጽሐፍ።

በዚያን ዘመን ስለነበረው ጥቅጥቅ ኋላቀርነት እናውራ እንጂ ዛሬም ለማዕድን ምርምሩም ሆነ ለሐዲድ ቅየሳው
የውጭ ሰው እንደምንፈልግ መዘንጋት የለበንም። ዘመናዊ (Secular) ትምህርት ዘመናዊ ባህል ያስከትላል።
የህዝብን አስተሳሰብ፣ ግንኙነት እና ባህል ይቀይራል። ስለዚህ ቀደም ብሎ ዘመናዊ ባህል በኢትዮጵያ ማደግ
ባለመጀመሩ ዛሬም ከፍተኛ ትምህርት አላቸው በሚባሉት ገዢዎቻችን እና በእኛም ተማርን በምንለው
ተቃዋሚዎች ዘንድ ኋላቀርነት በህይወት እየኖረ ስለመሆኑ ጥርጥር ሊገባን አይገባም። ያ ባይሆን ኖሮ በእርስ በርስ
ጦርነት የሚካሄደውን ኋላቀር የመንግስት ሽግግር ባህላችንን ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አንስተን ሰላማዊ ትግል
ይሻላል የሚል ውይይታ ባልከፈትን ነበር። ያ ባይሆን ኖሮ አምባገነን ገዢዎቻችን ለምርጫ እና ዴሞክራሲ ባህል
ማደግ እንቅፋት ባልሆኑ ነበር። ዛሬም ኢትዮጵያ በመሐይምነት፣ በድህነት እና በኋላቀርነት እየተሰቃየች ነው።

የሆነው ሆኖ “ኢትዮጵያ ረጅም የነፃነት ዘመን ሲኖራት በስልጣኔ ያልተራመደቸው ለምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ
ይህ ጥናት አውራ (አብይ) ምክንያቶች ናቸው የሚላቸውን ያቀርባል፥ (1ኛ) ዘመናዊ ትምህርት (Secular
Education) ቀደም ብሎ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በመደረጉ እና (2ኛ) በእርስ በርስ ጦርነት የሚፈጸመው
የመንግስት ሽግግር ባህላችን ናቸው። እነዚህን ሁለት አውራ ምክንያቶች ለጥቀን በአጭር ባጭሩ እንመለከታለን።

