Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, January 28, 2014

ህወሓት/ኢህአዴግ የትግራይ ህዝብ አማራጭ ሀሳብ እንዳያገኝ እያካሄደ ያለውን አፈና አጥብቀን እንቃወማለን!!! ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ፤
ፓርቲያችን አንድነት በአፅንኦት እንደሚያምነው የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የዴሞክራሲ ዕጦት ሰለባ ነው፡፡ስርዓቱ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል እንደሚያደርገው በትግራይም ሰብዓዊ መብት ይረግጣል፣ ፍትህ ይደፈጥጣል፣ በካድሬዎች ይደበደባል፣ ይንገላታል፣ እንዲሰደድ ይደረጋል፡፡ ስርዓቱና በስርዓቱ ውስጥ የደላቸው ሹማምንት በስሙ ከመነገድ በዘለለ ዋጋ የተከፈለበትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዘርግቶ ተጠቃሚ ማድረግ አልቻለም፡፡ ህወሓት/ኢህአደግ ክልሉን እንደዋና ካምፕ በማየት በአፈና ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ የትግራይ ህዝብ የነፃ ፕሬስ ውጤቶችን እንዳያገኝ፤ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዳያዳምጥ የተፈረደበት ሕዝብ ነው ማለት ማጋነን አይደለም፡፡ ይሄ እውነትም ሕወሓት/ኢህአዴግ በተለያየ ጊዜ በህዝቡ ላይ በፈፀማቸው ኢ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች የታየ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አምባገነኑ ህወሓት/ኢህአዴግ አረና ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል አዲግራት ከተማ ሊያደርግ የነበረው ሕዝባዊ ስብሰባ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ታፍኖበታል፣ አባላቱ ተደብድበዋል እንዲሁም ታስረዋል፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት የትግራይ ህዝብ አማራጭ እንዳያገኝና በጉልበት የህወሓት አንጡራ ሀብት ብቻ ሁኖ እንዲያገለግል ከመፈለግ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ፓርቲያችን በመቀሌ ከተማ ሊያደርግ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በከፍተኛ አፈናና እስር እንዲያስተጓጉል መደረጉ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ የትግራይ ህዝብ አማራጭ ሓሳብ የማዳመጥ፣ የሚጠቅመውን የመምረጥና የመቃወም ሕገ-መንግስታዊ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን በፅኑ ያምናል፡፡ ስለዚህ አማራጭ ሓሳብ በሚያቀርቡ ፓርቲዎች ላይ ህወሓት/ኢህአዴግ እየወሰደ ያለውን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ርምጃና አፈና በጥብቅ እንቃወማለን፡፡ አንድነት የአረና ፓርቲ የሚያደርገውን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ ህወሓት/ኢህአደግ ለማደናቀፍ የሚያደርገውን ህገወጥ ዘመቻ እንዲያቆም እየጠየቀ አሁንም ተቃዋሚዎችን ‹‹ከጠላቶቻችን ጋር የሚተባበሩ›› በማለት የትግራይን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለመነጠል የሚካሄደውን ዘረኝነት የተሞላበት ከፋፋይ ርምጃ ለአገራችን እጅግ አደገኛ እንደሆነ አምኖ እንደ ሌላው ህዝብ ሁሉ ለነፃነቱ መከበር የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥልና ሰላማዊ ትግሉን በመደገፍ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን እንዲሆን የከበረ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ!!! አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጥር 19 ቀን 2006ዓ.ም አዲስ አበባUDJ

No comments:

Post a Comment

wanted officials