አስገራሚ ዜና – ሽመልስ ከማል ተሳደቡ፣ አስፈራሩ “በአብዛኛዎቹ የህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚታየው ማስታወቂያ እንጥል እቆርጣለሁ፣ ግግ እቧጥጣለሁ የሚል የአንድ ደብተራ ማስታወቂያ ነው” አቶ ሽመልስ ከማል መንግስት የህትመት ውጤቶች አከፋፋዮች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ፍንጭ ሰጠ በዘሪሁን ሙሉጌታ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በሀገሪቱ ውስጥ ፈርጀ ብዙ ኀሳቦች ለህብረተሰቡ እንዳይደርስ እያደረጉ ነው ባሉዋቸው የጋዜጣና መፅሔት አከፋፋዮች ላይ መንግስት በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቁ። ሚኒስትር ዴኤታው ይሄህን የተናገሩት “የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስትና የመገናኛ ብዙኃን ግንኙነት” በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት በኢንተርኮንቲነታል ሆቴል ሰሞኑን ባዘጋጀው የአንድ ቀን ሲምፖዚየም መዝጊያ ላይ ነው። የፕሬስ ነፃነት አፈና ሲነሳ በአከፋፋዮች አማካኝነት የሚደረግ አፈና አንዱ መሆኑን በመጥቀስ ጥቂት መፅሔቶችንና ጋዜጦችን በባለቤትነት የያዙ ግለሰቦች የማከፋፈል ስራውን በሞኖፖል ይዘው የአመለካከት ፈርጀ ብዙነት እንዳይኖር በማድረግ፣ በርካታ ህትመቶችን በለጋነታቸው ለሞት እንዲበቁ በማድረግ የአፈና ስራ ውስጥ የገቡ ወገኖች አሰራራቸው በፍጥነት መስተካከል አለበት ብለዋል። “ሚዲያን የመደጎምና የማስተካከሉ ስራ መንግስት በአግባቡ በተጠና ሁኔታ መግባት እንዳለበት ያምናል” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው በሚዲያ የኀሳብ ገበያ ውስጥ ምቹ ሁኔታዎችን በማዘጋጀት ለኢንዱስትሪው ቀና እድገት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአከፋፋዮች በኩል በርካታ ችግሮች ተለይተው እየተጠኑ መሆኑንም ጠቁመዋል። የህትመት ሚዲያው ብቻ ሳይሆን የሕዝብ የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች ከችግሮች ነፃ አለመውጣታቸውንም የጠቀሱት አቶ ሽመልስ መንግስት ፈጣን መረጃ የሚሰጥ የሚዲያ ስርዓት እንዲፈጠር እንደሚፈልግ ገልጸዋል። መንግስት መረጃዎችን በገፍ የሚያቀርብ፣ ጥራት ባለውና ወቅታዊ በሆነ መንገድ የሚሰራ የሚዲያ ስርዓት እንዲገነባ ይፈልጋልም ብለዋል። ብሔራዊ የሚዲያ ፖሊሲው በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የህብረተሰቡን የፖለቲካ ብዙሃነት፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ፈርጀብዙነት ከመቀበል የሚነሳ መሆኑ አስታውሰው፤ ነገር ግን ሚዲያው በማንኛውም የባለቤትነት ውስጥ ቢሆንም ብሔራዊ መግባባትን ለማስረፅ መተኪያ የሌለው ቀዳሚ ሚና እንዲጫወት ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል። ሚዲያው በብሔራ ዊ መግባባት ላይ እንዲሰራ መንግስት ቢፈልግም ከማንኛውም ርዕዮተዓለም ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆን ይፈልጋል ብለዋል። አሁን ያለው የሚዲያ ችግር በንግድ ሚዲያ መርህ ወይም በገበያ መርህ መንቀሳቀስ አለመቻል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽመልስ አብዛኛዎቹ ሚዲያዎቻቸው ገበያቸውን ከማስታወቂያ የሚሸፍኑ አይደሉም ብለዋል። “በአብዛኛዎቹ የህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚታየው ማስታወቂያ “እንጥል እቆርጣለሁ፣ ግግ እቧጥጣለሁ” የሚል የአንድ ደብተራ ማስታወቂያ ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ማስታወቂያ የላቸውም። ኮሜርሺያል አይደሉም፤ ኮሜሪሻያል ካልሆኑ ይደጎማሉ። በድጎማ የሚተዳደሩ ከሆነ ታማኝ አንባቢ ነው ያላቸው። ከተወሰኑ ርዕዮተአለማዊ አጥሮች አልፈው መጓዝ አይፈልጉም። ስለሆነም የህትመት ሚዲያ እድገት ላይ አንድ ትልቅ ጋሬጣ የሆነው ከነፃ ሚዲያ ህግጋት ውጪ ተንጋዶ የበቀለ የሚዲያ አካሄድ ነው” ያሉት አቶ ሽመልስ ይህንን ለማስተካከል መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ሊተባበሩ ይገባል ብለዋል። የሰንደቅ ዜናዎች (ጥር 21/2006)
No comments:
Post a Comment