(1ኛ) ዘመናዊ ትምህርት (Secular Education) ለረጅም ዘመን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በመደረጉ
ስመ ጥሩዋ አክሱም የኢትዮጵያ መንግስት መቀመጫ ከተማ በነበረችበት ዘመን በንግድ ላይ የበቀለ ስልጣኔ
ነበራት። የራስዋ ፊደል ነበራት። የራሱዋን ገንዘብ ከወርቅ እና ከብር አቅልጣ በመስራት በዚያን ዘመን በአለም ገበያ
ክብር አግኝታለች። በቀይ ባህር እና ህንድ ውቅያኖስ ላይ የምትነግድ ኃያል አገር ነበረች። በዚያን ዘመን በአለም
ውስጥ ከነበሩት አራት ኃያላን አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። የነ ኢዛና እና የነ ካሌብ ዘመን የአክሱም ስልጣኔ
ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዘመን እንደነበር ተጽፎ እናያለን። የነብዩ መሐመድን ስብከት ተከትሎ አዲስ ስልጣኔ ከተነሳበት ጊዜ ወዲህ ጀምሮ ስልጣኔዋ ማቆልቆል ይጀምራል። ተከትሎም በመንግስት ሽግግር እርስ በርስ ጦርነት
ውስጥ ለረጅም አመቶች ትዘፈቃለች። እስከ ንግስት ዮዲት ዘመነ መንግስት ፍጻሜ ድረስ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ
ጦርነት ውስጥ እንደነበረች ከእስክንድሪያ ግብጽ ይመጡ የነበሩት አቡኖች ታሪክ ይጠቁማል። ጦርነቱ ያበቃው
መራ ተክለ ሃይማኖት በጦርነቱ ቀንቶት የኢትዮጵያን የመንግስት መቀመጫ ከአክሱም ነቅሎ ደጋፊዎቹ ወደ
ተበራከቱበት ላስታ ከተማ ሲተክል ነበር። ይኽ የዛጉዌ ስረወ መንግስት ጅማሬ ነበር።
የሆነው ሆኖ አክሱም ገናና ሳለች ክርስቶስ ከተወለደ 200 አመቶች ግድም ወዲህ በአክሱም የነበሩት የኢትዮጵያ
መሪዎች ስለ አዲሱ ክርስትና ሃይማኖት ከክርስቲያን ነጋዴዎች፣ ከውሮፓውያን ጎብኚዎች እና ከመንገደኞች ወሬው
ነበራቸው። ሃይማኖቱ ኢትዮጵያ ሊደርስ የቻለው ፍሬምናጦስ እና አዲየስ በተባሉ ሁለት የአረብ ተወላጆች
(ምናልባት ሶሪያ) ነበር ተብሎ ይታመናል። በ320 ዓ.ም. ግድም ኢዛና ያባቱን ዙፋን ሲወርስ ፍሬምናጦስ ወደ
እስክንድሪያ ግብጽ ተጉዞ በእስክንድሪያ ግብጽ የተቀመጡትን የአካባቢው የበላይ መንፈሳዊ አባት`(ፓትሪያክ)
በኢትዮጵያ አዲሱን ሃይማኖት (ክርስትናን) በበላይነት የሚመራ መንፈሳዊ አባት (አቡን) ወደ ኢትዮጵያ እንዲልኩ
እንደጠየቀ እና ፓትሪያኩ ፍሬምናጦስን የኢትዮጵያ የመጀመሪያው አቡን አድርገው እንደሾሙት ሃሮልድ
ማርኩይስ ይተርካል። አቡን ፍሬምናጦስ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ ኢዛናን የኢትዮጵያ የመጀመሪያው
ክርስቲያን ንጉስ አደረገ። የዐፄ ኢዛና ክርስቲያን መሆን በአገሪቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፈተ። የክርስትና ሃይማኖት
በኢትዮጵያ ፈጥኖ በመሰራጨት ለአብዛኛው ደጋማ ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ህዝብ የማንነት መገለጫ ሆነ። በ4ኛው
መቶ አመት ውስጥ መነኩሴዎች የወንጌልን ቃል ሊያስተምሩ በኢትዮጵያ ተሰማሩ። በዚያው ዘመን በአክሱም
ጽዮን ማሪያም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ማዕከል ሆነች። ከአዲግራት በስተ መዕራብ ተራራማ አምባ ላይ የሚገኘው
ደብረ ዳሞ ገዳም በ5ኛው መቶ አመት ውስጥ ተመሰረተ።
አቡን ፍሬምናጦስ ሲሞት እስክንድሪያ ግብጽ አዲስ አቡን ላከች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ኃይለ ስላሴ ዘመነ
መንግስት ፍጻሜ ድረስ ለ1600 አመቶች ያህል ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት የሚመራው ከእስክንድሪያ
