አንዱዋለም ግንቦት ሰባት ከተባለ እኔም ግንቦት ሰባት ነኝ – ግርማ ካሳ
«በሕገ መንግስቱ የመደራጀት መብታቸው የተጠበቀላቸው ፓርቲዎችን አልከሰስንም።ፓርቲዎችን ግን ሽፋን አድርገዉ ስርዓቱን ወይንም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ እንቀሳቀሳለን የሚሉ ኃይሎችን ግን ዛሬም ፣ ነገም ፣ ሕጉን የማስከበር ግዴታና ሃላፊነት ስላለብን ከመከሰስ አያመልጡም ማለት ነዉ።»
ኢቲቪ በቅርቡ በ«ሽብርተኝነት» ላይ፣ በቅርቡ ባቀረበዉ አሳዛኝ ዶኩሜንተሪ ላይ ፣ የፌደራል መንግስት አቃቤ ሕግ፣ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ የተናገሩት ነበር።
ኢቲቪ በቅርቡ በ«ሽብርተኝነት» ላይ፣ በቅርቡ ባቀረበዉ አሳዛኝ ዶኩሜንተሪ ላይ ፣ የፌደራል መንግስት አቃቤ ሕግ፣ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ የተናገሩት ነበር።
እኝህ የሕግ ባለሞያ እየደጋገሙ ሕግን ስለማክበርና ስለ ሕገ መንግስቱ ነግረዉናል። ስለሕገ መንግስት ካነሳን አይቀር አንድ ነገር ጣል ላድርግ። የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 29 ንኡስ አንቀጽ 4 «በመንግስት ገንዘብ የሚካሄድ ወይንም በመንግስት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል» የሚል ድንጋጌ ያካትታል። ኢቲቪ በሕዝብ ገንዘብ የሚተዳደር እንደመሆኑ ይህ የሕገ መንግስት አንቀጽ ይመለከተዋል። ነገር ግን ኢቲቪ በቀጥታ፣ ሕግ መንግስቱን ሲንድ፣ ገለልተኛነት በጎደለው መልኩ የአንድ ድርጅትን የፖለቲክ ፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ ሲሆን ነው እያየን ያለነዉ። እነ አንዱዋለም አራጌ ላይ፣ ኢቲቪ የአንድ ወገንን አቋም የያዘ፣ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲያዥጎደጉድ፣ ቢያንስ ቢያንስ ጥቂት ሰኮንዶች፣ የአንዷለምን ጠበቃዎች፣ ወይንም ቤተሰብ፣ አሊያም የትግል አጋሮቹ የሆኑት የአንድነት አመራር አባላትን ለማነጋገር አልተሞከረም። እንግዲህ ከዚህ የምንረዳዉ፣ ሕግን በማክበር አኳያ፣ ሕወሃት/ኢሕአዴጎችና ኢቲቪ፣ አንድ ጣታቸዉን ወደሌሎች ሲጠቁሙ፣ አራቱ ጣቶቻቸው ወደ እነርሱ መዞራቸውን፣ ሕገ መንግስቱን እየጣሱ ያሉ እነርሱ መሆናቸውን ነዉ።
«አንዱዋለም አራጌን በተመለከተ፣ የግንቦት ሰባትን ተእልኮ ለማስፈጸም አገር ዉስጥ በሕቡእ (ስዉር) ይንቀሳቀሳል በሰላማዊ ትግል እንታገላለን የሚሉ የፓርቲዎችን ሽፋን አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረ በመሆኑ በቂ ማስረጃ አቅርበናል» ሲሉ ነበር የፌደራል አቃቤ ሕጉ ለኢቲቪ አክለው የገለጹት። ምን አይነት መረጃ እንዳቀረቡ ግን አልነገሩንም። ለምን ቢባል ምንም ስለሌለ።
