Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, January 28, 2014

የወያኔ የውሸት ዘገባዎች ሲጋለጡ -የ“ኦክስፋም” ጥናት ውጤት ኢትዮጵያ በምግብ የመጨረሻዋ አገር ናት ይላል

የወያኔ የውሸት ዘገባዎች ሲጋለጡ


“ኦክስፋም” በመልካም ሥራቸው ከታወቁ ትላልቅ ዓለም ዓቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነው። በቅርቡ አንድ መቶ ሀያ አምስት አገሮችን ያካተተ ከምግብ አቅርቦትና አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል። ጥናቱ አራት ዝርዝርና አንድ አጠቃላይ አመላካቾች አሉት።
1. አመላካች አንድ: የምግብ እጥረት
ይህ አመላካች “በየአገሮቹ ምን ያህል ለበላተኛው የሚበቃ ምግብ አለ?” የሚለውን ይለካል። በጥናቱ ውጤት መሠረት በምግብ እጥረት እጅግ የተጎዱ የመጨረሻዎቹ አስር አገሮች የሚከተሉት ናቸው: – ቡሩንዲ፣ የመን፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ ናይጄሪያ፣ ላኦስ፣ ባንግላዴሽ፣ መካከለኛዉ አፍሪካ ሪፑብሊክ እና ህንድ። ኢትዮጵያ አገራችን ከመጨረሻ አራተኛ ናት።
2. አመላካች ሁለት: ለምግብ የመክፈል አቅም (Affordability)
ይህ አመላካች “የአገሩ ሕዝብ በአገሩ ዋጋ ምግብ ገዝቶ ለመብላት ምን ያህል አቅሙ ይፈቅድለታል?” የሚለውን የሚመልስ ነው። አሁንም ከመጨረሻ እንጀምር። አንጎላ፣ ዚምባቡዌ፣ ቻድ፣ ጉያና፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ጋምቢያ እና ኢራን የየአገሩ ሕዝብ ምግብ መሸመት የሚቸገሩባቸው አገሮች ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ ከመጨረሻ አምስተኛ ናት።
3. አመላካች ሶስት: የምግብ ጥራት
ይህ የምግብ ይዘትንና የአያያዝ ንጽህናን የሚመለከት ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ሞዛምቢክ፣ ቻድ፣ ቶጎ፣ ዛምቢያ፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ፣ ባንግላዴሽ፣ ሌሶቶ ከመጨረሻው እስከ አስረኛ ደረጃ ይዘዋል። ኢትዮጵያ በምግብ ጥራት የመጨረሻዋ አገር ናት።
4. አመላካች አራት፡ የሰውነት ውፍረት እና የስኳር በሽታ
ይህ አመላካች ከልክ ያለፈ ውፍረት ዓለም ዓቀፍ የጤና ችግር እየሆነ በመምጣቱ የገባ አመልካች ነው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥሩ ውጤት ያመጣችሁ በዚህ አመላካች ብቻ ነው። ኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝቧ ቀጫጫ ነው፤ የስኳር በሽታም እንደሌላው አገር የተስፋፋባት አገር አይደለችም።
5. አማካይ ውጤት
የእነዚህ አራት አመላካቾች ድምር ውጤት አጠቃላይ ውጤትን ይሰጣል። በአጠቃላይ ውጤት: ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ አንጎላ፣ ማዳካስካር፣ የመን፣ ቡሩንዲ ናይጄሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዚምባቡዌ፣ ሴራሊዮን ከመጨረሻ እስከ አስረኛ ወጥተዋል። ኢትዮጵያ ከመጨረሻ ሁለተኛ ነች።
ይህ ምንን ያመለክታል?
ወያኔ ባለፉት አስር ዓመታት በተከታታይ ከ11% በላይ ኢኮኖሚውን አሳድጌዋለሁ ሲለን ነበር። እድገቱ ያተኮረው ገጠር፤ ምንጩም ግብርና ነው ብሎን ነበር። ሐቁ ግን ከላይ የተመለከተው ነው።
እርግጥ ነው የወያኔ ሹማምንት በከተሞች ሕንፃዎችን ይገነባሉ፤ በገጠሮች በመቶዎች ሄክታር የሚለካ ለም መሬት ይዘው ፈጣን ገንዘብ በሚያስገኙ የአበባ፣ የጫትና የቃጫ ምርት ላይ ተሰማርተዋል። ከራሳቸውም አልፈው ሀብታም የውጭ አገራት ሸሪኮቻቸውን በአገራችን ለም መሬት ይበልጥ ያበለፅጓቸዋል። የእነሱ የግላቸው፣ የቤተሰቦቻቸው፣ የዘመዶቻቸው እና የሸሪኮቻቸው ኢኮኖሚ እየተመነደገ መሆኑን እናውቃለን። ይህን በገዛ ዓይኖቻችን የምናየው ሀቅ ነው።
ሆኖም ግን የእነሱ ኢኮኖሚ ማደግ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማደግ አለመሆኑ እናውቃለን። አገራችን ከጓረቤት አገሮች ጋር ስትነፃፀር ወደ ኋላ እየቀረች መሆኑ ያንገበግበናል። በቅርቡ አክስፋም በጥናት ያረጋገጠዉ የኢትዮጵያ ገበሬዎች በየቤታቸው ከወዳጆቻቸው ጋር በምስጢር የሚያወሩትን እውነት ነው።
ከሳምንት በፊት ደግሞ “ኢኮኖሚክ ኢንተለጀንስ ዩኒት” የተሰኘው ታዋቂ የምርምር ተቋም አንድ የጥናት ውጤት ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህ የጥናት ውጤት መሠረት በዓለም በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ያሉ አስር አገሮች በቅደም ተከተል ሞንጎሊያ፣ ሴራሊዮን፣ ቱርክሜንስታን፣ ቡታን፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ላኦስ፣ ቲሞር-ሊስቲ፣ ኤርትራ እና ዛምቢያ ናቸው። በዝርዝሩ ውስጥ ኢትዮጵያ አገራችን የለችበትም።
በዓለም አቀፍ መድረኮችም የወያኔ መረጃዎች ውሸትነት እየተጋለጡ መሆናቸው በጎ ምልክት ነው። የሚያሳዝነው ግን ይህንን ሀቅ የሚያዉቁ ምዕራባዉያን ለጋሽ አገሮች አሁንም ወያኔን እየረዱና እየደገፉ ሥቃያችን የሚያራዝሙብን መሆኑ ነው።
ለዚህም ነው ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዘላቂ መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው በአገራችን መሠረዊ የሆነ የአስተዳደር ለውጥ ሲኖር ነው ብሎ የሚያምነው። የወያኔ አገዛዝ በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እስካልተተካ ድረስ የኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ መደህየቱ፤ ጥቂት ሀብታሞች ደግሞ በብዙሀኑ ድህነት መበልፀጋቸው አይቀርም። የወያኔ ውሸቶች ለኢትዮጵያ ድሀ ምግብና መጠለያ አይሆኑለትም። ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ማምጣት የምንችለው ወያኔን አስወግደን በምትኩ ለሕዝብ ሁለተናዊ እድገት የሚጨነቅ መንግሥት መምረጥ ስንችል ብቻ ነው።
ስለሆነም ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በውሸት እድገት እያደናቆረን፤ በተግባር ግን እያደኸየን ያለውን ዘራፊውን ወያኔን አስወግደን በሕዝብ ነፃ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት እንዲኖረን ትግላችን እናጠንክር ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment

wanted officials