Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, January 12, 2014

መንግሥት በቅርቡ በሩን ለዓለም ንግድ ድርጅት ክፍት እንደማያደርግ አስታወቀ


ብሔራዊ የመረጃ ማዕከል ተመሠረተ
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በሚደረገው የድርድር ሒደት፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ታጠናቅቃለች ተብሎ ቢጠበቅም፣ በመንግሥት ስትራቴጂካዊ የተባሉ ዘርፎች በቅርቡ ክፍት እንደማይደረጉ ይፋ ተደረገ፡፡ 
የቴሌኮም፣ የፋይናንስ፣ የኢነርጂና ሌሎች ለመንግሥት ወሳኝ መሆናቸው ታምኖበት በሥሩ የሚያስተዳድራቸውን ዘርፎች ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት ክፍት እንደማያደርግ ይፋ ያደረጉት፣ በንግድ ሚኒስቴር የንግድ ድርድርና ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ገረመው አያሌው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የምትገኘው በዓለም ልትገበያይ የምትችልባቸው የወጪና ገቢ ዕቃዎችና የአገልግሎቶች ታሪፍ ዋጋ ድርድር ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 
አገሪቱ እስካሁን በአገልግሎት ዘርፎች ላይ ውይይት ባትጀምርም፣ ከተደራዳሪ አገሮች በኩል የሚቀርቡላት የአገልግሎት ዘርፎች ለውድድር ክፍት የማድረግ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደማታስተናግድ ተገልጿል፡፡ የድርድር ሒደቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልቃል ተብሎ መገመት እንደማይቻልም አዝማሚያዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ 
አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ታሪፍ ላይ ድርድር እያደረገች ሲሆን፣ ይህም አሁን ካለው ታሪፍ ወደታች መቀነስ ሳይሆን ባለው የ35 በመቶ ታሪፍ ወደፊት ድርድሩ ቢጠናቀቅ፣ ወደፊት በዕጥፍ ወይም ከዚያም ባነሰ መጠን ሊጨምር በሚችልበት መጠን ላይ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከአውሮፓና በቅርቡም ከደቡብ ኮሪያ ጋር በመደራደር ላይ ትገኛለች፡፡ 
እነዚህ አገሮች ለኢትዮጵያ ጥያቄ እያቀረቡ አራተኛው ዙር ድርድር ላይ መድረሳቸውንም አቶ ገረመው ጠቁመዋል፡፡ በአራተኛው ዙር 168 ጥያቄዎች ቀርበው ምላሾቻቸው መጠናቀቁንም አስታውቀዋል፡፡ የጥያቄዎቹ መነሻ ኢትዮጵያ ያቀረበቻቸው ሰነዶች ሲሆኑ፣ በርካታ በመሆናቸው ደግሞ ጠያቂዎቹ አገሮች በቀረቡላቸው ምላሾች አለመርካታቸውን፣ ወይም ደግሞ ግልጽ ያልሆኑላቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ለማወቅ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ 
በተያያዘ ዜና ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትም ሆነ ለአገር ውስጥ ወይም ለውጭ ተቋማትና ግለሰቦች በቀላሉ የንግድና ኢኮኖሚ ነክ መረጃዎችን በአንድ ማዕከል ለማቅረብ የሚያስችል ብሔራዊ የመረጃ ማዕከል ማቋቋሙን፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል፡፡ ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያሟላ ጥያቄ የቀረበለት በመሆኑ፣ የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር ሒደት በሚጠይቀው መሥፈርት መሠረት መቋቋሙን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡  
 Source : Ethiopian?reporter

No comments:

Post a Comment

wanted officials