አንዱዋለም ያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሲያደርግ የነበረው በግልጽና በገሃድ ነዉ። ለተለያዩ ፓልቶክ ክፍሎች፣ አገር ዉስጥና በዉጭ ለሚገኙ ሜዲያዎች በርካታ ቃለ መጠይቆችን ሰጥቷል። በአገር ቤት፣ በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ ሆነ በተለያዩ ቦታዎች በተደረጉ ዉይይቶችና ስብሰባዎች ያቀረባቸው ንግግሮች በሙሉ የተደበቁ አይደሉም። ዉጭ ካሉ ኢትዮጵያዊያን ጋር (አንዱም እኔው ነበርኩ) ፣ ብዙ ጊዜ በስልክ ሃሳቦችን ተለዋዉጧል። በስልክ ያደረጋቸው ንግግሮችም፣ 24 ሰዓት የሰላማዊ ተቃዋሚ መሪዎችን ስልክ በሚጠልፈው ቴሌ ዘንድ የተሰሙ ናቸው። ቤቱና ቢሮዉ ከላይ እስከ ታች ተበርብረዉ ፣ የሚስጥራዊ የኮሚኒኬሽን መሳሪያዎች፣ ቦምቦች፣ ፈንጂዎች፣ ሚስጥራዊ ሰነዶች አልተገኙም። ኤሜሎቹ በሙሉ ተነበዋል። አንዱዋለምን ከግንቦት ሰባት ጋር የሚያገናኝ፣ በሕቡእ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ የሚያመለክት አንዳች መረጃ አቃቤ ሕግ አላቀረበም። መረጃዎች ቢኖሩ ኖሮ፣ «እንኳን ዘንቦብሽ ድሮም ጤዛ ነሽ» እንደተባለ፣ ዜጎችን በማዋረድና በማሳነስ የሚታወቀዉ ኢቲቪ፣ ይሄን ጊዜ በስፋት ያወራልን ነበር።
ኢቲቪ ግን አንዱዋለምን ለመክሰስ ያቀረበው፣ አንድ የአንድነት አባል የነበሩ፣ ተስፋሁን አናጋዉ የተባሉ ሰው የተናገሩትን ነዉ። አንዱዋለም ከታሰረ በኋላ አቃቤ ሕጎች መረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው፣ የዉሸት መረጃዎች ማሰባሰቡ የግድ ሆነባቸው። የታሰሩ ሌሎች የአንድነት አባላትን ማግባባት ጀመሩ። «በአንዱዋለም ላይ እኛ ተናገሩ የምንላችሁን ከተናጋራችሁ እንፈታቹሃለን» ብለው እጆቻቸዉን ጠመዘዙ። ብዙዎች በአንዱዋለም ላይ የዉሸት መረጃ ማቅረቡ ሕሊናቸውን ስለከበደው ፍቃደኛ አልሆኑም። ነገር ግን እንደ ተስፋሁን አናጋው፣ የሚባሉ ደካማ ሰዎች ተገኙና የዉሸት ምስክርነት ቀረበ። እንግዲህ በአገዛዙ ካድሬዎች ተቀናብረው ከቀረቡ የዉሽት ምስክርነቶች ዉጭ፣ ቅንጣት የምታክል፣ አንዱዋለምን ሽብርተኛ ወይንም ከግንቦት ስባት ጋር የሚሰራ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ አልቀረበም።
«ግንቦት ሰባት ፣ ግንቦት ሰባት ……» እንባላለን። ከጅምሩ በግንቦት ሰባት ላይ ጠንካራ ተቃዉሞ ያለኝ ሰው ነኝ። የግንቦት ሰባት ፖለቲካ አይመቸኝም፣ ለአገርም ይጠቅማል ብዬ አላስብም። ግንቦት ሰባቶች ከያዙት የተሳሳተ መንገድ እንዲመለሱ፣ በሻእቢያ ድጋፍ ሳይሆን፣ በሕዝብ ጉልበት በመተማመን ወደ ሰላሙ መንገድ እንዲመጡ መክሪያለሁ። በተለያዩ ጊዜያት ለአንባቢያን ያቀረብኳቸውን ጽሆፍችን መመልከት ይቻላል።
ከቅንጅት ጊዜ ጀምሮ በአገር ዉስጥ በሰላም ለዉጥ ለማምጣት የሚሰሩ ድርጅቶችን ደግፊያለሁ። በተለይም የአንድነት ፓርቲ በጣም የሚመቸኝ ፓርቲ እንደመሆኑ፣ አንዱዋለም አራጌን ጨምሮ፣ ከፓርቲዉ አመራር አባላት ጋር ሃሳብ የተለዋወጥኩባቸው በርካታ ጊዜያት ነበሩ። አንዱዋለም አራጌ፣ እግዚአብሄርን የሚፈራ፣ የልጆች አባት፣ የሰላማዊ ትግል አርበኛ ነዉ። አንዱዋለም ስለ ትጥቅ ትግል ያለዉን አመለካከት አውቃለሁ። በየትኛዉም መድረክና ፍርድ ቤት፣ መጽህፍ ቅዱስ ላይ እጄን ጭኜ የምመሰክረዉ ነዉ። አንዱዋለም አራጌ የግንቦት ስባት አባል ወይንም ሽብርተኛ ነው የሚለውን፣ በምን መስፈርትና መልኩ ልቀበለው አልችልም። በርግጥ አንዱዋለም የግንቦት ሰባት አባል ከተባለ፣ እኔም የግንቦት ሰባት አባል ነኝ እንደ ማለት ነዉ።
በጣም ያሳዝናል። እንደ አንዱዋለም አራጌ አይነት አገር ወዳድ ዜጎች፣ አገራቸዉን በመዉደዳቸው፣ የሕዝብ መብት ይከበር በማለታቸው፣ «ሽብርተኞች» በሚል አሳዛኝ ክስ ሲታሰሩ ማየት፣ አገራችን ኢትዮጵያ ዜጎች ቀና ብለው የሚራመዱባት ሳይሆን ፣ አሳፋሪ ድራማ የሚካሄድባት፣ ሕግ መቀለጃ የሆነባት አገር መሆኗ፣ በርግጥ ልብን የሚያደማ ነው።