ግብጽ በሚላኩ አረብ አቡኖች ነበር። በኢትዮጵያ በዘመናዊ መልክ የተደራጀው ዳግማዊ ምንሊክ አንደኛ ደረጃ
ትምህርት ቤት የተከፈተው በ1900 ዓ.ም. እንደሆነ እና እሱም እንዲመራ የተደረገው ከእስክንድሪያ ግብጽ
በሚመጡት በእነዚሁ አረብ አቡኖች እንደነበር ባህሩ ዘውዴ ይተርካል። ና በሚከተሉዋቸው ቄሶች ስለነበር
በኢትዮጵያ የመፈጠሩት ምሁራን በሙሉ መንፈሳውያን ነበሩ። የኢትዮጵያ ነገስታትም በልጅነታቸው የሚማሩት
ይኼንኑ መንፈሳዊ ትምህርት ብቻ ነበር። በኢትዮጵያ የሚሰጠውም ትምህርት በእስክንድሪያ ግብጽ በአረበኛ
ተጽፎ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ብሉይ ኪዳንን፣ አዲስ ኪዳንን፣ መጽሐፈ ሊቃውንትን ምነናን፣ ምንኩስናንና
ብህትናን የሚያወድስ እንዲሁም የጻድቃን፣ የሰማዕታትና የመልአክት ገድል (ስራዎች) እና ድርሳን (ታሪክ) ያካትት
እንደነበር “የግራኝ ወረራ” በሚለው መጽሐፉ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ዘርዘር አድርጎ ያመለክታል። ከዚያ ይህ
ትምህርት ከአረብኛ ቋንቋ ወደ ግዕዝ እየተተረጎመ በየገዳሙ እና ደብሩ እየተሰራጨ ወጣቱ (ወደፊት ንጉስ
የሚሆኑትን ጨምሮ) እንዲማሩት ይደረጋል። ስለዚህ በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ የምታመርታቸው ምሁራን የውጭ
አገር ቋንቋ ችሎታም አረበኛ ብቻ ነበር።
የክርስትና እምነት በአክሱም ኢትዮጵያ ካለምንም እክል ቢሰራጭም በውጭው የክርስቲያን አለም ውስጥ ግን
የእየሱስ ክርስቶስን ባህሪ በሚመለከት የእምነት ልዩነት ተፈጥሮ ውስጥ ውስጡን ያነጋግር ነበር። አብዛኛው
የምዕራብ አውሮፓ (ስፔይን፣ ፖርቱጋል፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ወ.ዘ.ተ.) ክርስትና እምነት መንፈሳዊ
አባቶች እየሱስ ክርስቶስ በአንድ በኩል ከአምላክ በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ከሆነችው ከማሪያም በመወለዱ
“ሁለት-ባህሪ” አለው የሚል እምነት ሲይዙ በተለይ የኦርቶዶክስ እምነት ፈጣሪዋ የእስክንድሪያ ግብጽ እና
እየሩሳሌም መንፈሳዊ አባቶች ግን ሁለቱ ባህሪዎች ተዋህደው “አንድ-ባህሪ” ሆነዋል የሚል አቋም ነበራቸው።
በተፈጠረው የእምነት ልዩነት ላይ ለመወያየት ከተደረጉት ጉባኤዎች ውስጥ በ451 ዓ.ም. በጥንታዊቷ ኬልቄዶን
(Chalcedon) ከተማ (ዛሬ የኢስታንቡል/ቱርክ አካል ነች) በተደረገው ጉባኤ የክርስቲያኑ አለም በጸብ ከሁለት
ተከፍሎ እንደተለያየ ተክለ ፃዲቅ መኩርያ “የግራኝ ወረራ” በሚለው መጽሐፉ በሰፊው ይተርካል። ከዚህ ጉባኤ
ወዲህ ሁለቱ ወገኖች በጸበኛነት ስሜት መተያየት ይጀምራሉ። በመካከላቸው አለመተማመን እና መናናቅ ተተከለ።
ጠቃሚ የቴክኒክ፣ የህክምና፣ የምህንድስና እውቀት ከሁለት-መንፈሶች (ምዕራብ አውሮፓ አገሮች) ሲመጣም
አንድ-መንፈሶች የከሃዲዎች ንብረት አድርገው በመቁጠር ያናንቁ ጀመር፡፡ ኢትዮጵያ ተወካይ የመላክ መብት
ስላልነበራት የእስክንድሪያ ግብጽ አቡኖችን የነገሯትን ነበር የተከተለችው።
ያም ሆነ ይኽ ጥያቄው መነሳቱ እና ውይይት መደረጉ የስልጣኔ ምልክት ነው። አንድ-መንፈስ ወይንም ሁለት-
መንፈስ የሚለውን እምነት መከተልም ችግር አይደለም። ችግሩ የእስክንድሪያ ግብጽ አቡኖች በድፍን ጥላቻ
መዋጣቸው ነበር። ኢትዮጵያን በጥላቻ መርዝ መበከላቸው እና ከምዕራብ አውሮፓ የሚመጣን ማንኛውን ዘመናዊ ስልጣኔ የእየሱስ ክርስቶስ ከሃዲዎች ንብረት አድርጋ በመቁጠር የስልጣኔው ተጠቃሚ እንዳትሆን ማድረጋቸው
ትልቅ ስህተት ነበር። የኢትዮጵያም ጭፍን ተከታይነት ስህተት ነበር። የቀድሞ አባቶቻችን በመንፈሳዊ እና
በምድራዊ (Secular) ስልጣኔ መካከል ያለውን ልዩነት ለይተው አለማየታቸው ስህተት ነበር። ጥላቻ ያሳውራል
የሚለው አባባል ሃቅ እንደሆነ እናያለን። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለዘመናዊ ትምህርት (Secular Education)
ማለትም ለስልጣኔ እና ለዘመናዊነት በሯን ዘጋች።
እንደሚታወቀው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ8ኛው መዕተ ዓለም ጀምሮ እስከ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ 6ኛው
ምዕተ ዓመት ድረስ ለ1300 አመቶች ያህል በሜድትራኒያን ባህር አካባቢ የጥንታዊ ግሪክና ሮማ (Greco-Roman
World) ስልጣኔ አብቦ ነበር። የጥንታዊ ግሪክና ሮማ ፈላስፋዎችና ምሁራን በሳይንስ፣ በሂሳብ፣ በምህንድስና፣
በህክምና፣ በአስተዳደር፣ በፖለቲካ ሳይንስ፣ በስዕልና በቅርጽ ስነ-ጥበብ፣ በባሩድ የሚተኮስ መሳሪያ በመስራት፣
በህንጻና በመንገድ ስራ መስኮች ብዙ ጽፈው ትተውት ሄደዋል። በዚኽ ዘመነ ከነበሩት ሰዎች ውስጥ አርስቶትል
(348-322 ዓ.ዓ.)፣ ሶቅራጥስ (469-399 ዓ.ዓ.)፣ ፕሌቶ (427-347 ዓ.ዓ.)፣ ፓይታጎርስ (570-495 ዓ.ዓ.) ጥቂቶቹ
እንደሆኑ በስልጠና ክፍል አንድ ጠቅሰናል። (ፓይታጎርስ - Pythagoras Theorem ታስታውሳላችሁ? )
ከ11ኛው መቶ ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በኬልቄዶን ጉባኤ ሁለት-መንፈስ የሚል አቅዋም በወሰዱት አገሮች (ስፔይን፣
ፖርቱጋል፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ወ.ዘ.ተ.) ዋና ከተማዎች ጥንታዊ የግሪክና የሮማ ፈላስፋዎችና ምሁራን
በእጅ ጽፈው በየቦታው ትተውት የሄዱት የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የምህንድስና፣ የንግድ፣ የስነጥበብ፣ የመንገድ ስራ፣
የህክምና፣ የአስተዳደር፣ የፖለቲካ ሳይንስ እና የመሳሰለው እውቀት ዳግማዊ ትንሳኤውን (Renaissance) አገኘ።
ይህ እውቀት ከተቀበረበት እየተፈለገ በተለያዩ ቋንቋዎች እየተተረጎመ ተባዝቶ በአውሮፓ ተሰራጨ። አውሮፓ
እነዚህን እውቀቶች ከ11ኛው እስከ 16ኛው መቶ አመት ሳታቋረጥ በህዝቧ ውስጥ በማሰራጨቷ ትልቅ የባህል
ለውጥ አደረገች። ስለዚህ ምዕራብ አውሮፓ በእንዱስትሪ፣ በቴክኒክ፣ በንግድና በእርሻ፣ በምህንድስና፣ በህክምና፣
በቤትና በመርከብ ግንባታ፣ በአስተዳደር፣ በድንጋይ ቀረፃ፣ በብረታ ብረት፣ በባሩድ ስራና በባሩድ የሚተኮሱ
መድፍና ነፍጥ ስራዎች ወደፊት ተራመደች። መርከቦችና ዘመናዊ መሳሪያ በብዛት ማምረት ጀመረች። በኢንግሊዝ
አገር የተካሄደው የኢንዱስትሪ አብዮትም ይህን የባል ለውጥ ተከትሎ የመጣ ነበር።
ከ11ኛው እስከ 13ኛው ምዕተ ዓመት በምዕራብ አውሮፓ ዳግማዊ ትንሳኤውን (Renaissance) ያገኘው ዘመናዊ
እውቀት በየአገሩ ከተሰራጨ በኋላ የህዝቡን አስተሳሰብና ባህል መለወጥ የተቻለው ትምህርት ቤቶች በተለይም
ኮሌጆችና ዩንቨርስቲዎች ተከፍተው የህብረተሰቡን ወጣት በማስተማር ነበር። በምዕራብ አውሮፓ፣ በአረብ
ሙስሊም አገሮች እና በኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች የተከፈቱበት ጊዚያት በንፅፅር እንመልከት፥

http://www.goolgule.com/why-ethiopia-is-backward/?utm_medium=fbshare.me-facebook-post&awesm=fbshare.me_r8Pg&utm_content=fbshare-js-large&utm_source=direct-fbshare.me&utm_campaign=

No comments:

Post a Comment

wanted officials