እንግዲህ፣ ሁሌ እንደማደርገዉ፣ ጥሪ ለኢሕአዴጎች አስተላልፋለሁ። ኢሕአዴግ ዉስጥ፣ ለአገርና ለሕዝብ የሚያስቡ ካሉ፣ በድርጅታቸው ዉስጥ እየተደረገ ያለውን አፈናና ግፍ በቃ የማለት አቅምና ጉልበት ሊኖራቸው ይገባል ባይ ነኝ። ድርጅታቸው ዉስጥ ያሉ ጥቂቶች ድርጅታቸውን ይዘው ገደል እንዲወስዱ ሊፈቀድላቸው አይገባም። እነ አንዱዋለምን በማሰር ኢሕአዴግ ምንም የሚጠቀመው ነገር የለም። እነ አንዱዋለምን በዉሸት ክስ ከሶ፣ በቴለቭዥኝ ደግሞ ስማቸውን ማጉደፍ፣ ነዉር ነዉ። ኢሕአዴግ የበለጠ እንዲጠላ የሚያደርግ ነዉ። የአረና ትግራይ አመራር አባል አብርሃ ደስታ አንዴ ሲጽፍ፣ የሕወሃት እምብርት በነበረችው የትግራይ ክልል፣ አንዱዋለም አራጌ በጣም ተወዳጅ ፖለቲከኛ እንደሆነ ገልጾ ነበር። አንዱዋለም አራጌ፣ በክልሎች ሁሉ ሕዝብ የሚያውቀዉ ጀግና መሪ ነዉ። በርሱ ላይ እየተደረገ ያለው ዘመቻ፣ የበለጠ አንዱዋለምን ከፍ የሚያደርግ፣ ኢሕአዴግን ደግሞ የሚያሳንስ ነዉ። አንዱዋለምን እና ሌሎች የሕሊና እስረኞች፣ አለመፍታት በቀጥታ ከሕዝቡ ጋር እንደመላተም ነው። አይጠቅምም። ጉዳት አለው።
ለኢሕአዴጎች ጥሪ ባቀርብም፣ የነአንዱዋለም ጉዳይ፣ የኢሕአዴጎች ጉዳይ ብቻ ግን አደለም። ኢሕአዴጎች ወደ ሕሊናቸው ተመልሰው መልካም ነገር ያደርጉ ዘንድ እነርሱን ማነጋገርና ለማሳመን መሞከር፣ ማበረታታት ተገቢ ነዉ የሚል እምነት ቢኖረኝም፣ ሁሉንም ነገር ከነርሱ ጠብቆ ቁጭ ማለቱ ግን፣ እጅግ በጣም ትልቅ ስህተት ነው። እነርሱ ቢሰሙ መልካም ነዉ፤ ካልሆነ ግን እያንዳንዳችን መብታችንን የማስከበር ሃላፊነት ያለብን ይመስለኛል። ዛሬ እነ አንዱዋለም ናቸው። ነገ እያንዳንዳችን ቤት ይንኳኳል ። ዛሬ ሊመቸን ይችላል። ነገር ግን ለሕይወታችን ምንም ዋስትና አይኖረንም። አንድ የመንግስት ባለስልጣን ፊታችንን አይቶ ከጠላን፣ በቀላሉ ወደ ወህኒ ሊወረወረን የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ማወቅ አለብን። አለን የምንለውን ቢዝነስ አንዱ ከፈለገዉ፣ «ያለ የሌለዉን እያመጡ፣ ይሄን ያህል ግብር ክፈል» ተብለን ከጨዋታ ዉጭ በቀላሉ ልንሆን የምንችልበት አገር ነዉ ያለችን። አቤት የምንልበት የሕግ ስርዓት የለም። አብዛኞቹ ዳኞች በመመሪያ የሚፈርዱ ካድሬዎች ናቸው። በመሆኑም፣ ኢትዮጵያ፣ ሕግ የበላይ የሆነባት፣ ለሁሉ ዜጎቸ እኩል የሆነች፣ ኢትዮጵያዊያን ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ የሚችሉባት፣ መቀባባል፣ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ ሰላም ፣ ፍትህና ወንድማማችነት የሰፈነባት፣ የበለጸገች አገር እንድትሆን፣ እያንዳንዳችን የድርሻችንን መወጣት አለብን። ዳር ሆኖ ተቀመጦ ማውራት ይብቃ። ሌሎች ለምን እንዲህ አላደረጉም ብሎ መክሰስ ይብቃ። ሌሎች ሞተው በነርሱ አስክሬን ላይ ተረማመደን ለመሻሻል መሞከር ይብቃ። አገራችን የእስክንደር፣ ወይንም የአንዱዋለም፣ ወይንም የበቀለ ገርባ፣ ወይንም የርዮት አለሙ ብቻ ሳትሆን የሁላችንም ናት፣ ሁላችንም ተስፋ ሳንቆርጥ፣ ሌሎች ነጻ እንዲያወጡን ሳንጠብቅ፣ የድርሻችንን እንወጣ።
No comments:
Post a Comment